ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰብዓዊ ሕግ መከበርን እንዲያረጋግጥ ጥሪ አቀረቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ከአሁን በኋላ ጥያቄያቸው በሰላማዊ መንገድ የሚመለስላቸው እንጂ የሚያምጹ ዜጎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች ወይም መሥሪያ ቤቶች ሊኖሩ አይገባም!” ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጎርጎሮሳውያኑ አዲስ ዓመት 2025 ዓ. ም. የመጀመሪያ እሑድ ካረቀረቡት የመልዓከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀጥለው ባሰሙት ንግግር፥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲያቆም በማለት ጥሪ አቅርበው፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የሰብአዊ ሕግ መከበሩን ለማረጋገጥ የማያወላዳ እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።
ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በተለይ ለዩክሬን፣ ለፍልስጤም፣ ለእስራኤል፣ ለሊባኖስ፣ ለሶርያ፣ ለምያንማር እና ለሱዳን ትኩረት በመስጠት በዓለም ሁሉ ሰላም እንዲሰፍን ምዕመናን ጸሎት እንዲያቀርቡ አደራ ብለዋል።
ቅዱስነታቸው ከዚህ በፊት ያቀረቧቸው ጥሪዎች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የጄኔቫ ስምምነቶች 75ኛ ዓመትን በማስታወስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት 27/2024 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት፥ ለሕዝቦች ሕይወት ክብር እንዲሰጠው፥ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕጎችን በማክበር ለሲቪል መዋቅሮች እና ለአምልኮ ቦታዎች ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
በጦርነት ምክንያት በአንዳንድ ቦታዎች ሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶች እንደሚወድሙ መነገሩን አስታውሰዋል።
ጦርነት ሁሌም ሽንፈት ነው!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ታኅሳስ 27/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ያሰሙትን ንግግር ከማጠቃለላቸው በፊት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ጦርነት መቼም ቢሆን ድልን እንደማያስገኝ በማሳሰብ፥ “ጦርነት ምንጊዜም ሽንፈት መሆኑን አንርሳ!” ሲል ተናግረዋል።