ፈልግ

አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ጄ. ትራምፕ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ጄ. ትራምፕ   (2025 Getty Images)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ለተወዳጁ የአሜሪካ ሕዝብ መለኮታዊ በረከቶችን እለምናለሁ!” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሆነው ለተሾሙት ዶናልድ ጄ. ትራምፕ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸው ላይ ለተወዳጁ የአሜሪካ ሕዝብ፣ ለተመራጩ ፕሬዚደንት ትራምፕ እና ቤተሰባቸው መለኮታዊ በረከቶችን በመለመን ወደ ሰላም የሚያደርጉትን ጥረት እግዚአብሔር እንዲመራው ጸሎት አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በሕዝቦች መካከል ሰላም እና ዕርቅ እንዲሰፍን የሚያደርጉትን ጥረት እግዚአብሔር እንዲመራው እጸልያለሁ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጸሎታቸውን ያቀረቡት በሀገሪቱ ታሪክ 47ኛ ፕሬዚደንት ሆነው ለተሾሙት ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ጄ. ትራምፕ ሰኞ ጥር 12/2017 ዓ. ም. በላኩት መልዕክታቸው ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን በመቀጠል፥ “የአሜሪካ አርባ ሰባተኛው ፕሬዚዳንት ሆነው በተመረጡበት ወቅት የተጣለቦትን ከፍተኛ ኃላፊነቶች በትጋት እንዲወጡ ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ጥበብን፣ ጥንካሬን እና ጥበቃን እንዲሰጥዎ ጸሎቴን አቀርባለሁ” ብለዋል።

“ራስን በሥራ መለወጥ እና ሁሉንም ሰው ተቀብሎ ማስተናገድ የሚለውን የሀገርዎን መርህ በመያዝ፥ በእርስዎ የአመራር ዘመን የአሜሪካ ሕዝብ ጥላቻን፣ መድልዎን እና መገለልን አስወግዶ ለብልጽግና እና የበለጠ ፍትሃዊ ማኅበረሰብን ለመገንባት ዘወትር እንደሚተጋ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም፥ “ሰብዓዊ ቤተሰባችን የጦርነት መቅሠፍት ሳያንሰው በብዙ ፈተናዎች ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ወቅት በሕዝቦች መካከል ሰላም እና ዕርቅን ለማስፋፋት የሚያደርጉትን ጥረት እግዚአብሔር እንዲመራው እጸልያለሁ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ “ከዚህ ስሜት ጋር ለእርስዎ፣ ለቤተሰብዎ እና ለተወዳጁ የአሜሪካ ሕዝብ የተትረፈረፈ መለኮታዊ በረከቶችን እለምናለሁ” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።


 

21 January 2025, 09:49