ፈልግ

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የአሜሪካ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ጽህፈት ቤት  በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የአሜሪካ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ጽህፈት ቤት  

የአሜሪካ ብፁዓን ጳጳሳት የፅንስ ማስወረድ ክኒኖችን ስርጭት ለመከላከል የጸሎት እና የድርጊት ተነሳሽነት መጀመራቸው ተነገረ

በአሜሪካ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ የሕይወት ጥበቃ እንቅስቃሴዎች ኮሚቴ ሁሉም ካቶሊካውያን የፅንስ ማስወረድ ክኒኖች ስርጭት እንዲቆምና እርምጃ እንዲወሰድ መጸለይ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በአሜሪካ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ የሕይወት ጥበቃ እንቅስቃሴዎች ኮሚቴ በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ካቶሊካዊያን የፅንስ ማስወረድ ክኒኖችን ስርጭት ለመከላከል ከነሃሴ 12 ጀምሮ እስከ ጥቅምት ድረስ የሚቆይ የፅንስ ማስወረድ ክኒኖች መስፋፋትን ለመግታት በሚደረግ የተቀናጀ የጸሎትና የተግባር እንቅስቃሴ ላይ እንዲሳተፉ ግብዣ ማድረጋቸው ተነግሯል።

የአሜሪካ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት ፖል ኮክሌይ እና በጉባኤ የሕይወት ጥበቃ እንቅስቃሴዎች ኮሚቴ ሊቀ መንበር የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ቶማስ ነሃሴ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. በጋራ ባወጡት መግለጫ “እያንዳንዱ የፅንስ ማስወረድ ተግባር የአንድ ህፃን ሞትን እና የእናት መጎዳትን የሚያስከትል እርምጃ ነው” ያሉ ሲሆን፥ ብፁዓን ጳጳሳቱ አክለውም በአሁኑ ወቅት የፅንስ ማስወረድ ክኒኖችን በቀላሉ ማግኘት በመቻሉ የፅንስ ማስወረድ መጠኑ በሚያሳዝን ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን እና የጤና አደጋዎችም በዚያው ልክ መጨመራቸውን ገልጸዋል።

ለካቶሊካዊያን የተደረገው ይህ ጥሪ የሕይወት ጠባቂ ለሆነው ለቅዱስ ዮሴፍ አማላጅነት የሚቀርብ በእንግሊዝኛ እና በስፓኒሽ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ጸሎትን ያካተተ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም ካቶሊካዊያን ስለ ፅንስ ማስወረድ ክኒኖች አደጋ ግንዛቤ የሚያገኙበት እና በዚህ ሂደት ውስጥ ለሚሳተፉ ፋርማሲዎችና የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች መልዕክት መላክ የሚችሉበት እንዲሁም ለህይወት ክብር የመስጠት ጸሎት እና ለተግባራዊ እርምጃ የተዘጋጀውን የአሜሪካ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤን ድህረ-ገጽ እንዲጎበኙ ማበረታታቸው ትመላክቷል።

ይህ ተነሳሽነት የተጀመረው በዩናይትድ ስቴትስ በምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ‘ህይወትን የማክበር ወር’ በሚል ጭብጥ ጥቅምት ወር ላይ ከሚከበረው በዓል ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ የተጀመረ መሆኑም ጭምር ተነግሯል።

ሴቶችን ለአደጋ የሚያጋልጥ ስርዓት
ብፁዓን ጳጳሳቱ ከዚህም ባሻገር የሃገሪቱ የምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር (FDA) የፅንስ ማስወረድ መድኃኒቶች በርቀት የህክምና ምክክር ወይም ‘ቴሌ ሄልዝ’ አማካኝነት እንዲታዘዙ በማድረግ እና በአካባቢው በሚገኙ ፋርማሲዎችም ሆነ በኦንላይን ገበያዎች እንዲሸጡ በመፍቀድ በመላ ሀገሪቱ በፖስታ የሚላኩ የፅንስ ማስወረድ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ ማድረጉን ጠቅሰው፥ በዚህም አካሄድ በማህፀን ውስጥ ለሚገኝ ህይወት ጥበቃ የሚያደርጉትን የክልል ህጎች እየጣሱ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

“ይህ አካሄድ ሴቶች ያለ ምንም የህክምና ክትትል በቤት ውስጥ ብቻቸውን ፅንስ ሲያስወርዱ ለከፍተኛ ስቃይ እንዲጋለጡ ያደርጋል” ያሉት ብፁዓን ጳጳሳቱ፥ ከዚህም ባሻገር በዓመጽ ባህሪ በሚታወቁ አጋሮች እና ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ለሚፈጸም ብዝበዛ ተጨማሪ ዕድሎችን ይፈጥራል ብለዋል።

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግንቦት ወር ላይ ይሄንን አስመልክቶ በዝቅተኛ ፍርድ ቤት ህጋዊ ክርክር እየተካሄደ ባለበት ወቅት የእርግዝና ማቋረጫ ክኒኖች ‘በቴሌሜዲሲን’ ወይም በርቀት የህክምና አገልግሎት አማካኝነት እንዲታዘዙ እና በፖስታ እንዲላኩ በጊዜያዊነት የሚፈቅደውን ትዕዛዝ ማራዘሙ የሚታወስ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር የአሜሪካ የፌዴራል የህዝብ ጤና ኤጀንሲ የሆነው የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ሪፖርት መሠረት በአሜሪካ ከሚከናወኑት የእርግዝና ማቋረጥ ሂደቶች መካከል 58 በመቶ የሚሆኑት በመድኃኒት የተከናወኑ መሆናቸውን ያመላክታል።

21 Aug 2026, 14:46