ሊቀ ጳጳስ ፎርቹናተስ ንዋቹኩ ሊቀ ጳጳስ ፎርቹናተስ ንዋቹኩ  (Vatican Media)

የሜክሲኮ ወጣቶች የሚስዮናዊነት ጥሪያቸውን በድፍረት እንዲቀበሉ ጥሪ ቀረበላቸው

ከ6,000 በላይ የሚሆኑ የሜክሲኮ ካቶሊካዊያን ወጣቶች በ15ኛው ብሔራዊ የሚስዮናዊ ወጣቶች ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ባለበት ወቅት የቅድስት መንበር የወንጌል ስርጭት ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ፎርቹናተስ ንዋቹኩ፣ ‘ወጣቶች የተጠሩት በሰፊው ባህር ላይ ለመጓዝ እንጂ በዓሳ ማቆያ ገንዳ ውስጥ ተገድቦ ለመቆየት አይደለም’ በማለት ወጣቶች በነፃነት ወንጌልን እንዲያውጁ በምሳሌ አስታውሰዋቸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የሜክሲኮው የቅዱስ ሉዊስ ፖቶሲ ሃገረ ስብከት ከሜክሲኮ የጳጳሳዊ የሚስዮናዊያን ማህበራት ጋር በመተባበር ከሃምሌ 16-19 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደውን 15ኛ ብሔራዊ የሚስዮናዊ ወጣቶች ጉባኤ ያስተናገደ ሲሆን፥ ጉባኤው “ወጣቶች ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ሆነው፥ በተልዕኮ አማካይነት የተስፋ አብሳሪዎች ይሆናሉ” በሚል መሪ ቃል መላው ሀገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች የተውጣጡ ከ6,000 በላይ ወጣቶች በተገኙበት መከበሩ ተነግሯል።

ከምቾት ክልል ባሻገር የሚደረግ ተልዕኮ
ለአራት ቀናት የቆየው ይህ ጉባኤ በጸሎት፣ በስልጠና፣ በሚስዮናዊ ተሞክሮ እና በዲጂታል ዓለም ውስጥ እየተስፋፋ የመጣውን ተልዕኮ ጨምሮ ለወንጌል ስርጭት በተደረገ የታደሰ ቁርጠኝነት ወጣቶቹን ማጠናከሩ የተገለጸ ሲሆን፥ በጉባኤ ላይ የተገኙት ለአንደኛ ደረጃ የወንጌል ስርጭት እና ለተወሰኑ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት የተመደበው የቅድስት መንበር የወንጌል ስርጭት ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፎርቹናቱስ ንዋንቹኩ ወጣቶቹ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚስዮናዊነት ትዕዛዝ በሙሉ ልብ ምላሽ እንዲሰጡ አበረታተዋቸዋል።

ሊቀ ጳጳሱ ይሄንን ያሉት “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱና ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” ከሚለው የወንጌል ትዕዛዝ በመነሳት ሲሆን፥ ሁሉም ክርስቲያኖች መልካሙን ዜና ለሁሉም ሰው በአካልም ሆነ በዲጂታል መድረኮች ለማድረስ እንደተጠሩ አስታውሰዋል።

መረቦችን ወደ ጥልቁ ለመጣል የተደረገ ጥሪ
ሊቀ ጳጳስ ንዋቹኩ ወጣቶቹ ልክ በገሊላ ባህር ላይ እንደነበሩት ደቀ መዛሙርት ሁሉ፣ ከተለመደው አካባቢያቸው አልፈው እንዲሄዱ ያበረታቱ ሲሆን፥ ወጣቶቹ የተላኩት በኢንግሊዘኛው ‘አኳሪየም’ ተብሎ ወደ ሚጠራው ዓሳ ማቆያ ገንዳ፣ ማለትም ወደ ትንሽ፣ አስተማማኝ፣ ቀድሞ ወደሚታወቅ እና ቁጥጥር ወደሚደረግበት ቦታ እንዳልሆነ ጠቁመው፥ ነገር ግን ወደ ሰፊው፣ ጥልቅ እና አንዳንዴም ማዕበል ወደሚበዛበት ወደሰፊው ባህር እንደሆነ አሳስበው፥ እያንዳንዱ የሰው ልጅ ልብ የተፈጠረው ለሰፊው የእግዚአብሔር ተልዕኮ አድማስ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

የወጣቶቹ የሚስዮናዊነት ጥሪ የተጀመረው በሚስጥረ ጥምቀት እንደሆነ እና አስቀድመው እንደተላኩ እንዲሁም አንድ ተልዕኮ እንደተሰጣቸው ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ ይህም ክርስቶስን ማሳወቅ፣ እርሱን መውደድ እና እርሱን መከተል እንደሆነ ያመላከቱ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው በማከልም ወጣቶቹ በእግዚአብሔር እንዲታመኑ እና ባሉበት ቦታ ሁሉ ወንጌልን በድፍረት እንዲሰብኩ ጥሪ አቅርበዋል።

የሚስዮናውያን ልብ
ከዚህም በተጨማሪ ሊቀ ጳጳስ ንዋንቹኩ ወጣቶች ማዳበር የሚገባቸውን ሦስት የሚስዮናዊ ባሕርያትን እንዲቀበሉ ያበረታቱ ሲሆን፥ የመጀመሪያው ለክርስቶስ የሚደረገውን ጥልቅ ቁርጠኝነት የሚያደናቅፍ ማንኛውንም ነገር ትቶ የመሄድ ፈቃደኝነት የሆነውን ከለመዱት ነገር ‘መለየት’ እንደሆነ አስረድተው፥ ሁለተኛው ነገር ‘መገናኘት’ እንደሆነ፣ ይህም ትክክለኛ የወንጌል ስርጭት የሚጀምረው ሃሳቦችን ከመናገር ይልቅ በእውነተኛ ግንኙነት መሆኑን መገንዘብ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ሦስተኛው እና የመጨረሻው ‘የክርስቶስን መስቀል መቀበል’ እንደሆነ ጠቅሰው፥ የሚስዮናዊነት ሥራ አፋጣኝ ውጤቶች ስለማያሳዩ፣ ብዙውን ጊዜ መስዋዕትነትን፣ ጽናትን እና ታማኝነትን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ ንዋንቹኩ በመጨረሻም ወጣቶቹ የተልዕኮ ተግዳሮቶችን እንዳይፈሩ አሳስበው፥ የሰብዓዊነት ባህር ሰፊ እንደሆነ እና ዓለማችን ሚስዮናውያን እንደሚያስፈልጋት፣ ቤተክርስቲያን ወጣቶችን እንደምትፈልግ እና ክርስቶስም ጥሪ እያደረገላቸው እንደሆነ ያሳሰቡ ሲሆን፥ የክርስቶስን ፊት ለሌሎች ለማሳየት ከሕይወታቸው ጋር የተቆራኘውን ነገር ለመሠዋት ፈቃደኞች መሆን እንዳለባቸው መክረዋል።

ለዛሬ ዘመን የሚሆን ሚስዮናዊ ደቀመዝሙር መሆን
ጉባኤው የወደፊቱን በልበ ሙሉነት በመመልከት የቤተክርስቲያኗን የሚስዮናዊነትሥራ ቀጣይነት ያስታወሰ ሲሆን፥ ስብሰባው የተካሄደው የዓለም ተልዕኮ እሑድ መቶኛ ዓመት እና የሜክሲኮ ወጣት ሚሲዮናዊያን ሊግ 75ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተከበረበት ወቅት እንደሆነ፥ እንዲሁም 15ኛው ብሄራዊ የሚሲዮናውያን የወጣቶች ጉባኤ ቤተክርስቲያን ወጣት ሚስዮናውያን ደቀ መዛሙርትን ለማቋቋም ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑ ተነግሯል።

የሜክሲኮ ጳጳሳዊ ተልዕኮ ማኅበራት ብሔራዊ ዳይሬክተር የሆኑት አንቶኒዮ ደ ጂሰስ ማስኮሮ በበኩላቸው እነዚህ ክንውኖች እ.አ.አ. ከ 1982 ዓ.ም. ጀምሮ በስብሰባዎች፣ በምስክርነቶች፣ በቅዱስ ቁርባን ሥነ-ሥርዓቶች፣ በጸሎት እና በኅብረት የበለጸገ መርሃ ግብር አማካኝነት የሚስዮናውያንን ዝግጅትና ስልጠና ሲቀርጹ መቆየታቸውን ያመላከቱ ሲሆን፥ የዘንድሮው ጉባኤ ቁልፍ ትኩረት በዲጂታል የወንጌል ስርጭት ላይ ያተኮረ እና በጉባኤው ላይ የተሳተፉ ካቶሊካዊያን የይዘት ፈጣሪዎች ማህበራዊ ሚዲያ ወንጌልን ለማወጅ የሚያስችል መድረክ መሆኑን ለተሳታፊዎች ማካፈላቸው ተነግሯል።

የጉባኤው መርሃ ግብር የተጠናቀቀው ተሳታፊዎች ያደረጉትን ሚስዮናዊ ጉዞ በመከተል የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ቡራኬን ያስተላለፉት በሜክሲኮ የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይ በሆኑት ሊቀ ጳጳስ ጆሴፍ ስፒተሪ መሪነት በተካሄደ መስዋዕተ ቅዳሴ ሲሆን፥ ተሳታፊዎች በአንድ ጉባኤ ላይ ተካፍሎ ለመመለስ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ማህበረሰባቸው ሲመለሱ እንደ ሚስዮናዊ ደቀ መዛሙርት የወንጌልን ተስፋ እና ደስታ ለማካፈል አዲስ ቃል ኪዳን በመግባትም ጭምር እንደሆነ ተገልጿል።

03 Aug 2026, 14:04