ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሆስፒታል ውስጥ ሌላ ጥሩ ምሽት ማሳለፋቸው ተገለጸ!
“ሌሊቱ በመልካም ሁኔታ አለፏል፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አሁንም እረፍት እያደረጉ ነው" ሲል የቅድስት መንበር የፕሬስ ጽ/ቤት ሐሙስ ማለዳ የካቲት 27/2017 ዓ.ም ለጋዜጠኞች አስታውቋል።
ረቡዕ አመሻሽ ላይ የፕሬስ ጽ/ቤት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የጤና ሁኔታን አስመልክቶ የየዕለቱን የህክምና መረጃ በማቅረብ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል።
"ቅዱስ አባታችን ምንም አይነት የመተንፈሻ አካላት ችግር ሳይገጥማቸው ዛሬም ተረጋግተው በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። በእቅዱ መሰረት፣ ተጨማሪ፣ ከፍተኛ ፍሰት ያለው ኦክሲጅንና የሜካኒካል አየር መተንፈሻ መሣርያ ተጠቅመዋል" ሲል መግለጫው አክሎ ገልጿል።
"ቅዱስ አባታችን የአተነፋፈስ ሁኔታቸው እየተሻሻለ መጥቷል፥ ከጤና ሁኔታቸውውስብስብነት አንጻር ትንበያው እንደተጠበቀ ይቆያል" ያለው መግለጫው ትላንት ረዕቡ እለት የካቲት 26/2017 ዓ.ም ጠዋት በ10ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው የግል አፓርታማ ውስጥ ሁነው ቅዱስ አባታችን በእለቱ የተጀመረውን የዐብይ ጾም ምክንያት በማድረግ የተከናወነውን የዐመድ መቀባት መንፈሳዊ ሥነ-ሥነስርዓት ላይ ተሳትፈዋል፣ ከእዚያም ቅዱስ ቁርባን መቀበላቸው ተገልጿል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካቲት 7/2017 ዓ.ም ሆስፒታል ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ በሁለትዮሽ የሳንባ ምች በሽታ በመጠቃታቸው የተነሳ በሮማ ከተማ በሚገኘው የጂሜሊ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ይታወቃል።
የእርሳቸው የሁለትዮሽ የሳንባ ምች በሕክምና ውስጥ የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ መደበኛውን ዝግመተ ለውጥ ይከተላል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከታዘዙት የሕክምና ዘዴዎች ጋር በንቃት ይተባበራሉ፣ ስሜታቸውም መልካም ነው።
የጳጳሱ ዶክተሮች ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ቀውሶች አለመኖራቸውን ያብራራሉ፣ ነገር ግን ለተጨማሪ ግምገማዎች ጊዜ ያስፈልጋል። የጤና ሁኔታቸው ሁኔታ ውስብስብ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ቢገኝም የተረጋጋ ሆኖ ይቆያል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 20 ቀናት ያህል በሆስፒታል ውስጥ አሳልፈዋል።