ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ከተቀበሏቸው ማየት ከተሳናቸው መካከል ከአንዲት አዳጊ ሕጻን ጋር ሲነጋገሩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ከተቀበሏቸው ማየት ከተሳናቸው መካከል ከአንዲት አዳጊ ሕጻን ጋር ሲነጋገሩ  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ወጣቶች ዘወትር ወደ ፊት መጓዝን እዳያቆሙ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጣሊያን የዐይነ ስውራን ማኅበር የተወጣጡ ማየት ከተሳናቸው ወጣቶች ጋር በቫቲካን ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ከወጣቶቹ ጋር ተገናኝተው የመንፈሳዊ ንግደትን ትርጉም በማስመልከት ባደረጉት ንግግር፥ ወጣቶቹ እንቅስቃሴያቸውን ሳያቋርጡ ዘወትር ወደ ፊት መጓዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ዓርብ ታኅሳስ 25/2017 ዓ. ም. ጠዋት ከጣሊያ የዐይነ ስውራን ማኅበር ከተወጣጡ ማየት ከተሳናቸው አዳጊ ሕጻናት እና ወጣቶች ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል። ቅዱስነታቸው ወጣቶቹን በቫቲካን ተቀብለው መንፈሳዊ ንግደትን አስመልክተው ባደረጉት አጭር ንግግር፥ ዘወትር ወደ ፊት መጓዝን ማቆም እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

ወደ ፊት መጓዝ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጎርጎሮሳውያኑ 2025 የሚከበረው የኢዮቤልዩ ዓመት ጭብጥ የሆነውን “የተስፋ ነጋዲያን” የሚለውን በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የመንፈሳዊ ንግደት ፅንሰ-ሀሳብ ከጉዞ ጋር በውስጣዊነት የተሳሰረ መሆኑን በመጠቆም፥ ወጣቶቹ እንቅስቃሴያቸውን ሳያቋርጡ ዘወትር በጉዞ ላይ እንዲሆኑ መመኘታቸውን ገልጸዋል።

መድረሻን ማወቅ
መንፈሳዊ ንግደት ወደ ፊት መጓዝ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን መድረሻም ያለው መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ “በዚህ የኢዮቤልዩ ዓመት የምዕመናን መድረሻ ቅዱስ በር ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።“ቅዱስ በር በእርግጥ ምልክት ይሁን እንጂ የመዳን ምሥጢር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚወክል፣ ወደ አዲስ ሕይወት እንድንገባ የሚያስችለን ነው” ብለዋል። ወደ ቅዱስ በር ለመድረስ መጓዝ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን መንፈሳዊ ነጋዲያን በመሆን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያውቁ እና ቃሉን እንዲሰሙ መመኘታቸውን ገልጸዋል።

የተስፋ ነጋዲያን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሕይወታቸውን በዚህ መንገድ ለመምራት የመረጡ የተለያዩ ወጣቶችን፥ ፒየር ጆርጆ ፍሬሳቲን፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስን፣ ቅድስት ክያራን እና የሕፃኑ ኢየሱስ ቅድስት ቴሬዛ ምሳሌን በማቅረብ ንግግራቸውን አጠናቅቀዋል።

“ውድ ጓደኞቼ ሆይ! እነዚህ የተስፋ ነጋዲያን ናቸው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተገናኙ እና ከእርሱ ጋር የተጓዙ ወጣቶች መሆናቸውን በመግለጽ፣ እኛም ፈለጋቸውን በመከተል፥ ለምናገኛቸው በሙሉ ትንሽ የተስፋ ምልክቶች ልንሆን እንችላለን” ብለዋል።

 

04 January 2025, 16:17