የዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ባለሙያዎች ማህበር የአፍሪካ ፕረዚዳንት የዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ባለሙያዎች ማህበር የአፍሪካ ፕረዚዳንት  

በዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መገናኛዎች ህብረት ውስጥ አፍሪካ የአመራር ዕድሉን ዳግም ማግኘቷ ተነገረ

በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ውስጥ “ዲጂታል መገናኛዎች ለባሕሎች መግባባት እና ለአካባቢ ደህንነት” በሚል ርዕሥ በተዘጋጀው የዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ባለሙያዎች ማህበር ጉባኤ (SIGNIS) ላይ አዲስ የዳይሬክተሮች ቦርድ መቋቋሙ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ የተካሄደው ከሃምሌ 27 እስከ ነሃሴ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ በኪጋሊ ሩዋንዳ በሚካሄደው የዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ባለሙያዎች ማህበር ጉባኤ ጎን ለጎን እንደሆነ እና በዚህም ምርጫ ውጤት መሰረት እ.አ.አ. ከ 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶች የቦርዱን አብላጫ ቁጥር መያዛቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዘመናዊ ሚዲያ ተግዳሮቶችን፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ሥነ-ምግባራዊ አጠቃቀም እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሚሉት ርዕሦች ላይ የሚወያዩ ከመላው ዓለም የተውጣጡ የመገናኛ ባለሙያዎች እና የሚዲያ ተቋማት ተወካዮች ከሃምሌ 28 ጀምሮ በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ የተሰባሰቡ ሲሆን፥ ከኪጋሊ ሃገረ ስብከት፣ ሩዋንዳዊው ካህን አባ ፊዴሌ ሙታባዚ አዲሱ የዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ባለሙያዎች ማህበር የአፍሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው ተነግሯል።

የሩዋንዳ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሥር የሚታተመው ‘ኪንያማቴካ ጋዜጣ’ ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና የሩዋንዳ ጳጳሳት ጉባኤ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አባ ሙታባዚ ምርጫውን ተከትሎ የስልጣን ዘመናቸውን ካጠናቀቁት ከምሁሩ ናይጄሪያዊ ካህን ፕሮፌሰር አባ ዋልተር ቺክዌንዱ ሥልጣን የተረከቡ ሲሆን፥ አዲሱ እና የተሟላው የዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ባለሙያዎች ማህበር የአፍሪካ ሪጂን የዳይሬክተሮች ቦርድ የናይሮቢ የካቶሊክ ሚዲያ ኔትወርክ ሊቀመንበር የሆኑትን ቨርጂኒያ ካቡጉንን እንደሚያካትት የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ አዲሱ የዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ባለሙያዎች ማህበር የአፍሪካ ቅርንጫፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውም ጭምር ተገልጿል።

በዚህ ሰባት አባላት ባሉት የዳይሬክተሮች ቦርድ ውስጥ ከተመረጡት መካከል የቡርኪናፋሶው አባ አሌክሲስ ኡድራኦጎ የሚገኙበት ሲሆን፥ አባ አሌክሲስ ጸሐፊ እና ገንዘብ ያዥ ሆነው መመረጣቸው ተነግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ እህት አናስታኒያ ከሞዛምቢክ፣ አቶ ኩዳክዋሼ ከዚምባብዌ፣ ወይዘሮ ክላሪስ ከናይጄሪያ፣ እንዲሁም ወይዘሮ ምዋሚ ከዛምቢያው መመረጣቸው ተገልጿል።

ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ እና ሁሉን አሳታፊ የሆነ
አባ ሙታባዚ ከተመረጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር ለተወካዮቹ ምስጋናቸውን አቅርበው መጪው የሥራ ወቅት ድጋፋቸው እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ ምርጫውን ከመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና ከሚነገሩ ኦፊሴላዊ ቋንቋዎች ማለትም እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እና ፖርቹጋልኛ ቋንቋዎች አንጻር የአፍሪካን እውነታ በትክክል የሚያንፀባርቅ እና ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ሂደት እንደሆነ ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የአፍሪካ ተወካዮች ጉባኤ አብዛኛዎቹን የቦርድ አባላት ሴቶች አድርጎ በመምረጡ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ ሴቶች ከፆታቸው ባሻገር ልምድ ያላቸው የሚዲያ ባለሙያዎች እና አስተዳዳሪዎች በመሆናቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኪጋሊ እየተካሄደ ባለው የዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ባለሙያዎች ማህበር ዓለም አቀፍ ጉባኤ የአካባቢው አዘጋጅ ኮሚቴ ጊዜያዊ ሰብሳቢ የሆኑት አባ ሙታባዚ፣ በአዘጋጆቹ የተከናወነው ጥንቃቄ የተሞላበት ዝግጅት እና ውጤታማ አሰራር በተወካዮቹ ዘንድ አድናቆት ማትረፋቸውን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ
በኪጋሊ የተካሄደው የዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ባለሙያዎች ማህበር ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከአምስት አህጉራት የተውጣጡ ከ40 በላይ ሀገራት የተወከሉ ከ200 የሚበልጡ የካቶሊክ ጋዜጠኞችን፣ የሚዲያ ባለሙያዎችን እና የግንኙነት ስራ ባለሙያዎችን በአንድ ላይ ያሰባሰበ ሲሆን፥ ይህ በአፍሪካ ሲስተናገድ የመጀመሪያው የዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ባለሙያዎች ማህበር ዓለም አቀፍ ጉባኤ መሆኑ ተነግሯል።

ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ባለሙያዎች ማህበር እንደ ዓለም አቀፍ የግንኙነት ባለሙያዎች ማህበር በይፋ የተመሰረተው እ.አ.አ. በ 2001 ዓ.ም. እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፥ ማህበሩ የተቋቋመው በሮም በተካሄደ የጋራ ጉባኤ ላይ እንደሆነ እና ይህም የተፈጠረው እ.አ.አ. በ 1928 ዓ.ም. የተመሰረቱትን ሁለት ነባር የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ተቋማትን አንድ ላይ በማዋሃድ እንደሆነ ተገልጿል።

06 Aug 2026, 14:19