“ወንጌልን በቀስታ ወይም በሹክሹክታ ማብሰር” የኢስያ ጸጥ ያለ ምስክርነት መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ክሌደን ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በቅርቡ በጃካርታ በተካሄደው የኢስያ ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን (FABC) 12ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢንዴ ሊቀ ጳጳስ እና የኢንዶኔዥያ ጳጳሳት ጉባኤ (KWI) ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ክሌደን፣ ስብሰባው ተሳታፊዎች በመላው ኢስያ በሚገኙ የተለያዩ የቤተክርስቲያኗ ሁኔታዎች ውስጥ እግዚአብሔር ቀድሞውኑ እየሠራ መሆኑን እንዲገነዘቡ እንዳገዛቸው ገልጸው፥ “እያንዳንዱ እውነተኛ ግንኙነት ታላላቅ ነገሮችን ለመለማመድ የሚያስችል አጋጣሚ መሆኑን ጉባኤው በድጋሚ ግልጽ አድርጎታል” ሲሉ በቃለ መጠይቃቸው ወቅት ገልጸዋል።
ከተለያዩ የኢስያ ሃገራት የመጡ ተሳታፊዎችን ማዳመጥ “ልብን የሚያሞቅ እና የአስተሳሰብ አድማስን የሚያሰፋ” እንደነበር የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፣ ከዚህም ባሻገር የጉባኤው ተሳታፊዎች የካቶሊካዊያን ቁጥር አብዛኛውን ጊዜ አነስተኛ በሆነባቸው የአከባቢ አቢያተ ክርስቲያናት ውስጥ የእግዚአብሔርን መገኘት እንዲገነዘቡ መርዳቱን አስታውሰዋል።
“አናሳ ቡድን መሆን ተስፋ ለመቁረጥ እና እጅ ለመስጠት ምክንያት አይደለም” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፣ ይልቁንም “ምስክርነት ለመስጠት እና የወንጌልን እሴቶች በተግባር ለማዋል የሚያስችሉ ትሑትና ቀላል መንገዶችን በፈጠራ ለማግኘት የሚያስችል አጋጣሚ ነው” ያሉ ሲሆን፥ ለእርሳቸው ይህ በኢስያ ውስጥ ለሚገኘው የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ልዩ የሆነ ገጽታን እንደሚያሳይ ጠቅሰው፥ “በኢስያ ውስጥ ወንጌልን በሹክሹክታ ስለማድረስ እናወራለን” ካሉ በኋላ፥ የወንጌል መንገድ የትሕትና መንገድ መሆኑን እንደገና መገንዘብ ለእሳቸው በጉባኤው ወቅት ከተከናወኑት ‘ታላላቅ ነገሮች’ አንዱ እንደነበር እና ይህንን ጸጥ ያለ ምስክርነት ከደካማነት የመነጨ ስልት አድርገው ሳይሆን፣ የኢስያ አብያተ ክርስቲያናት ለዓለም አቀፏ ቤተክርስቲያን ሊያበረክቱት የሚችሉት አስተዋጽዖ አድርገው እንደሚመለከቱት አስረድተዋል።
ሲኖዶሳዊ አመራርን የሚረዱ አራት ዓይነት ለውጦች
የጉባኤው የመጨረሻ መልዕክት፣ ሲኖዶሳዊነት ወይም አብሮ የመጓዝ መንፈስ የአሰራር መዋቅሮችን ከመለወጡ በፊት ልቦችን እንደሚለውጥ አጽንዖት የሰጠ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳስ ክሌደን ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት ይህ የቤተክርስቲያን መሪዎች ከሚያዳምጡበት መንገድ ጀምሮ ተጨባጭ የሆነ የልብ ለውጥን እንደሚጠይቅ ጠቁመው፥ “በመጀመሪያ ደረጃ አዳማጭ መሪ ለመሆን ከልብ የሚደረግ ለውጥ ያስፈልጋል” ያሉ ሲሆን፥ እንዲህ ዓይነቱ ማዳመጥ በካቶሊካዊያን ብቻ የተገደበ ሳይሆን የሌላ ሃይማኖት ተከታዮችን፣ የተፈጥሮ ዓለምን እንዲሁም ሴቶችን፣ ህጻናትን፣ ወጣቶችን እና ድሆችን ጨምሮ አብዛኛውን ጊዜ ችላ የተባሉትን ሰዎች ማካተት እንዳለበት አመላክተዋል።
ማዳመጥ ጳጳሳዊ ስልጣንን እንደማይቀንስ በአጽንዖት የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ ከዚህም ይልቅ ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ጠቁመው፥ ምክንያቱም መሪዎች ስልጣንን "የበላይነትን የመጫን ኃይል" አድርገው ሳይሆን፣ የማገልገል ጥሪ መሆኑን፣ እንዲሁም የግንኙነት ድልድይ ገንቢዎች የመሆን ጥሪ አድርገው እንዲረዱት ያስችላቸዋል ብለዋል።
ሁለተኛው ለውጥ ወደ ባህላዊ መስተጋብር የሚደረግ ሽግግር እንደሆነ ያመላከቱት ሊቀ ጳጳስ ክሌደን፥ እጅግ ሰፊ የሆነ የባህል እና የሃይማኖት ልዩነት ባለበት አህጉር ውስጥ፣ የቤተክርስቲያን መሪዎች ሌሎችን በሚመለከቱበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩትን አድልዎ ወይም የተሳሳቱ አመለካከቶች የበለጠ ሊገነዘቡ እንደሚገባ ጠቁመው፥ "ብዙውን ጊዜ፣ በባህላዊ አድልዎ ምክንያት እግዚያብሔር በሌሎች ውስጥ እና በሌሎች በኩል የሚያከናውናቸውን ታላላቅ ነገሮች ማየት አንችልም" ሲሉ አስረድተዋል።
ሊቀ ጳጳስ ክሌደን ሦስተኛው ነጥብ ወደ ቅዱስ ቁርባናዊ መንፈሳዊነት የሚደረግ ሽግግር መሆኑን ገልጸው፥ ለጉባኤው በቀረበውና ‘ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቅዱስ ቁርባን ስጦታ በሚመነጨው ፍቅር ላይ የተመሠረተ የቤተክርስቲያን አንድነት መንፈሳዊነትን’ በሚጠይቀው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መልዕክት ላይ በመመስረት፣ ቅዱስ ቁርባን የቤተክርስቲያን መሪዎችን ጥሪያቸው የራሳቸው እንዳልሆነ እንደሚያስታውሳቸው ተናግረዋል።
ቤተክርስቲያን በመጀመሪያ ደረጃ በጳጳሳት ላይ የተመሰረተች እንዳልሆነች እና የእነሱ የግል ንብረት እንዳልሆነች ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፤ ከዚህም ይልቅ ቤተ ክርስቲያን የእግዚያብሔር ቤት እንደሆነ አመላክተው፥ ስለዚህም አመራር ማለት በክርስቶስ ራስን አሳልፎ በሚሰጥ ፍቅር እና ለቤተክርስቲያን በሚደረግ አገልግሎት ውስጥ መሳተፍ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።
አራተኛው የመለወጥ እርምጃ ምናልባትም ቀላል የሚመስለው ‘ምስጋና’ እንደሆነ የጠቆሙት ሊቀ ጳጳሱ፥ ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም እንኳ ለቤተክርስቲያን በአደራ የተሰጡትን ምዕመናን በማሰብ ቤተክርስቲያን ምስጋናን እንድታቀርብ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ በአብዛኛው የኢስያ ክፍሎች ክርስቲያኖች እና ካቶሊኮች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው በመሆናቸው ቤተክርስቲያንን ተስፋ ወደማጣት ሊመራት እንደማይገባ አሳስበው፥ ይልቁንም እምነት የተመሠረተው፣ ሰዎችን ወደ እርሱ ለማቅረብ የራሱ የሆኑ መንገዶች ባሉት በእግዚአብሔር ላይ ባለው መተማመን ላይ ነው ብለዋል።
በለውጥ ላይ ባለችው ኢስያ ውስጥ ድልድዮችን መገንባት
በኢስያ ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን ጉባኤ ወቅት ቤተክርስቲያን እንደ ድልድይ ገንቢ የምትታይበት ምስል በተደጋጋሚ የተነሳ ቢሆንም፥ ሆኖም ግን የግንኙነት ድልድይ የመገንባት ሥራ በሃይማኖት ተቋማት መካከል ከሚደረግ ውይይት እጅግ የዘለለ መሆን እንዳለበት የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ክሌደን፥ በቤተክርስቲያን ውስጥ፣ በተለይም ከፍተኛ የወጣት ቁጥር ባለው አህጉር ውስጥ፣ ከወጣቶች ጋር ድልድይ የመገንባት አስፈላጊነትን ጠቁመው፥ ከዚህም ባሻገር የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ሃገራቸውን ለቀው ወደ ተለያዩ ሃገራት የሚሻገሩ ስደተኞችን ጉዳይ አንስተው፣ ቤተክርስቲያን በራሷ ማህበረሰቦች ውስጥ ባሉ የተለያዩ የባህል ቡድኖች መካከልም ድልድዮችን መገንባት እንዳለባት አሳስበው፥ ከቤተክርስቲያን ውጭ ደግሞ በጎ ፈቃድ ካላቸው ሰዎች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ፣ ከመንግስታት እና ከፍጥረት ጋር ድልድዮችን የመገንባት አስፈላጊነትን አጽንዖት በመስጠት ተናግረዋል።
የኢስያ ማህበረሰቦች ከሚያጋጥሟቸው በርካታ ተግዳሮቶች መካከል በተለይ አጣዳፊው ነገር የሥነ-ምህዳራዊ ቀውስ እንደሆነ ያመላከቱት ሊቀ ጳጳሱ፥ ምንም እንኳን በርካታ ተግዳሮቶች በኢስያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም፣ ከሁሉም የሚልቀው ግን የሥነ-ምህዳራዊ ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሰው፥ በርካታ የኢስያ ሃገራት የኢኮኖሚ ልማትን እያከናወኑ ቢሆንም፥ ነገር ግን ከባቢ አየርን በከፍተኛ ሁኔታ በሚጎዳ መልኩ የተፈጥሮ ሀብቶችን እያባከኑ እንደሆነ አሳስበው፥ በተለይም የደን መጨፍጨፍን፣ የመሬት ወረራን እና ‘ለተፈጥሮ በሚኖራቸው ውጤት ላይ ብዙም ትኩረት ሳይሰጥ’ የሚከናወኑ የማዕድን ማውጣት ሥራዎችን ጠቅሰዋል።
ተልዕኮ በመጀመሪያ ደረጃ የእግዚአብሔር ነውሊቀ ጳጳስ ክሌደን በኢስያ የምትገኘው ቤተክርስቲያን ትልቁ ራዕይ፣ ተልዕኮ ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር ተልዕኮ እንደሆነ ጥልቅ እምነት ያለው ‘ሚሲዮ ዴይ’ ወይም «የእግዚአብሔር ተልዕኮ» በሚለው ጽንሰ-ሀሳብ ላይ የተመሠረተ ሚስዮናዊ መንፈሳዊነት ላይ እንደሆነ ገልጸው፥ “እግዚአብሔር ወደ ሰዎች ልብ ለመድረስ፣ ባህሎችን ለመቅረጽ እና ሃይማኖቶችን ለማነሳሳት የራሱ የሆነ መንገድ እንዳለው” ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ጋር ድልድዮችን በመገንባት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፣ ክርስቲያኖችም በዚያ ሥራ ውስጥ እንደ "ድልድዮች እና ድልድይ ገንቢዎች" ሆነው እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ ይህ የጸና እምነት የተስፋ መሰረትም ጭምር እንደሆነ አስረድተው፥ በኢስያ የምትገኘው ቤተክርስቲያን የወደፊት ተስፋ የሚኖራት ተልዕኮው የእግዚአብሔር ተልዕኮ ስለሆነ ብቻ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ ይህ አመለካከት በኢንዶኔዥያ ቤተክርስቲያን እና በሰፊው የኢስያ ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን ቤተሰብ ውስጥ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ስለ አመራር ያላቸውን ግንዛቤ ጭምር እንደሚቀርጽ ገልጸዋል።
ለእርሳቸው የሚያዳምጥ፣ የተለያዩ ድምጾችን የሚቀበል እና ኃላፊነትን ለመጋራት የማይፈራው "ሲኖዶሳዊ አመራር" የሁሉም መልስ እንደሆነ ያላቸውን እምነት የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፥ ‘ስልጣንን እናጣለን ብለን መፍራት እንደማይገባ፤ ይልቁንም በርካታ ሰዎችን በአመራር ውስጥ እንዲሳተፉ መጋበዝ እና ማበረታታት እንደሚገባ ያመላከቱ ሲሆን፥ "የቤተክርስቲያኗ የወደፊት እጣ ፈንታ ስያሜ 'አብሮ መጓዝ' እና 'ኃላፊነትን መጋራት' የሚለው እንደሆነ ጠቁመዋል።
"የግንኙነት ድልድዮች እና ድልድይ ገንቢዎች ሁኑ"
የኢስያ ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን ጉባኤ ሲጠናቀቅ፣ ከመላው ኢስያ የመጡት ካቶሊካዊያን ከጉባኤው ምን ዓይነት መልዕክት ይዘው እንደሚሄዱ የተጠየቁት ሊቀ ጳጳስ ክሌደን፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ እንዳደረገው ሁሉ፣ እናንተም ድልድዮች እና ድልድይ ገንቢዎች ለመሆን ድፍረት ይኑራችሁ” በማለት ምናልባትም በኢስያ ውስጥ ስላለው የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ያላቸውን አስተሳሰብ ዋና ይዘት የሚያንፀባርቅ መልስ መልሰዋል።
ካቶሊኮች ብዙውን ጊዜ እንደ አናሳ ቡድን በሚኖሩበት አህጉር፣ የወንጌል ስርጭት የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በከፍተኛ ድምፅ በመናገር ላይ ሳይሆን በጥልቀት ማዳመጥን፣ በትህትና መጓዝን እና በትዕግስት መገንባትን በመማር ላይ ሊሆን እንደሚችል የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ክሌደን፥ በኢስያ የምትገኘው ቤተክርስቲያን የምታያሳየው ጸጥ ያለ ምስክርነት፣ ማለትም “ወንጌልን በሹክሹክታ ማድረስ” የተልዕኮ ጥንካሬ የሚገኝበት ቦታ እንደሆነ በማመላከት አጠቃለዋል።