የቬትናም ካቶሊካዊያን ወደ ላ ቫንግ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ቤተ መቅደስ መንፈሳዊ ንግደት ማድረጋቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ይሄንን መንፈሳዊ ንግደት ተከትሎ የፓሪስ የውጭ ተልዕኮ ማህበር አባል እና ቬትናማዊ ካህን የሆኑት አባ ላንድሪ ቫረን የእመቤታችን ፍልሰታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚደረጉትን አስደናቂ መንፈሳዊ ንግደቶች በመጥቀስ፣ “ላ ቫንግ በቬትናም ውስጥ በፈረንሳይ እንደሚገኘው ሉርድ ማሪያም ሁሉ ቅዱስ ስፍራ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ከነሃሴ 7 እስከ 9 ባለው ጊዜ ውስጥ በቬትናም የሁዌ ሃዋሪያዊ አስተዳደር ስር የሚገኘው የላ ቫንግ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ብሔራዊ ቤተ መቅደስ መጽናናትን ለማግኘት እንዲሁም እውነተኛ ደቀ መዛሙርት እና ሚስዮናውያን መሆንን ለመማር “ጉዞ ወደ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤት” በሚል መሪ ቃል ታላቅ መንፈሳዊ በዓል ማሰናዳቱ ተነግሯል።
“ይህ ቅዱስ ስፍራ ባለው ታሪካዊ እና ባህላዊ ምክንያቶች የተነሳ ለላ ቫንግ እመቤታችን ማሪያም ልዩ የሆነ አክብሮት እና ፍቅር ባላቸው የቬትናም ሕዝቦች እምነት ማዕከል ላይ ይገኛል” ያሉት አባ ቫረን፥ ይህ ቤተ መቅደስ ፈረንሳይ ውስጥ እንደሚገኘው ታዋቂው ሉርድ ማሪያም ቤተ ክርስቲያን ሁሉ በቬትናምም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቅዱስ ስፍራ እንደሆነ አስረድተዋል።
የፓሪስ የውጭ ሃገራት ተልዕኮ ማህበር አባል እና ቬትናማዊ ካህን የሆኑት አባ ላንድሪ ቫረን ይህንን የተናገሩት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ፍልሰታ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሚደረጉ ታላላቅ መንፈሳዊ ንግደቶች ላይ በመመስረት ሲሆን፥ መንፈሳዊ ንግደቶቹ ከሰሜን፣ ከደቡብ እና ከመካከለኛው ቬትናም እንዲሁም በውጭ አገር ከሚኖሩ የቬትናም ማህበረሰቦች የተወጣጡ መሆናቸው እና በአካባቢው ቤተክርስቲያን ግምት መሰረት፣ በዚህ ዓመት የተሳታፊዎቹ ቁጥር ከ200,000 በላይ እንደነበር ተገልጿል።
ለቬትናም ሕዝብ የሚሆን ምሳሌ
“እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እ.አ.አ. በ 1789 ዓ.ም. ለቀድሞ አባቶቻችን ፈጽሞ እንደማትተወን የነገረቻቸውን ቃል ሁሉም ሰው ያምናል” በማለት የህዝቡን ጠንካራ እምነት የገለጹት አባ ፍራንሲስ በበኩላቸው፥ “እናታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ለሀገሪቱ፣ በቬትናም ለምትገኘው ቤተክርስቲያን እና ለሰላም የምናቀርበውን ጸሎት እንደምትሰማ እናምናለን” ብለዋል።
ካህኑ አክለውም ህዝቡ ለእግዚአብሔር ያለው መሰጠት በመስዋዕተ ቅዳሴ፣ በእርቅ ወይም በንስሃ ምስጢራት፣ በመስቀል መንገድ ስግደት እና በምሕረት ጸሎት ሰዓታትን በመሳሰሉ ተግባራት አማካኝነት እንደሚገለጽ ጠቁመው፥ “ምዕመናኑ በቅድስት ድንግል ማሪያም ልብ ውስጥ እና በመጎናጸፊያዋ ጥላ ስር እንዳሉ ይሰማቸዋል፤ እሷም መጠጊያቸው ናት” ያሉ ሲሆን፥ የዘንድሮው ጉባኤ በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ከሰጠበት ጉዳይ ውስጥ የሚስዮናዊነት ወይም የስብከተ ወንጌል ጉዳይ ዋናው መሆኑን ጠቁመው፥ “ሰዎች የማርያምን ምሳሌ በመከተል፣ እግዚያብሔርን እና ለልጆቹ ያለውን ፍቅር ለሌሎች ማድረስን ይማራሉ” ሲሉ አስገንዝበዋል።
የአምልኮው መነሻ
በላ ቫንግ የሚደረገው አምልኮ መነሻው እ.አ.አ. በ 1798 ዓ.ም. በቬትናም ታሪክ ውስጥ ክርስቲያኖች እጅግ ከፍተኛ ስደት የደረሰባቸው ወቅት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፥ በወቅቱ የነበሩት የሃገሪቱ ንጉሠ ነገሥት ካን ቲን ካቶሊኮች የ«ባዕድ ሃይማኖት» ተከታዮች ናቸው በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ አብያተ ክርስቲያናት እንዲወድሙና ምዕመናኑ እንዲሰደዱ ማዘዛቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ይሄንንም ተከትሎ አብዛኛዎቹ ካቶሊካዊያን ለስደት በመዳረግ በማዕከላዊ ቬትናም የኩንግ ትሪ ግዛት ውስጥ በሚገኘው የላ ቫንግ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ እንደተጠለሉ፣ እዚያም በነበሩበት ወቅት ከፍተኛ ለሆነ ረሃብ፣ ህመምና ብርድ ተጋልጠው መቆየታቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
እነዚህ ካቶሊካዊያን ስደተኞች በየምሽቱ በትላልቆቹ የባንያን ዛፎች ስር ይሰበሰቡ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፥ እዚያም እሳት በማቀጣጠል የመቁጠሪያ ጸሎት ያደርጉ እንደነበር፥ ከእነዚህ የምሽት ጸሎቶች መካከል በአንዱ ወቅት፣ በብርሃን የተከበበች፣ ባህላዊ የቬትናም ልብስ የለበሰች፣ ህፃን ልጅ በእቅፏ የያዘች እና በሁለት መላዕክት የታጀበች ሴት እንደተገለጠችላቸው ታሪካቸው ይገልጻል።
በመላዕክት የታጀበችው ‘ሴት’ በተገለጠችበት ወቅት “ልጆቼ ሆይ፣ ጠንካራ ሁኑ፤ እምነትም ይኑራችሁ፣ ጸሎታችሁንም ሰምቻለሁ” በማለት ከሁሉም በላይ የማጽናኛ መልዕክት ያስተላለፈች ሲሆን፥ በዚህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በትክክል የአንዲት ቬትናማዊት ሴት ገጽታና አለባበስ ይዛ መገለጧ ትልቅ ትርጉም እንዳለው እና በአካባቢው ቤተ ክርስቲያን በስፋት የተሰራጨውና በተለይም ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጀምሮ ጎልቶ የወጣው ይህ ምስል በእምነት እና በማንነት መካከል ያለውን ጥልቅ ግንኙነት ያሳያል ተብሏል።
በአከባቢው የነበሩ ካቶሊካዊያን የ«ባዕድ ሃይማኖት» ተከታዮች ናቸው ተብለው ለዘመናት ሲከሰሱ ከቆዩ በኋላ፥ ‘ላ ቫንግ ሙሉ በሙሉ ካቶሊክ እና በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ቬትናማዊ መሆን እንደሚቻል ይመሰክራል’ በማለት የአሁኑ ዘመን ብፁዓን ጳጳሳት ማረጋገጣቸው ተገልጿል።
ሕያው ትዝታ የሆነ እምነት
ከሁሉም በላይ፣ ይህ የልጆቿን መከራ የምትጋራ እናት ምስል መሆኑ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለስደት እና ለበሽታ የተጋለጡ፣ እንዲሁም ጥበቃ ለሌላቸው ስደተኞች እንደምትገለጥ የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት የላ ቫንግ እመቤታችን ቅድስት ማሪያም ቤተመቅደስ "የመሸሸጊያ እናት" መባሉ እና እርሷም በጦርነት፣ በወረራ እና በስደት ለተጎዱ ሰዎች ቁስል ማስታገሻ መሆኗ ተነግሯል።
እስካሁን ድረስም ምዕመናን ይህንን ትዝታ በሕይወት ለማቆየት እንደሚጥሩ እና ለዚህም ማሳያ በመንፈሳዊ ንግደቱ ወቅት በባንያን ዛፎች ጥላ ስር በድንኳን እንደሚያድሩ፣ የመቁጠሪያ ጸሎት እንደሚያደርጉ፣ እንዲሁም በክብረ በዓሉ ወቅት በ 1798 ዓ.ም. የነበረውን የስደት ሁኔታ እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን መገለጥን የሚያሳይ ተውኔት እንደሚቀርቡ የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህም መንገድ፣ ይህ መንፈሳዊ አምልኮ የእምነትን ታሪክ ከአካባቢው ማህበረሰቦች ተጨባጭ ሕይወት ጋር የሚያገናኝ ሕያው ትዝታ ይሆናል ተብሏል።