የማሪያም አፍቃሪዎች እንሁን የማሪያም አፍቃሪዎች እንሁን  (Lazaro Gutierrez fotografo della archidiocesi di Managua )

የማሪያም አፍቃሪዎች እንሁን

እግዚአብሔርን የምናፈቅር ከሆነ ማርያምን ደግሞ ማፍቀር አለብን። የተመረጠች ፍጥረት በመሆኗና በመንፈስ እናታችንን ስለሆነች ልጃዊ ፍቅር ልንገልጥላትና ከፍጥረታት ሁሉ በላይ ልናከብራት ይገባናል። እመቤታችን ማርያም የፍጥረታት የበላይ ስለሆነች አምላክም ከሁሉም ፍጥረት አስበልጦ ስለመረጣት ከአዳም ልጆች ሁሉ በላይ ናት። የሰማይ ንግሥት በመሆንዋ ከፍ ያለ አክብሮት የሚገባት ፍቅርም የሚሰጣት እናት ናት። ፈጣሪ ራሱ ከአፈቀራት እኛ ተራ የሆንን ፍጥረታት እርሷን ለማፍቀር ስለማይቻለን ታላቅነቷ ራሱ እንድናከብራት ይገፋፋናል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

እመቤታችን ማርያም የመድኒታችን የኢየሱስ እናት ናት። ኢየሱስን የምናፈቅር ከሆነ እናቱን ማፍቀር ግዴታ ነው። ይህ ካልሆን ግን ኢየሱስ አይደሰትብንም። እናቱን ካልወደድንለት እርሱም አይወደንም። ኢየሱስ በእኛ እንዲደሰት ከፈለግን ማርያምን ማፍቀር አንርሳ። እመቤታችን ማርያም የመንግስተ ሰማያት እናታችን ናት። በሥጋ እናታችን የምትሆንንን ለየት ባለ ፍቅር የምንወዳትን ያቺን ሰማያዊት እናታችን ደግሞ እንዲሁም እንድናፈቅራት ያስፈልጋል። ማርያም ከሁሉም እናቶች ትበልጣለች። ለእኛም ብዙ ታስብልናለች፣ ልቧ ዘወትር ከእኛ ጋር ነው፣ አምላክ የፈጠራት ለአዳም ልጆች ሁሉ እናት እንድትሆን ብሎ ነው።

እመቤታችን ማርያም እኛን ታፈቅረናለች። ምንም እንኳን እኛ ክፋዎች ብንሆን እርስዋ አትጠላንም። ጥቅማችንን ትፈልጋለች፣ ስለ ደኀንነታችንን ታስብልናለች፣ ስለ ኃጢአታችንም ካሳ ልጇን ሰጥታናለች። በእኛ ጥቅም ስለምትደሰት ጥሩ ተግባርን ስንፈጽም ደስ ይላታል፣ ክፋን ስናደርግ ደግሞ ታዝናለች፣ ስለዚህም ኃጢአትን ትተን ጽድቅን እንድናደርግ ትማጠነናለች። እርሷ በእግዚአብሔር ፊት ጠበቃችን ናት፣ ምህረትና ጸጋን ታማልደናለች፣ ልመናዋ ደግሞ የሚሰማ ነው፣ እርሷ እኛን ይህን ያህል የምታፈቅረንና የምትጨነቅልን ከሆነ እኛም እርስዋን በሙሉ ልባችን ልናፈቀራት ይገባናል።

እመቤታችን ማርያም የጸጋ መስኖ ናት። እግዚአብሔር ደኀንነታችንን በማርያም በኩል እንዲመጣልን እንዳደረገ እንዲሁም ደግሞ ጸጋን በእርስዋ በኩል እንድናገኝ ይፈልጋል። እርስዋ የጸጋ አዳይ ናት። ለእኛ ደግሞ ጸጋ የግድ ያስፈልገናል። ያለ እርሷ ምንም ዓይነት የጽድቅና የደኀንነት ሥራ ማድረግ አንችልም። ለእኛ ጸጋ ማጣት ማለት ዝናም እንዳጣ የእርሻ መሬት መሆን ማለት ነው።

ስለዚህ ይህችን የጸጋ መስኖ በመጠጋት የእርስዋ ወዳጆች መሆን ለደኀንነታችን ዋስትና ነው። የሚወዳትን በልዩ መንገድ ትመራቸዋለች። በሰማይ ከእርስዋ ጋር እንዲነግሡ ታደርጋቸዋለች ዕርዳታዋን ወይም የደኀንነትን ጸጋ እንድናገኝ የእርሷዋ አፍቃሪዎች እንሁን።

12 Aug 2026, 10:54