ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የዓለም መሪዎች የድሃ አገሮችን ዕዳ እንዲሰርዙ ጥሪ አቅርበዋል!

የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ዘንድ የ2025 ዓ.ም አዲስ አመት በትላንትናው እለት ተክብሮ ማለፉ ይታወሳል። በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምእመናን በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ ባስተላለፉት የአዲስ አመት መልእክት “የድሃ አገሮችን ዕዳ በመሰረዝ ወይም ጉልህ በሆነ መልኩ በመቀነስ ጥሩ ምሳሌ እንዲሆኑ” ለፖለቲካ መሪዎች ጠንካራ ጥሪ አቅርበዋል ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በምእመናን በተጨናነቀው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ንግግር ሲያደርጉ ሁልጊዜ አጥፊ ለሆነው ጦርነት "እብይ" ማለት እንደሚገባው በድጋሚ አጽንኦት ሰጥተው የገለጹ ሲሆን ጦርነት “ሁልጊዜ ያጠፋል” ሲሉ አስታውቀዋል።

እንዲሁም የትኛውም ሀገር ወይም ህዝብ "በዕዳ መጨፍለቅ" እንደሌለበት አሳስቧል።

የድሃ አገሮች ዕዳ መሰረዝ

በወቅቱ ለዓለም መሪዎች ባቀረቡት የይግባኝ ጥሪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “እግዚአብሔር ዕዳን ይቅር ለማለት የመጀመሪያው ነው” ያሉ ሲሆን ክርስቲያናዊ ባህል ያላቸው የአገር መሪዎች የድሃ አገሮችን ዕዳ በመሰረዝ ወይም በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ አርአያ እንዲሆኑ አበረታታለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

ሰላም ፈጣሪዎች ምስጋና

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል በአለም አቀፍ ደረጃ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ፍትህና ሰላምን ለማስፈን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እየሰሩ ላሉት ሁሉ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

“ግጭቶች በተከሰቱባቸው ብዙ ክልሎች ውስጥ ለውይይት እና ድርድር ለሚሰሩ ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብሏል። ሁሉም ውጊያ እንዲያበቃ እና ለሰላምና እርቅ ወሳኝ ትኩረት እንዲሰጡ እንጸልይ ያሉ ሲሆን ሐሳቤ በጦርነት ወደማታመሰው ዩክሬን፣ ጋዛ፣ እስራኤል፣ ምያንማር፣ [ሰሜን] ኪቩ እና ሌሎች በብዙ ግጭቶች ውስጥ ለሚገኙ አገራት ሰላም ይሰፍን ዘንድ ጸሎት ማድረጋችንን  መቀጠል ይኖርብናል ብሏል።

የጦርነት አውዳሚ እውነታ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ የጣሊያንን የቴሌቭዥን ፕሮግራም "አ ሱዋ ኢማጂኔ" የተሰኘውን ጣቢያ ዋቢ በማድረግ ጦርነት ያስከተለውን ውድመት የሚያሳዩ ምስሎችንና ፎቶግራፎችን አይተናል ብለዋል።

“ወንድሞች እና እህቶች ጦርነት ያወድማል። ሁልጊዜ ያጠፋል! ጦርነት ሁሌም ሽንፈት ነው። ሁሌም! ሰላም እንዲሰፍን ለሚጥሩ ሁሉ ከልብ አድናቆቴን እገልጻለሁ" ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

ለጣሊያን ፕሬዝዳንት እንኳን ደስ አለዎት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለጣሊያኑ ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ መልካም ምኞታቸውን በመግለጽ "በአዲሱ ዓመት መልካም ነገር ሁሉ እንደሚመጣ" ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ እና ጸሎታቸውን አረጋግጠዋል ። የጣሊያን ፕሬዚዳንት ጆርጆ ማተሬላ እ.አ.አ በ2025 አዲስ አመት ዋዜማ ላይ ለሕዝቡ ባደረጉት የአዲስ ዓመት ንግግር ላይ የ58ኛው የዓለም የሰላም ቀን አስፈላጊነት እና የሁሉንም ኅሊና ጥሪ በመጥቀስ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱን መልእክት አስተጋብተዋል።

"ሁሉም - የሀገር እና የመንግስት መሪዎች፣ የአለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች፣ የሲቪል እና የሃይማኖት ባለስልጣናት - የዓለምን ቁስሎች፣ አስጨናቂውን የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መበታተን እና በአገሮች መካከል እየጨመረ የመጣውን የሰላማዊ ልማት ስጋት ለመፍታት ተጠርተዋል" በማለት ፕሬዚዳንት ጆርጆ ማቴሬላ በዳጋሚ የቅዱስነታቸው ቃል አስተጋብተዋል።

በጣሊያን ሕዝብ ስም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጣይነት ባለው መልኩ ሰላምን ለማስፈን እና እንደ ስደት፣ የአካባቢ ውድመት እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚያስከትሉትን አደጋዎች እና እድሎች ለመፍታት አስቸኳይ እና ደፋር እርምጃዎችን እንደሚወስድ አረጋግጠዋል ፕሬዝዳንት ጆርጆ ማተሬላ።

 

02 January 2025, 14:59