ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሁሉም ሰው ስለ ትምህርት መብት እንዲጸልይ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመማር መብትን በማስመልከት ያዘጋጁትን የጥር ወር የጸሎት ሃሳባቸውን በዓለም አቀፉ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ በኩል ይፋ አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በወርሃዊ የጥር ወር የጸሎት ሃሳባቸው ሁሉም ሰው ስለ ትምህርት መብት እንዲጸልይ ጋብዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም አቀፉ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የጸሎት አውታረ-መረብ በኩል ለመላዋ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ይፋ ባደረጉት መልዕክታቸው፥ ቤተ ክርስቲያን ስለ ትምህርት መብት እንድትጸልይ የአደራ ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ለጥር ወር እንዲሆነ ብለው በላኩት የቪዲዮ መልዕክት፥ “ምንም ማጋነን አይሁንና
ዛሬ የትምህርት ውድመት እያጋጠመን ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

250 ሚሊዮን የሚሆኑት የትምህርት ዕድል የላቸውም!
“በጦርነት፣ በስደትና በድህነት ምክንያት ወደ 250 ሚሊዮን የሚጠጉ ወንድና ሴት ልጆች ትምህርት አጥተዋል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “በስደት ላይ የሚገኙ ቢሆንም ልጆች እና ወጣቶች ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ መብት አላቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም “ትምህርት የሁሉም ሰው ተስፋ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ትምህርት ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከአድልዎ፣ ከወንጀለኞች መረብ እና ከብዝበዛ ሊያድናቸው ይችላል” ሲሉ አስረድተዋል።

ትምህርት የአንድነት መሣሪያ ነው!
“በስደት ላይ የሚገኙ እጅግ በርካታ ታዳጊ ሕጻናት ይበዘበዛሉ!” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ትምህርት አስፈላጊ እንደ ሆነ በመጠቆም፥ ተቀብለዋቸው ከሚያስተናግዷቸው ማኅበረሰቦች ጋር እንዲዋሃዱ ሊረዳቸው ይችላል” ብለዋል።

የተሻለ የወደፊት ሕይወት
“ትምህርት ለተሻለ የወደፊት ሕይወት በሮችን ይከፍታል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዚህ መንገድ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ አገራቸው ለመመለስ ሲወስኑ ወይም በተሰደዱበት አገርም ቢሆን ለኅብረተሰቡ አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላሉ” ሲል አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ስደተኞችን የሚቀበል ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደተቀበለ ፈጽሞ አንርሳ” ብለው፥ ምእመናን ይህን መነሻ በማድረግ ስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና በጦርነት የተጎዱት ሰዎች የበለጠ ሰብዓዊ ዓለምን ለመገንባት የሚያስፈልጋቸው የትምህርት መብታቸው ዘወትር እንዲከበርላቸው መጸለይ እንደሚገባ በማሳሰብ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቪዲዮ መልዕክት
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቪዲዮ መልዕክት የቅዱስነታቸውን ወርሃዊ የጸሎት ሃሳቦችን የማሰራጨት ዓላማ ያለው ይፋዊ ዓለም አቀፍ ተነሳሽነት ሲሆን፥ የሚከናወነውም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት መረብ ወይም የጸሎት ሐዋርያነት በኩል እንደ ሆነ ይታወቃል።

ከ 2008 ዓ. ም. ጀምሮ ሲሰራጭ የቆየው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቪዲዮ መልዕክት በሁሉም የቫቲካን ማኅበራዊ አውታረ መረቦች ውስጥ ከ 203 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች ያሉት እና ከ 23 በላይ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በ 114 አገራት ውስጥ ሽፋን እንደሚያገኝ ታውቋል።

የቪዲዮ መልዕክቶቹ የሚቀነባበሩት አቶ አንድሪያ ሳሩቢ በሚያስተባብሩት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቪዲዮ ጸሎት ኔትወርክ ቡድን ተዘጋጅቶ በ “ላ ማኪ ኮሙዩኒኬሽን” እንደሚሰራጭ እና መርሃ ግብሩም በቫቲካን ሚዲያ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግለት ታውቋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት መረብ የቫቲካን ፋውንዴሽን ሲሆን፥ ካቶሊካዊ ምዕመናንን በጸሎት እና በተግባር የሚሰባሰብ፥ ዋና ዓላማውም ለሰው ልጅ እና ለቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ምላሽ ለመስጠት ሲሆን፥ በዓለማችን የሚታዩ ልዩ ልዩ ተግዳሮቶችን በማስመልከት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለመላዋ ቤተ ክርስቲያን በሚያዘጋጁት ወርሃዊ የጸሎት ሐሳብ በኩል እንደሚቀርብ ይታወቃል።
 

08 January 2025, 14:50