ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ አቶ ፑቲን ጦርነትን እንዲያቆሙ እና አቶ ዘሌንስኪም የሰላም ዕድሎችን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ መስከረም 22/2015 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባሰሙት ንግግር በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት አስታውሰው፣ የሩሲያው ፕሬዚደንት ቪላድሚር ፑቲን እና የዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ የሰላም ዕድሎችን ተጠቅመው ጦርነትን እንዲያበቁ በመማጸን የሰላም ጥሪያቸውን በድጋሚ አቅርበዋል። ክቡራት እና ክቡራን፣ ከዚህ ቀጥሎ ቅዱስነታቸው መስከረም 22/2015 ዓ. ም. ያደረጉትን ንግግር ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዩክሬን እየተካሄደ ያለው አውዳሚ ጦርነት ከፍተኛ ጭንቀትን ሊያስከትል ስለሚችል አሳሳቢ ሆኗል። ይህ በመሆኑ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካማቅረባችን በፊት የዛሬውን አስተንትኖን በዚህ ጉዳይ ላይ ለማድረግ እወዳለሁ። በእርግጥም ይህ በሰው ልጅ ላይ እየደረሰ ያለው አስከፊ እና የማይታሰብ ቁስል ከመፈወስ ይልቅ እየተስፋፋ ሄዶ የበለጠ ደም ማፍሰሱን ቀጥሏል። 

በዩክሬን እየተካሄ ባለው ጦርነት ምክንያት በእነዚህ ወራት ውስጥ እንደ ወንዝ የፈሰሰው የሰው ልጅ ደም እና እንባ እጅግ አሳዝኖኛል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በተለይም ሕጻናት የጦርነቱ ሰለባ በመሆናቸው፣ በርካታ ቤተሰቦችን ቤት አልባ ማድረጉ እና ውድመቶችን ማስከተሉ እንዲሁም ሰፊ የዩክሬን ግዛቶችን በብርድ እና በረሃብ ስጋት ላይ መጣሉ አሳዝኖኛል። በዚህ ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ አንዳንድ አስከፊ ድርጊቶች ፈጽሞ ተቀባይነት ሊኖራቸው አይችልም! የሰው ልጅ እንደገና ለአቶሚክ የጦር መሣሪያ ስጋት የመጋለጡ እውነታ ያሳዝናል።

ከዚህ ቀጥሎ ምንድነው የሚሆነው? ጦርነት መቼም ቢሆን ጥፋት እንጂ መፍትሄ አለ መሆኑን ለመገንዘብ ከዚህ በኋላ ምን ያህል ደም መፍሰስ አለበት? በእግዚአብሔር ስም እና በሁሉም የሰው ልጅ ልብ ውስጥ ባለው ምኞት ስም፣ ፈጣን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪዬን በድጋሚ አቀርባለሁ። የጦርነት ትጥቅ ይፈታ፤ በኃይል ሳይሆን በመግባባት፣ ፍትሃዊ እና የተረጋጋ መፍትሄ የሚያመጡ የድርድር መንገዶችን እንፈልግ። ይህ ሊሆን የሚችለው፣ የሰው ልጅ ሕይወት ቅዱስ እሴት፣ የእያንዳንዱን አገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እና የአናሳ ብሔረሰቦች መብት ሲከበር ነው።

በቅርብ ቀናት ውስጥ የተፈጠረውን አስከፊ ሁኔታ እና ዓለም አቀፍ ሕግ መርሆችን የሚቃረኑ ተጨማሪ ድርጊቶችን በጥብቅ እቃወማለሁ። ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የኒውክሌር መሣሪያ ስጋት ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ የሚያስከትለው አስከፊ መዘዝ በዓለም ዙሪያ ፍርሃትን ፈጥሯል።

ለወገኖቻቸው እና ለገዛ ሕዝባቸው ሲሉ ይህን የአመፅና የሞት ሽረት ፊልሚያ እንዲያቆሙ በመማጸን በቅድሚያ ለሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ቪላድሚር ፑቲን ጥሪዬን አቀርባለሁ። በሌላ በኩል በዩክሬን ሕዝብ ላይ በደረሰው ግፍ እና መጠነ ሰፊ ስቃይ የተሰማኝን ሐዘን በመግለጽ፣ የዩክሬን ፕሬዝዳንት አቶ ቮሎድሚር ዘሌንስኪ የሚቀርቡላቸውን የሰላም ሀሳቦች ለመቀበል ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪዬን አቀርባለሁ። ሁኔታዎች ተባብሰው ወደ አደገኛ ደረጃ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ጦርነቱ እንዲቆም፣ ዓለም አቀፍ ዋና ተዋናዮች እና የሀገራት መሪዎች የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ፣ የውይይት ጥረቶችን እንዲያበረታቱ እና እንዲደግፉ እጠይቃለሁ። ወጣቱ ትውልድ የሰላም አየር እንጂ የተበከለውን የጦርነት አየር መተንፈስ የለበትም!

ከሰባት ወራት ጦርነት በኋላ፣ ይህንን አስከፊ አደጋ ለማስወገድ፣ ምናልባት እስካሁን ያልተጠቀምናቸው መንገዶችም ካሉ ተመልክተን፣ ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች እንጠቀም። ጦርነት በራሱ ስህተት እና አስፈሪ ነው!

ልብን መለወጥ በሚችል በእግዚአብሔር ምሕረት እንታመን፤ ከብዙ የዓለም ክፍሎች ወደ ፖምፔይ የመቁጠሪያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ለጸሎት ከተሰበሰቡ ምእመናን ጋር በመንፈስ በመተባበር እኛም ወደ ሰላም ንግሥት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ልመናችንን እናቅርብ።”

03 October 2022, 17:15