ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ሲኖዶሳዊነት በኅብረት ወደ ፊት ለመጓዝ ተስፋ ሰጪ መንገድ ሆኖ መገኘቱን ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ማር አዋ ሳልሳዊን እና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በምሥራቅ አሦራውያን ቤተ ክርስቲያን መካከል በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሥነ-መለኮታዊ ውይይት የጋራ ኮሚሽን አባላትን ሰኞ ጥቅምት 17/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለዋል።
ቅዱስነታቸው ከእንግዶቹ ጋር ባደረጉት ንግግር፣ የብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ማር አዋ ሳልሳዊን እና የኮሚሽኑ አባላት የወንድማማችነት ጉብኝት እና ሥነ-መለኮታዊ ውይይት ወደ አንድነት በሚወስደው መንገድ ላይ እርስ በርስ የሚስማሙ መሆናቸውን ይመሰክራሉ” ሲሉ አብራርተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በንግግራቸው እውነተኛ ውይይት ቤተ ክርስቲያኖቻችንን አንድ የሚያደርግ የፍቅር መግለጫ ሲሆን በጎነት ያለበት ውይይትም በሥነ-መለኮታዊ መንገድ ግንዛቤን ማግኘት እንዳለበት አፅንዖት ሰጥተዋል።
የዕድገት ጊዜ
በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ይፋዊ ውይይት የተጀመረበትን 30ኛ ዓመት ለማክበር ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ማር አዋ ሳልሳዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. ሮምን መጎብኘታቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “የቀደሙት አባቶች ሐዋርያዊ ሥልጣን እና መንገድ በታማኝነት በመከተል በእነዚህ ዓመታት የተገኘው ዕድገት ጉልህ ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ማር ዲንካ አራተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1994 ዓ. ም. በጋራ ያወጡትን መግለጫ በመጥቀስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደተናገሩት፥ “እምነትን፣ ቅዱሳት ምስጢራትን እና የቤተ ክርስቲያን ሕግን በማስመልከት ያቀረቡት የጋራ ሃሳብ አንድነትን የሚያመላክት ነው” ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።
ሦስት ርዕሦችን የያዘው መግለጫው በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ባለው ሥነ-መለኮታዊ ውይይት ውስጥ ለቀጣዮቹ እርምጃዎች ማዕቀፍ ፈጥሯል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ1994 ዓ. ምሕረቱ ሠነድ ለ1,500 ዓመታት የቆየን ውዝግብ ለመፍታት የረዳ ሲሆን፥ ይህም በተራው በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የተደረገው የተራዘመ ውይይት በቅዱሳት ምስጢራት የጋራ እውቅና እና በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል የተወሰነ የአምልኮ ግንኙነት እንዲኖር ማስቻሉ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በጋራ ኮሚሽኑ ውስጥ የሚገኙ የነገር-መለኮት ሊቃውንት እነዚህን ስምምነቶች ለማሳካት ላደረጉት ቁርጠኝነት እና ጥረት ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
አዲስ ትኩረት
“አሁን በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ውይይት የሚያተኩረው በቤተ ክርስቲያን ሕገ ላይ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “ዋናው ፈተና በመጀመሪያው ሺህ ዓመት በመመርኮዝ የሙሉ ኅብረት ሞዴል ማዘጋጀት እና ለዘመናችን ተግዳሮቶች ቅን ምላሽ መስጠትም ጭምር ነው” ብለዋል።
የቀድሞው አባቶች እንደተከራከሩት ሁሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ይህ ሊሳካ የሚችለው በውይይት እንጂ የበላይነትን በማንጸባረቅ አይደለም” ብለው ይልቁንም ሞዴሉ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የስጦታ መጋራትን ማበረታታት እንዳለበት አሳስበዋል።
“ወደ ሙሉ ኅብረት በሚደረገው በዚህ ጉዞ ሲኖዶሳዊነት በኅብረት ወደ ፊት ለመጓዝ ተስፋ ሰጪ መንገድ ሆኖ ተገኝቷል” ሲሉ ቅዱስነታቸው አፅንዖት ሰጥተዋል። በመቀጠልም በሲኖዶሳዊነት ጉዞ የመጨረሻ ሠነድ ላይ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተናገሩትን ቃል በማስታወስ፥ “በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተካሄደው የሲኖዶሳዊነት ሂደት እንደ ሲኖዶሳዊ የክርስቲያኖች እንቅስቃሴ የአንድነት መሆን አለበት” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ቅዱስ ሲኖዶስን በአእምሯቸው በመያዝ፥ የኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል በሁሉም ክርስቲያኖች መካከል ሲኖዶሳዊነትን በተጨባጭ ተግባራዊ ለማድረግ እና አዲስ የሃይማኖታዊ ሲኖዶሳዊነት ልማዶችን ለማነሳሳት እንደሚረዳቸው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በዚህ የውይይት ጉዞ ላይ የሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ቅዱሳን በተለይም የነነዌው ቅዱስ ይስሐቅ አማላጅነትን ጠይቀው፥ በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ ክርስቲያኖች ዘወትር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ምስክርነት እንዲሰጡ በመጸለይ፥ “የጋራ ውይይታችን ወደ አንድ መሠዊያ ፊት ቀርበን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ስጋ እና ደም ወደምንጋራባት የተባረከች ቀን የሚያደርስ እና ይህንም ዓለም እንዲያምን” (ዮሐ. 17:21)” ሲሉ ጠይቀዋል።
