ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ተስፋ ማድረግ አያሳዝንም” ሲሉ አስገነዘቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ተስፋ ማድረግ ፈጽሞ የማያሳዝን በመሆኑ እኛ ክርስቲያኖች አንድ ላይ ሆነን በጸሎት መጽናት አለብን” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፥ የቅዱስ ሄንሪ ዓመታዊ በዓልን ለማክበር ወደ ሮም ለተጓዘው የፊንላንድ ልዑካን ቡድን ሰኞ ጥር 12/2017 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ባደረጉት ንግግር ነው።
የፊንላንድ የክርስቲያኖች አንድነት ማኅበር ቡድን ከጥር 10-17 ድረስ በሚዘጋጀው ዓመታዊ የክርስቲያን አንድነት የጸሎት ሳምንት ላይ ለመገኘት ወደ ሮም በሚመጣበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እንደሚገበኝ ይታወቃል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቡድኑ አባላት ባሰሙት ንግግር፥ “በዚህ ቅዱስ የኢዮቤልዩ ዓመት 2025 ዓ. ም. የተስፋ ተጓዦች በመሆን አብረን እንጓዛለን” ብለዋል። በማከልም፥ “በእምነት ጉዟችን ውስጥ የተስፋን ቃል የሰጠን የታመነ እንደሆነ ለዕብራውያን የተላከው መልዕክት ስለሚያረጋግጥልን ሳንጠራጠር ምስክርነታችንን እንጠብቅ” ብለዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ዐውድ ውስጥ ቅዱስ ሄንሪ የዚህ ተስፋ ዘላቂ ምስክር እና በእግዚአብሔር ላይ አስተማማኝ እና ቋሚ መሠረት ያለው መሆኑን አስታውሰዋል።
በጸሎት መጽናት
“ቅዱስ ሄንሪ ደካማ ቢሆንም ነገር ግን የሰላም መልዕክተኛ እንደመሆኑ ውድ የሆነውን የሰላም ስጦታ በጸሎት ተግተን እንድንጠብቅ ያሳስበናል” ብለው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን የክርስትና እምነት ላይ በማስተንተን ለሰላም በጋራ መጸለይ አስፈላጊ እንደሆነ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በሥጋ የገለጠ እውነተኛ ጌታችን እና መድኃኒታችን መሆኑን በማስታወስ፥ እርሱ ለእኛ ያለንን ፍቅር ልንቀበል ይገባል ብለዋል።
በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን ተስፋ ፈጽሞ የማያሳዝን መሆኑን አጥብቀው የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ሞት ቢሆን ሕይወት፣ መላዕክት ቢሆኑ ገዢዎች፣ ያለውም ቢሆን የሚመጣው፣ የሥልጣን ከፍታ ቢሆን ዝቅታ፣ በፍጥረት ሁሉ ዘንድም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን የሚችል ምንም የለም” ሲሉ አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ሥጋ የለበሰውን የእግዚአብሔር ፍቅር መመስከር ለተጠመቁት በሙሉ የጋራ መንፈሳዊ ጥሪያችን ነው” ሲሉ አስረድተው፥ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ በሥፍራው የተገኙትን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ጸሎት አብረው እንዲያደርሱ ከጋበዟቸው በኋላ ለጉብኝታቸውም ልባዊ ምስጋናን በማቅረብ የእግዚአብሔርን ቡራኬ ሰጥተው ሸኝተዋቸዋል።