የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ዓመታዊ 60ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል
አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
60ኛ ዓመታዊ መደበኛ ጉባኤያቸውን በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ኮንሶላታ ማርያም ቁምስና ውስጥ የጀመሩት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ከዚህ ጉባኤ መጀመር ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ሲካሄድ የነበረውን የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት አህጉር አቀፍ ስብሰባ ላይ ሲሳተፉ በመቆየታቸው የዘንድሮውን የጉባኤ ቀናትን እንደሚያሳጥረው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ፣ ማለትም በታህሳስ እና ሐምሌ ወር ላይ የሚደረግ ሲሆን፥ በዚህኛው 60ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብሪያን ንጎዚ ኡዳግዌ መገኘታቸው እና ከብፁዓን ጳጳሳቱ ጋር ስለ ዓለም አቀፍ እና ሃገር አቀፍ የቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
በፍልሰታ ማርያም ጾም ዋዜማ ላይ በተጀመረው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ዓመታዊ 60ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በተለይም ስለሃገራችን ሰላም እና እየተካሔደ ለሚገኘው አገራዊ የምክክር ጉባኤ ምዕመናን ጸሎት እንዲያደርጉ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህም ባሻገር እየተካሄደ በሚገኘው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት 60ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከሚነሱ አንኳር ጉዳዮች መካከል የሀገሪቱን የሰላም ሁኔታ፣ የቤተክርስትያን ሐዋርያዊ ህይወት እና ህጋዊ ማዕቀፍ ጉዳይ፣ የምዕመናን፣ የወጣቶች፣ የገዳማውያን እና የገዳማውያት ህይወት፣ ለተለያዩ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ስለሚያገለግሉ ገዳማውያን እና በጎ ፍቃደኞች ሁኔታ እና የቤተክርቲያን ተቋማት የሥራ ሂደት ጉዳዮች እንደሚነሱ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት የሆኑት የብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ የጡረታ እረፍትን ተከትሎ በቀጣይ ጉባኤውን የሚመሩ ጳጳስ ምርጫ በዋነኝነት የሚወያዩባቸው አጀንዳዎች መሆናቸውን የጉባኤው ማህበራዊ ተግባቦት ተወካይ ብፁዕ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ የባህርዳር ደሴ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ጉባኤ ከቀናት በፊት በኬንያ በተካሄደው 21ኛ የምሥራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤ ላይ የተወሰኑ ውሳኔዎች ተግባራዊ የሚሆኑበት መንገዶች ዙሪያ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በምትሰራቸው ልማታዊ እና ሃዋሪያዊ ተግባራት ወቅት ስለሚያጋጥሟት ተግዳሮቶች ዙሪያ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩንቨርሲቲን በተመለከተ፣ እንዲሁም በወጣቶች እና በሌሎች የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ እየመከረ እስከ ነሐሴ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚቆይ መሆኑም ተገልጿል።