“ተስፋ” የሚለው የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሕይወት ታሪክ በ80 አገራት ውስጥ መሰራጨቱ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው እና “ተስፋ” በሚል ርዕሥ የተጻፈው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሕይወት ታሪክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 80 አገራት ማክሰኞ ጥር 6/2017 ዓ. ም. መድረሱ ታውቋል። መጽሐፉ በሰሜን አሜሪካ የእንግሊዝኛ ተናጋሪ አንባቢያንን በራንደም ሃውስ አሳታሚ ድርጅት በኩል እና በእንግሊዝ በቫይኪንግ አሳታሚ ድርጅት በኩል እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
የመጀመሪያው ታሪካዊ መጽሐፍ
ራንደም ሃውስ አሳታሚ ድርጅት መጽሐፉ ይፋ ከመሆን ቀደም ብሎ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፥ በዓይነቱ ልዩ የሆነው ይህ መጽሐፍ በመጀመሪያ ወደ አንባቢያን እጅ እንዲደርስ የታሰበው ከቅዱስነታቸው ዕርፍት በኋላ እንደ ነበር ገልጾ፥ ነገር ግን የተስፋ ኢዮቤልዩ ዓመት እየተከበረ ባለበት በቅዱስ ዓመት መጀመሪያ ላይ እንዲሆን መወሰኑን አስታውቋል።
በር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በግል የተዘጋጁ ፎቶዎች እና ያልታተሙ ጽሑፎች ቀርበዋል
መጽሐፉ በራሳቸው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተዘጋጁ የግል ጽሑፎችን ጨምሮ እስከ ዛሬ ያልታተሙ አስደናቂ ፎቶግራፎችን መያዙ ታውቋል።
ከስድስት ዓመታት በላይ ጊዜ ተሰጥቶበት የተጻፈው ይህ የቅዱስነታቸው ሙሉ የሕይወት ታሪክ የሚጀምረው ከሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ ሲሆን፥ የጣሊያን የዘር ሐረግ ያላቸው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅድመ አያቶች በድፍረት ወደ ላቲን አሜሪካ መፍለሳቸውን የሚተርክ እንደሆነ ታውቋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የሕይወት ታሪክ የሚዘረዝር መጽሐፉ የልጅነት ጊዜያቸውን፣ የወጣትነት ዕድሜ ጉጉታቸው እና ጭንቀታቸው፣ ጥሪያቸውን፣ ከአዋቂነት ዕድሜ እስከ ርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ዘመን ድረስ የኖሩትን ሕይወት እንደሚያጠቃልል ታውቋል።
ትረካዎች እና ታሪኮች
ቅዱስነታቸው በትዝታዎቻቸው፥ የጵጵስና ዓመታት ወሳኝ ጊዜያትን እና የዘመናችንን የተለያዩ ጠቃሚ እና አከራካሪ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል ዓለምን እያስጨነቁ ያሉ ጦርነቶች፣ የቤተ ክርስቲያን እና የሃይማኖት የወደፊት ዕጣ ፈንታ፣ የማኅበራዊ ፖሊሲ፣ ስደት፣ የአካባቢ ቀውስ፣ ሴቶች፣ የቴክኖሎጂ ዕድገቶች እና ጾታን ያስታወሱ ሲሆን፥ ከዚህም በላይ “ተስፋ” የሚለው መጽሐፋቸው በርካታ ራዕዮችን፣ ታሪኮችን እና ግንዛቤዎችን ያካተተ እንደሆነ ተመልክቷል።
ራንደም ሃውስ አሳታሚ ድርጅት በመግለጫው፥ የሕይወት ታሪካቸውን የሚገልጸው መጽሐፉ አስደሳች እና ለዛ ያላቸው ቀሳቃሽ እና አንዳንዴም አስቂኝ ገጠመኞችን መያዙን ገልጿል።
አሳታሚ ድርጅቱ ከዚህም በላይ፥ “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሕይወት ታሪክ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አንባቢያንን የሚማርክ እና ለመጪው ትውልድ የተስፋ ትሩፋት የሚሆን ልብ የሚነካ ሥነ-ምግባራዊ እና መንፈሳዊ ኪዳን ነው” በማለት ገልጾታል።