ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሲየና ቅድስት ካትሪን የትምህርት ቤት ሚሲዮናዊያንን በቫቲካን ተቀብለው ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሲየና ቅድስት ካትሪን የትምህርት ቤት ሚሲዮናዊያንን በቫቲካን ተቀብለው   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሚስዮናውያን ውይይትን እና መንፈሳዊ ደስታን እንዲያስፋፉ አሳስቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማስተማር አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ሚስዮናውያት ኅብረትን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው የሲየና ቅድስት ካትሪን የትምህርት ቤት ሚሲዮናዊት ኅብረት አባል ለሆኑት የዶሚኒካን እህቶች ባደረጉት ንግግር፥ ግልጽነትን መሠረት ያደረገ የቅድስና፣ የዝግጅት እና የደስታ ተልእኳቸውን እንዲቀጥሉ ብርታትን ተመኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የምሥረታቸውን መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሮም አሥራ አምስተኛ ጥቅላላ ስብሰባ ካካሄዱትን የሲየና ቅድስት ካትሪን የትምህርት ቤት ሚሲዮናዊ ገዳማውያት ጋር ቅዳሜ ታኅሳስ 26/2017 ዓ. ም. በቫቲካን ተገናኝተዋል።

የዶሚኒካን ገዳማውያት ማኅበር በጣሊያን የተመሠረተው እንደ ጎርጎሮሳውያን በ1924 ዓ. ም. ሲሆን፥ ዋና ተልዕኮው የሉዊጂያ ቲንካኒ እና የቅዱስ ዶሜኒኮስ ገዳም ካኅን የአባ ሉዶቪኮ ፋፋኒ የወንጌል እሴትን ከማስፋፋት በተጨማሪ ለእምነት ደንታ በሌላቸው እና ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ባሉት መካከል ክርስቲያናዊ ሰብዓዊነትን ለማስተዋወቅ እንደ ሆነ ይታወቃል። ማኅበሩ በሮም በምሕጻረ ቃሉ “LUMSA” ወይም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕርገት ነጻ ዩኒቨርሲቲ መመሥረቱ ይታወቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለገዳማውያቱ ባደረጉት ንግግር፥ “የጊዜውን ሁኔታ በመረዳት ከቤተ ክርስቲያን ጋር በመሆን በኅብረቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ማሰላሰል” ለሚለው መሪ ቃል ምስጋናቸው አቅርበው፥ ይህም ከመሠረታቸው ክርስቲያናዊ ሰብዓዊነትን የማሳደግ እና መንፈሳዊ ፍላጎቶችን ከማስተናገድ ራዕይ እና ከዘመናዊ ማኅበረሰብ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ጠቁመው፥ ተልዕኮአቸውን መሠረት ያደረጉ ሦስት መሠረታዊ አስተሳሰቦችን እነርሱም ቅድስና፣ ዝግጅት እና ተወዳጅነት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቅድስና መንፈሳዊ ደስታ ነው!
ምንም እንኳን ብዙውን ጊዜ የሚያስፈራ ወይም ሊደረስበት የማይችል ቢመስልም ቅድስና የጋራ ጥሪ እና የሁሉም ክርስቲያኖች የመጨረሻ ዓላማ እንደሆን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አፅንዖት ሰጥተዋል። መንፈሳዊ ደስታ የሆነው ቅድስና ፈተናዎችን በመገንዘብ በእግዚአብሔር ፀጋ የሚገኝ እና በዛሬው ዓለም በተለይም ወጣቶችን ለማነሳሳት ወሳኝ እንደሆነ ገዳማውያቱን አስታውሰዋል።

ገዳማውያቱ ቅድስናን ለክርስቶስ ባላቸውን ቁርጠኝነት በወንጌል ምክርነት፣ በቅዱስ ቁርባን ሕይወት፣ የእግዚአብሔርን ቃል በየዕለቱ በማዳመጥ እና በማሰላሰል፣ በጸሎት እና በማኅበረሰቡ ሕይወት ውስጥ “የማሰላሰል ፍሬዎችን ለሌሎች ማስተላለፍ” የሚለውን የቅዱስ ዶሜኒኮስ ማኅበር መሪ ቃል እንደሚያስተምር አስረድተው፥ እነዚህ መሠረቶች ሐዋርያነታቸው ውጤታማ እና በመንፈሳዊነታቸው ፍሬያማ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጸንተው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል። “ቅድስናን ማግኘት ቀላል ባይሆንም አስደሳች እና የሚስብ መንፈሳዊ ደስታ ነው” ሲሉ አክለዋል።

ከሁሉም ሰው ጋር መወያየት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡት ሁለተኛው አመለካከት ቅድመ ዝግጅት ሲሆን፥ ይህም ተጨባጭ የሆነ ተግባራዊ ቅልጥፍና ሳይሆን ነገር ግን በወንጌላዊነት ራስን መወሰን፣ ቀጣይነት ባለው ጥናት ጥልቅ እውቀትን እና ችሎታን በማዳበር የሚኖሩት ሕይወት እንደሆነ እና በግል በማሰላሰል የተማሩትን እውነቶች በወንድማማችነት ለሌሎች ማካፈል እንደ ሆነ አስረድተዋል።

አክለውም ቅድመ ዝግጅቱ የማስተማር እና የመገናኛ ዘዴዎችን በማዘመን በማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መልካም የሆኑትን በግልጽ ከሁሉም ጋር መወያየትን እንደሚያካትት ገልጸዋል። በዚህ ረገድ በማኅበረሰቦች መካከል ቅናትን እና አለመግባባትን ከሚዘራው ከዲያብሎስ ጋር ካልሆነ በቀር ከሁሉም ጋር መወያየት አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስነታቸው አጥብቀው ተናግረዋል።

የደስታ እና የወዳጅነት መልዕክተኞች መሆን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፣ የዶሚኒካን ማኅበር ገዳማውያት በእርስ በርስ ግንኙነት ማንኛውንም ዓይነት ልዩነቶች በምስጋና በመቀበል የመንፈስ ቅዱስ እና የደስታ ስጦታ የሆነው የወዳጅነት መልዕክተኞች እንዲሆኑ አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው በማጠቃለያቸው፥ ቅድስናን፣ ዝግጅትን እና ወዳጅነትን መሠረት በማድረግ ተልዕኮአቸውን በግልጽ እና በድፍረት አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ለማደስ ዝግጁዎች ሆነው እንዲቀጥሉ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።
 

04 January 2025, 16:25