ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሎስ አንጀለስ የእሳት አደጋ ሰለባ የሆኑትን በጸሎታቸው አስታወሱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ ሎስ አንጀለስ ከተማ አቅራቢያ በተነሳው የእሳት አደጋ በደረሰው የሕይወት መጥፋት እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው ለሎስ አንጀለስ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሆሴ ጎሜዝ በላኩት መልዕክት፥ በአደጋው ከተጎዱ ጋር በመንፈስ ከጎናቸው መሆናቸውን ገልጸው፥ የሟቾችን ነፍስ ለልዑል እግዚአብሔር ፍቅራዊ ምሕረት በአደራ ሰጥተዋል።
በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በተፈረመው መልዕክታቸው፥ በአደጋው በሞቱት ሰዎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸው፥ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችንም በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው ተናግረዋል።
የእሳት አደጋው መጠን
በሎስ አንጀለስ አካባቢ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ 12,000 የሚያህሉ ሕንፃዎችን በማውደም ቢያንስ ለ11 ሰዎች ሕልፈት ምክንያት እንደሆነ እና በሺዎች የሚቆጠሩትን ከቄያቸው ማፈናቀሉ ታውቋል።
ባለፈው ማክሰኞ የጀመረው የእሳቱ ቃጠሎው ሐሙስ ዕለት መቀነሱ ቢነገርም ነገር ግን በሳምንቱ መጨረሻ ሊመለስ እንደሚችል ትንበያዎች አስጠንቅቀዋል።
የአየር ሁኔታ መረጃን የሚያቀርብ አንድ የግል ድርጅት እንዳስታወቀው፥ የጉዳቱ መጠን በገንዘብ ሲተመን ከ135 እስከ 150 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ገምቷል።
እሳቱ በጠቅላላው ከሳን ፍራንችስኮ ከተማ በሚበልጥ 142 ካሬ ኪሎ ሜትር ማዳረሱ ሲነግር ይህም መስጊድን፣ ምኩራብን፣ ካቶሊካዊ ቁምስናን እና ግማሽ ደርዘን የሚሆኑ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያናትን ማካተቱ ታውቋል