ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነት እና በኩባ የእስረኞች መፈታትን አደነቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእሑድ ጥር 11/2017 ዓ. ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ለዋለዉ የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እና ኩባ በቅርቡ የኢዮቤልዩ ዓመትን ምክንያት በማድረግ እስረኞችን እንደምትፈታ ማሳወቋን በማስታወስ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ይህን አድናቆታቸውን የገለጹት እሁድ ዕለት በሚመሩት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ ለተገኙት በሺዎች ለሚቆጠሩ ምዕመናን ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደነበር ታውቋል።
ስምምነቱን በማክበር ሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ጋዛ መድረሱን ማመቻቸት
በቅድሚያ የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ አደራዳሪዎችን እና ወደ ስምምነት እንዲደረስ ለማድረግ የተባበሩትን ሁሉ አመስግነዋል። ስምምነቱ በሁለቱም ወገኖች መካከል ወዲያውኑ እንደሚከበር ያላቸውን ተስፋ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ሁሉም ታጋቾች ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው እና ዘመዶቻቸው ጋር እንደገና መገናኘት እንደሚችሉ ተናግረው፥ እነርሱን እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠውላቸዋል።
ከዚህም በላይ አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ጋዛ እንደሚደርስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ በመጨረሻም ፍልስጤም እና እስራኤአል ‘ሁለት-መንግሥታት ይሁኑ’ በሚለው የመፍትሔ ሃሳብ ላይ መሥራት የቅድስት መንበር አቋም መሆኑን ደግመው ተናግረዋል።
እስራኤላውያንም ሆኑ ፍልስጤማውያን ግልጽ የተስፋ ምልክቶችን ማየት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “የሁለቱም አገራት የፖለቲካ ባለስልጣናት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ለሁለቱ ሀገራት ትክክለኛ መፍትሄ ሊያገኙ እንደሚችሉ አምናለሁ” ሲሉ ብርታትን ተመኝተው፥ ሁሉም ሰው ውይይትን፣ እርቅን እና ሰላም መምረጥ እንደሚገባ እና ለእነዚህ ሦስቱ ስኬታማነት ምእመናን ሁሉ እንዲጸልዩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ለምዕመናኑ ባሰሙት ንግግር፥ “በሁለቱ ወገኖች የተደረሰው ስምምነት ወዲያው ተግባራዊ ሆኖ ሁሉም ታጋቾች ወደ ቤታቸው ተመልሰው ከዘመዶቻቸው ጋር እንደሚገናኙ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
የኩባ መንግሥት የሰጠው ተጨባሽ ተስፋ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ የኩባ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ በተለያዩ ወንጀሎች የተከሰሱ 553 ሰዎችን የኩባ መንግሥት እንደሚፈታቸው ገልጸዋል። ውሳኔው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተነገረው፥ የኩባው ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ-ካኔል በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በፃፉት ደብዳቤ ሲሆን፥ “እስረኞቹ የሚፈቱት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. እየተከበረ ባለው መደበኛ የኢዮቤልዩ በዓል መንፈስ ነው” ሲል የኩባ መንግሥት አስታውቋል።
“ይህ ከኢዮቤልዩ ዓመት ዓላማዎች መካከል አንዱን የሚያካትት የታላቅ ተስፋ ምልክት ነው” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸውታል። ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ “በሰዎች እና በሕዝቦች ጉዞ ላይ እምነትን የሚጥሉ የዚህ ዓይነት ጅምር ሥራዎች በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ እንደሚከናወኑ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የኢዮቤልዩ ዓመት መመሪያ” በተሰኘው ጽሑፋቸው ላይ እንደገለጹት፥ “መንግሥታት ተስፋን ወደ ቀድሞ ሁኔታ ለመመለስ የታለሙ ጅምሮችን እንዲያራምዱ፥ ግለሰቦች በራሳቸው እና በኅብረተሰቡ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ለመርዳት የታሰበ የምህረት እና የይቅርታ ዓይነቶችን እና ሕግን ለማክበር የሚደረጉ ተጨባጭ ቁርጠኝነትን ጨምሮ በማኅበረሰቡ ውስጥ የመልሶ ማቋቋም ፕሮግራሞች ተግባራዊ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጥር 10-17/2017 ዓ. ም. ወደተዘጋጀው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ላይ በማትኮር በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን መልካም ሰንበትን ከመመኘታቸው አስቀድመው ባስተላለፉት መልዕክት፥ "ለክርስቲኖች አንድነት ጸሎት በሚደረግባቸው በእነዚህ ቀናት በሁሉም የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መካከል ያለው የሙሉ አንድነት ስጦታን ከእግዚአብሔር ዘንድ መለመናችንን አናቆምም” ሲሉ ተናግረው፥ “በጦርነት ለተሰቃዩ የዩክሬን፣ የፍልስጤም፣ የእስራኤል፣ የማያንማር እና ሌሎች ሕዝቦችም ዘወትር እንጸልይ” በማለት ምዕመናንን አሳስበዋል።