ፈልግ

በደቡብ ኮርያ መዲና ሴዑል ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የተዘጋጀ መዝሙር ይፋ ሆነ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጪው 2027 ዓ. ም. በደቡብ ኮርያ መዲና ሴኡል ለሚከበር ዓለም የወጣቶች ቀን አንድ ዓመት በቀረበት በዚህ ጊዜ ለፌስቲቫሉ የተዘጋጀው መዝሙር ይፋ መደረጉ ሲታወቅ የመዝሙሩ ርዕሥ “አይዟችሁ! ዓለምን አሸንፌዋለሁ” (ዮሐ. 16:33) የሚል እንደሆነ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመላው ወጣት ካቶሊኮች አእምሮ ውስጥ የሚያስተጋባ እንደሆነ የሚታመነው ይህ መዝሙር ለቀጣዩ የዓለም ወጣቶች ቀን (WYD) ይፋዊ ጭብጥ እንደሆነ እና ዝማሬው ከሐምሌ 27 አስከ ነሐሴ 2/2019 ዓ. ም. በደቡብ ኮርያ መዲና ሴኡል ላይ ለሚሰበሰቡት ካቶሊክ ወጣቶች ዓለም አቀፍ ስብሰባ መነሻ እንደሚሆን ታውቋል።

ለመላው ዓለም እንዲሆን የተዘጋጀ መዝሙር

የመዝሙሩ ጭብጥ “አይዟችሁ! ዓለምን አሸንፌዋለሁ” የሚል ርዕሥ ያለው እና ከዮሐ. 16:33 ላይ የተወሰደ እንደሆነ ታውቋል። ዓለም አቀፋዊ መዝሙር በመሆኑ በተለያዩ ቋንቋዎች ማለትም በኮርያኛ፣ በእንግሊዘኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በስፓኒኛ፣ በፖርቱጋልኛ እና በጣሊያንኛ ተተርጉሞ በመቅረብ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

የኅብረት ዝማሬ መሆኑ

የዚህ መዝሙር አንዱ ዓላማ የዝግጅቱን ቅድመ-ቅምሻ ማቅረብ ሲሆን ከሁሉም በላይ ለዓለም አቀፍ ስብሰባ በሚዘጋጁበት ወቅት ለተሳታፊዎች ቋሚ ማጀቢያ ሆኖ በማገልገል እያንዳንዱ እትም ለተሳታፊዎች ብዙ ትዝታዎችን የሚቀሰቅስ የራሱ ዜማ ያለው እንደሆነ ታውቋል።

የነጻ ውድድር ውጤት የሆነው መዝሙር ዋና ተግባሩ፥ “አይዞህ፣ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” (ዮሐ 16፡33) የሚለውን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2027 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ጭብጥን የሚተረጉም ኦሪጅናል ድርሰት መፍጠር እንደ ነበር ታውቋል።

ከውጪ አገራት የተሰበሰቡ 294 ድርሰቶችን ጨምሮ 434 ድርሰቶች የቀረቡ ሲሆን፥ ከእነዚህ መካከል የተመረጠው የመዝሙት ድርሰት በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ቀርቦ የጸደቀ መሆኑ ታውቋል።

በኮርያ የሚከበር ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን

መዝሙሩን ያቀናበረው የኮርያ ሙዚቀኛ ፍራንሲስ ጂዮን ኪም ሲሆን እርሱም የአገሩን እና የባሕሉን ጣዕም መስጠቱ ታውቋል። በብዛት በኮርያ ቋንቋ የተዘፈኑ ድምጾችን የያዘው መዝሙሩ ከአካባቢው ባህላዊ መሣሪያዎች ጋር በዘመናዊ ዝግጅት የተቀነባበረ ሲሆን፥ የሙዚቃ ቪዲዮው የሴኡልን የመሬት አቀማመጦች እና ምስላዊ እይታዎችን የሚያሳይ እና በሚቀጥለው የበጋ ወቅት ተሳታፊዎች ምን እንደሚጠብቃቸው የመጀመሪያ እይታን እንደሚሰጥ ታውቋል።

እንደ ተለመደው ሁሉ በዋና ከተማ ውስጥ በየሀገረ ስብከቶቹ የሚከበሩት የወጣቶች በዓላት ከዋናው ስብሰባ ቀደም ብሎ ከሐምሌ 22-25/2019 ዓ. ም. ድረስ የሚከበር ሲሆን፥ በዚህ ወቅት በደቡብ ኮርያ ውስጥ የሚገኙ አሥራ አምስት ሀገረ ስብከቶች ወደ አገሪቱ የሚመጡ ምዕመናንን እና መንፈሳዊ ነጋዲያንን በቁምስናቸው እና ቤተሰቦች ዘንድ ለመቀበል እንደሚዘጋጁ ታውቋል።

ከሠላሳ ዓመታት በላይ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1995 ዓ. ም. በፊሊፒን መዲና ማኒላ ከተከበረው ሌላ ይህ የኮርያ የወጣቶች በዓል በእስያ ውስጥ የሚከበር ሁለተኛው እንደሚሆን ታውቋል። ካቶሊካዊ ምዕመናን አናሳ በሆኑበት ኮርያ ውስጥ ዝግጅቱ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፥ በደቡብ ኮርያ ውስጥ ካቶሊካዊ ምዕመናን የህዝቡን 12 በመቶ እንደሚወክሉ ታውቋል።

ቀጣይ እርምጃዎች

ወደ ደቡብ ኮርያ የሚመጡ መንፈሳዊ ንጋዲያን ምዝገባ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት ወር 2026 ዓ. ም. የሚጀመር ሲሆን፥ ይህም በቆይታ ጊዜ እና በተመረጡ ዝግጅቶች ላይ በመመሥረት የተለያዩ ፓኬጆችን እንደሚያቀርብ፣ የሞባይል አፕሊኬሽን እና የተቀናጀ የሎጂስቲክስ ሥርዓትንም እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ታውቋል።

እንደቀደሙት በዓላት መስተንግዶ በአብዛኛው የሚቀርበው በሴኡል ከተማ ሀገረ ስብከት ውስጥ ባሉ ቤተሰቦች እና ቁምስናዎች ሲሆን፥ ወጣቶች የኮርያ ቤተ ክርስቲያንን የዕለት ተዕለት ኑሮ እንዲለማመዱ ወደ 230 የሚጠጉ ቁምስናዎችን እና አስተናጋጅ ቤተሰቦችን በጥንቃቄ በመመልመል እና በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

“እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2027 ዓ. ም. በሴኡል የሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን የተስፋ በዓል መሆኑን ለማረጋገጥ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን” ሲሉ የሴኡል ከተማ ሊቀ ጳጳስ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፒተር ቹንግ ሶን-ታይክ ተናግረዋል። የበዓሉ አስተባባሪ ቡድኖች ዝግጅቱን ለሦስት ዓመታት ሲከታተሉ መቆየታቸውን ገልጸው፥ አሁን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ከመቀበላቸው በፊት ወደ ቤት ዝርጋታ እንደሚገቡ ወደ 30,000 የሚጠጉ በጎ ፈቃደኞች እንደሚሰበሰቡ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ቀድሞውኑ በሥራ ላይ መሆናቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፒተር ቹንግ አስረድተዋል።

በሴኡል ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን የተዘጋጀ መዝሙር
04 Aug 2026, 17:01