ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የመጋቢት ወር የጸሎት ሃሳባቸውን ይፋ አደረጉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው በወርሃዊ መልዕክታቸው፣ በደል ለተፈጸመባቸው ሰዎች፣ በተለይም በቤተ ክርስቲያን በኩል በደል የተፈጸመባቸውን በማስተወስ፣ ተበዳዮቹ ለተፈጸመባቸው በደል ትክክለኛውን ምላሽ ከራሷ ከቤተ ክርስቲያን ሊያገኙ ይገባል ብለዋል። መልስ ሊሰጣቸው የሚገባው በደሉ የለተፈጸመባቸው ሰዎች በመሆናቸው ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ እና የተከሰተውን አሰቃቂ ሁኔታ ለመጠገን እና እንደገና እንዳይከሰት ለመከላከል ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በመልዕክታቸው አሳስበው፣ ይቅርታ መጠየቅ አስፈላጊ ቢሆንም በቂ እንዳይደለ ተናግረዋል።
ማዳመጥ፣ አብሮ መሆን፣ ከጉዳት መከላከል እና አንድነትን መልሶ መጠገን
ለተፈጸሙት በደሎች በቂ ምላሽ ለመስጠት በደሎችን ወደ ብርሃን ማውጣት፣ ወደ ማኅበረሰቡ እና ወደ ቤተሰብ ዘንድ ማቅረብ ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የተፈጸሙት አሳዛኝ ክስተቶች በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በማንኛውም የተለያዩ ማኅበራዊ ተቋማት ውስጥ ተደብቀው መቆየት እንደሌለባቸው አሳስበዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፣ ቤተ ክርስቲያን የተጎዱትን ማዳመጥ፣ ሥነ-ልቦናዊ ድጋፍ መስጠት እና ጥበቃን ማድረግ መሠረታዊ እንደሆነ ገልጸው፣ አስተማማኝ ቦታን መስጠት እንደሚገባ አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለተበዳዮቹ ያላቸውን ስጋት እና የጥቃት ጉዳዮችን ወደ ብርሃን እንዲገለጥ ያቀረቡትን ጥሪ በቪዲዮ ምስል ያዘጋጀው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት አውታረ መረብ ቅንብር፣ ብርሃንን እና ጨለማን በማነጻጸር፣ ስለ እያንዳንዱ የሰው ልጅ ሕይወት ልዩነት እና በአመፅ ምክንያት ስለሚደርሰው ጥልቅ ስቃይ የሚናገር ኃይለኛ ተምሳሌታዊ ይዘት ያለው ታሪክ እንደሆነ ተመልክቷል።
እያንዳንዱ ሕይወት ምን ያህል የጥበብ ሥራ መሆኑን የሚያመላክቱ አበቦችን የሚያሳዩ እና በብርሃን እጦት ሲጠወልጉ ታይተዋል። ምስሎቹ የተለያዩ ቀለማት ያላቸው፣ አንዳንዶቹ በዝርዝር የተገለጹ፣ ሌሎቹ ደግሞ በሕፃን እጅ የተሳሉ፣ በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የተንጠለጠሉ ናቸው። የልጆች መኝታ ክፍል፣ ስፖርት መሥሪያ ክፍል እና ሳሎን ያለው፣ ሁሉም ክፍሎች፣ አንዳቸውን ከሌላው የሚለያዩ መጋረጃዎች የሚቆጣጠራቸውን ጨለማን የሚጋሩ፣ ብርሃኑ እንዲገባ የሚያስችሉ መሆናቸው ተመልክቷል። የፀሐይ ብርሃን ጨረሮች ቤቱን ለማብራት ብቻ ሳይሆን ወደ ተጎዱ አበቦች ዘልቆ በመግባት ወደ ሕይወት እንዲመለሱ እና እራሳቸውን ለማንሳት እንዲጀምሩ የሚያደርግ መሆኑም በቪዲዮ ምስል ተመልክቷል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ የቅዱስነታቸውን የመጋቢት ወር የጸሎት ሐሳብ መሠረት በማድረግ ባቀረቡት አስተያየት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴ. 18፡6 ላይ ሲናገር፡- “በእኔ ከሚያምኑ ከእነዚህ ታናናሾች አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ውስጥ ቢሰጥም ይሻለዋል።” ተብሎ የተጻፈውን በመጥቀስ፣ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቋቋሙት በማይችሉት ወንጀሎች ፊት መከራ መቀበሉን እንደሚያሳይ ገልጸው፣ ለዚህ ስህተት ምላሽ ማግኘት አስቸጋሪ ነው ብለዋል። “ቤተ ክርስቲያን በምትፈጽመው ጥፋት የሚፈጠሩ ቁስሎችን ይዞ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ በጸሎት መቅረብ መልካም ነው” በማለት የሎዮላው ቅዱስ ኢግናጤዎስ በመንፈሳዊ ልምምዶቹ ቁጥር 319 ላይ የጻፈውን እና ር. ሊ. ጳ. ፍርናንችስኮስም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2018 ዓ. ም. ለእግዚአብሔር ሕዝብ ያስተላለፉትን መልዕክት አባ ፍሬደሪክ አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጋቢት ወር የጸሎት ሃሳባቸው፣ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሥልጣን፣ በሕሊና እና በጾታዊ ጥቃት በደል ለተፈጸመባቸው በሙሉ እንድትጸልይላቸው፣ ይህም ሕሊናችንን እንዲያነቃን፣ የመተሳሰብ ባሕል እንዲኖረን፣ አንድነታችንን እና ቁርጠኝነትን እንዲያሳድግ መፈለጋቸውን አባ ፍሬደሪክ አስታውሰው፣ ጸሎቱ ወደነዚህ ጥቃቶች ባጋጠሙን መዋቅራዊ እና ርዕዮተ ዓለም ምክንያቶች ላይ እንድናሰላስል እና ተመልሰው እንዳይደገሙ ያደርገናል ብለው፣ ጸሎት ልባችንን የሚከፍት፣ እንድንሰማ እና እንድንመለከት የሚያስችለን፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል እና የቤተ ክርስቲያንን ገጽታ በሚያበላሹ ወንጀሎች ላይ እንድንሠራ የሚጋብዝ በመሆኑ፣ የቅዱስነታቸው የጸሎት ሃሳብ እንደሚናገረው፣ የተጎጂዎች ሕመም እና ስቃይ፣ ለጥያቄዎችም ተጨባጭ ምላሽ ለማግኘት የሚያስችለን መሆኑን አስገንዝበዋል።