የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት የመጀመሪያ የዝግጅት ጉባኤ የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት የመጀመሪያ የዝግጅት ጉባኤ  

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት የመጀመሪያ የዝግጅት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት (SECAM) “በአፍሪካ የምትገኘው ሲኖዶሳዊት ቤተክርስቲያን፡ እ.አ.አ. በ2028 ዓ.ም. ወደሚካሄደው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ የአብሮነት ጉዞ” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የመጀመሪያ የዝግጅት አህጉራዊ ጉባኤ በኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ አዲስ አበባ ከሃምሌ 28 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፥ በዚህ ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይን ጨምሮ፣ የአፍሪካ እና የማደጋስካር ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ፕረዚዳንት ብፁዕ ካርዲናል ፍሮዶሊን አምቦንጎ፣ የሴካም ዋና ጸሃፊ ክቡር አባ ራፋኤል ፣ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ እና ብፁዓን ጳጳሳት፣ ካህናት እና ገዳማዊያት ተገኝተዋል።

  አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤዎች ጽህፈት ቤት የተሰናዳው የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ በሚገኘው ፍሬንድ ሺፕ ሆቴል የስብሰባ ማዕከል ውስጥ እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከዚህን በፊት የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ. ም. የአፍሪካና የማዳጋስካር ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ጉባኤን በአዲስ አበባ ማዘጋጀቷ ይታወሳል።

“በአፍሪካ የምትገኘው ሲኖዶሳዊ ቤተክርስቲያን፡ እ.አ.አ. በ 2028 ዓ.ም. ወደሚካሄደው የቤተክርስቲያን ጉባኤ የሚደረግ የአብሮነት ጉዞ” በሚል ጭብጥ በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው ጉባኤ ሃምሌ 28 ቀን 2018 ዓ.ም. በፍሬንድ ሺፕ ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በተካሄደ መስዋዕተ ቅዳሴ የተጀመረ ሲሆን፥ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው ይህ አህጉራዊ ጉባኤ ሃምሌ 29 በሚደረግ የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አብሮ የመጓዝ ሲኖዶስ ተጠናቅቆ የመጨረሻው ሰነድ ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ተግባራዊነቱን መመዘን ላይ ያተኮረ ጉባኤ እንዲጀመር በቅድስት መንበር አቅጣጫ መቀመጡ የሚታወቅ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት በቅድስት መንበር የሲኖዶስ ጽህፈት ቤት በሀገረ ስብከቶች፣ በቀጠናዎች፣ በአህጉራት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረገው ውይይት የተግባራዊነቱ ምዘና በጽሁፍ በሚቀርብ ሪፖርት ብቻ ሳይሆን ለውጡ በቤተክርስቲያን የሐዋርያዊ አገልግሎት ህይወት ያመጣውን ልዩነት በመንፈሳዊነት በማስተዋል በህብረት እንዲሁም በትህትና የሚገመገም ሊሆን እንደሚገባው ተገልጿል።

ሲኖዶሳዊ የትግበራ ሂደት

የትግበራ ሂደት ጉባኤ በቅድሚያ ከቁምስናዎች በመነሳት፣ በሰበካዎች፣ እንዲሁም በጳጳሳት ጉባኤ ደረጃ ውይይት የሚደረግበት ሲሆን፥ በሁለተኛ ደረጃ በቀጠናዎች የሚካሄድ ውይይት እንደሚኖር ተገልጿል። በሶስተኛ ደረጃ በአህጉራት ውይይት በማድረግ በጥቅምት ወር 2020 ዓ.ም. ለሚካሄደው የዓለም አቀፍ ጉባኤ ግብዓት በመሆን ይጠናቀቃል።

በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚገኙ ስምንት ክልላዊ የጳጳሳት ጉባኤዎች በዚህ ሁለት ቀናትን ለሚቆይ ስብሰባ ተወካዮቻቸውን የላኩ ሲሆን፥ በጉባኤው የመክፈቻ መርሃ ግብር ላይ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ የጉባኤው ተሳታፊዎችን ‘ወደዚህች ጥንታዊ የሰው ዘር መገኛ ወደሆነችው ኢትዮጵያ እንኳን በሰላም መጣችው’ በማለት የመግቢያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው አፍሪካ ለዓለም አቀፋዊቷ ወይም ለሁለንተናዊቷ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተስፋ መሆኗን አስገንዝበው፣ በዚህም መሰረት በአህጉሯ ውስጥ የሚካሄዱ የዚህ ዓይነት ጉባኤዎች ትልቅ ጠቀሜታ እንዳላቸው ያስታወሱ ሲሆን፥ ምንም እንኳን የአፍሪካ ቤተክርስቲያን በአንድነት ለመጓዝ አንዳንድ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ይሄንን ተግዳሮት በጋራ ለመፍታት ጸሎት ዋነኛው መሳሪያ መሆኑን አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይ ሊቀ ጳጳስ ብሪያን ንጎዚ ኡዳግዌ በበኩላቸው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ሰላምታ እና ቡራኬ ለጉባኤው ተሳታፊዎች በማቅረብ፥ የአፍሪካ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ተገኝተው በዚህ የተቀደሰ ጉባኤ ላይ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ቡራኬ በማቅረባቸው የተሰማቸውን ደስታ የገለጹ ሲሆን፥ ጉባኤው በሲኖዶሳዊነት መንፈስ ተካሂዶ የአፍሪካ ቤተክርስቲያን ተግዳሮቶችን መፍታት የሚችሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን እንደሚያቀርብ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት (SECAM) የተመሰረተው፣ በአፍሪካ ውስጥ በምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ በአንድ ድምፅ ለመናገር የሚያስችል መድረክ ለመፍጠር እ.አ.አ. በ 1962-1965 ዓ.ም. በተካሄደው በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ወቅት በአፍሪካ ብፁዓን ጳጳሳት በተገለጸው ፍላጎት መሰረት እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ ይህ በመሆኑም ምክንያት የሴካም መመስረት፣ የአፍሪካን ራዕይ ለጠቅላላው ቤተክርስቲያን ለማድረስ የሚያስችል አህጉራዊ መዋቅር ለመገንባት ብፁዓን ጳጳሳቱ ባሳዩት ቁርጠኝነት የተገኘ ውጤት እንደሆነ የጉባኤው መረጃ ያሳያል።

ከዚህም ባሻገር በእንግሊዘኛው ምህፃረ ቃል SECAM (Symposium of Episcopal Conferences of Africa and Madagascar) (ሴካም) ተብሎ የሚጠራው የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚየም ዓላማ እና ግቡ በሁሉም የአፍሪካና ደሴቶቿ ውስጥ የሚገኙ የጳጳሳት ጉባኤዎች መካከል መልካም የሆነ ህብረትንና ትብብርን እንዲሁም፤ በቤተክርስቲያኒቷ ውስጥ የጋራ ተግባርን ለማጎልበት፣ ቤተ ክርስቲያን በመዳን ሥራ ላይ የምትሰራውን አበርክትሆ ለማገዝ፣ እንዲሁም ቤተክርስቲያኗ በአፍሪካ አህጉር ላይ የእግዚያብሄርን ቤተሰብ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት ለማሳካት የተመሰረተ ህብረት ሲሆን፥ የህዝቦቿን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ደህንነትን ለማረጋገጥ በሚሰራው ሥራ ላይም ተሳትፎ ያደርጋል ተብሏል።

በዚህ አህጉራዊ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስን ጨምሮ የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የጅማ ቦንጋ ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ልሳነክርስቶስ የባህር ዳር ደሴ ሃገረስብከት ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመቂ ሃገረ ስብከት ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የእምድብር ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ብፀዕ አቡነ መርሃክርስቶስ የሃዋሳ ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ደጀኔ የሶዶ ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሚልኪያስ የነቀምቴ ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ክቡር አባ ከተማ አስፋው የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸኃፊ፣ ክቡር አባ አብርሃም ገብረማርያም የሐዋሪያዊ ሥራዎች አስተባባሪ፣ ገዳማዊያት፣ የምዕመናንና የወጣት ተወካዮች ተገኝተዋል።

05 Aug 2026, 06:17