ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የሕይወት ጎዞን ኢየሱስ በሚሰጠው ተስፋ መጀመር እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከኮርዶባ ሀገረ ስብከት ከመጡ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች ጋር ጥር 9/2017 ዓ. ም. ረፋድ በቫቲካን ተገናኝተው ሰላምታ ካቀረቡላቸው በኋላ የሕይወት ጉዞን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር፥ በሕይወት ጎዳና ውስጥ የተለያዩ የተስፋ ምልክቶች መኖራቸውን አብራርተዋል።
ጉዞ ወደ ሰማዩ ቤታችን!
“ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመገናኘት ወደ ሰማዩ ቤት ለመድረስ የሚደረግ አቢይ ጉዞ የመጀመሪያው የተስፋ ምልክት ነው” ሲሉ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።
ይህ የጉዞ አቅጣጫ ወደ ምቹ ሕይወት እንደማይመራ አሳስበው፥ ምክንያቱም ምቾትን መምረጥ ወደ ሞት የሚመራ መሆኑን ተናግረው፥ “የምቾት መንገድ መምረጥ በኀፍረት ወደ ኋላ መመለስን ያስከትላል” ብለዋል።
በጉዞ ላይ የሚያጋጥሙ ፈተናዎች
ሰዎችን በሕይወት ጎዞአቸው ወቅት ሊያጋጥሟቸው የሚችል ፈተና መኖሩን የሚያሳይ ሁለተኛ ምልክት መኖሩን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥
የዘርዓ ክኅነት ትምርት ቤት ወጣቶች የከተማቸው ተወላጅ የሆነው የቅዱስ ፔላጊዮስ የሕይወት ምሳሌ በመከተል በእግዚአብሔር መንገድ ላይ ጸንተው እንዲጓዙ እና በጉዞአቸው ወቅትም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚደግፋቸው እና የተስፋ ፍሬዎች እንዲሆኑ ብርታት እንደሚሰጣቸው አውቀው የተስፋ ዘሪዎች እንዲሆኑ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።
ለዕረፍት የሚቀርቡ ቦታዎች
ከኮርዶባ ሀገረ ስብከት የመጡ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች በሕይወት ጉዟቸው ወቅት አጭር ቆይታ ካደረጉበት አንዱ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ተገናኝተው የኢዮቤልዩ ዓመት ቅዱስ በር መሻገራቸው እንደሆነ ታውቋል።
“ሁሉም ሰው በሕይወቱ መካከል እና በቅዱስ ቁርባን ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚገኝ ሊያውቅ ይገባል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በጉዞአችን ወቅት ድካም ሲሰማን ማረፍ እንደሚገባ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይልን የሚጨምርልን መሆኑን አስረድተዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠን ተስፋ ይዘው ጉዞን ካልጀመሩት ወደ ፍጻሜው መድረስ እንደማይቻል ገልጸው፥ አንድ ሰው ወደ መድረሻው እንደሚደርስ እርግጠኛ መሆን የሚችለው በዚህ ተስፋ ሲተማመን ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።
ሆኖም የተስፋ ዘር መሆን ማለት፥ “በትህትና የተሞላ ቃል መናገር ወይም ጥሩ ነገርን መምረጥ ማለት አይደለም” ሲሉ ተማሪዎችን አስጠንቅቀው፥ የሕይወት መንገድ ሰው ብቻውን የሚጓዘው ሳይሆን፥ ነገር ግን ማኅበረሰብን ወደ መልካም በመምራት፣ ከአደጋ እና ከችግር በመከላከል፣ በመርዳት እና እግዚአብሔር ለተልዕኮአችን የሰጠንን ሰው መባረክን የሚጠይቅ መሆኑን በማስረዳት ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።