ፈልግ

ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ጉባኤ በሩዋንዳ ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ጉባኤ በሩዋንዳ 

ማኅበራዊ ሚዲያ ለመገናኛ እና ለወንጌል አገልግሎት አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ

የዘመናዊ ሚዲያ ተግዳሮቶችን፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ሥነ-ምግባራዊ አጠቃቀም እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሚሉት ርዕሦች ላይ የሚወያዩ ከመላው ዓለም የተውጣጡ የመገናኛ ባለሙያዎች እና የሚዲያ ተቋማት ተወካዮች ከሐምሌ 28/2018 ዓ. ም. ጀምሮ በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ መሰብሰባቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ “ዲጂታል መገናኛዎች ለባሕሎች መግባባት እና ለአካባቢ ደህንነት” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉባኤ፥ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የተፈረመውን መልዕክት ጨምሮ የተለያዩ የአብሮነት መልዕክቶችን የያዘ መልዕክት፥ በሩዋንዳ የሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ተውካይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አርናልዶ ኤስ ካታላን ለጉባኤው በንባብ አቅርበዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ አርናልዶ ኤስ ካታላን “የሰው ልጅ ታላቅነት” የተሰኘውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ ሠነድ በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ “የአውታረ መረብ ላይ ግንኙነት መረጃን ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ባሕልን መፍጠር ነው” ሲሉ ተናግረው፥ ምክንያቱም ሰዎች ዓለምን የሚመለከቱበትን መንገድ የመቅረጽ ኃይል ስላለው እና በዚህም ምክንያት የጋራ ህሊናን በእጅጉ ስለሚነካ ነው” ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መገናኛዎች ጉባኤ በሩዋንዳ
ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መገናኛዎች ጉባኤ በሩዋንዳ

እርቅ፣ ብሔራዊ አንድነት ማሳደግ እና ትብብር

የኪጋሊ ሊቀ ጳጳስ እና የሩዋንዳ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት አንትዋን ካምባንዳ የጉባኤውን ጭብጥ በመጥቀስ ባደረጉት ንግግር፥ ሚዲያ ለመገናኛ እና ለወንጌል አገልግሎት ያለውን አስፈላጊነት ሲያብራሩ፥ ሚዲያ ፈውስን፣ እርቅን፣ ብሔራዊ አንድነትን እና ትብብርን ለማስተዋወቅ እንደ መንገድ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1994 ዓ. ም. ከተከሰተው የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ትምህርት በመውሰድ፣ በአገሪቱ ውስጥ ለጦርነት አስተዋጽኦ ያደረገውን ሚዲያ በአግባቡ አለመጠቀምን ጠቁመው፥ የጉባኤው ተሳታፊዎች ሚዲያን በአግባቡ ባለመጠቀም ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶችን እና ጉዳቶችን ለመገምገም ጊዜ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና የአንድነት መድረክ

የቅድስት መንበር መገናኛዎች ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በዲጂታል ዓለም ውስጥ አካላዊ ግንኙነት ያለውን አስፈላጊነት ሲያብራሩ፥ “እንደዚህ ዓይነት ስብሰባዎች በዲጂታል ዓለም ውስጥ በአካል የመገናኘት አስፈላጊነትን ያስታውሱናል” ብለው፥ መግባባት የሚጀምረው በቴክኖሎጂ ሳይሆን ከሰዎች ጋር በመገናኘት ነው” ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ተቋም “SIGNS” የቤተ ክርስቲያን ቢሮክራሲ ሳይሆን ነገር ግን የሰዎች አውታረ መረብ፣ ተመሳሳይ እምነት የሚጋሩ የባለሙያዎች አውታረ መረብ መሆን እንዳለበት አሳስበው፥ “እነዚህ የእምነት ግንኙነቶች የሚመሠረቱበት፣ እውነተኛ መረጃ የሚጋራበት እና ጥሩ የሥራ ዕቅዶች የሚነደፉበት ቦታ መሆን አለበት” ብለዋል።

የቅድስት መንበር መገናኛዎች ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ
የቅድስት መንበር መገናኛዎች ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ

ለአንድነት የሚደረግ የመገናኛ አስፈላጊነት

ለቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ያላቸውን አድናቆት የገለጹት፥ የዓለም አቀፍ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ተቋም “SIGNS” ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ሄለን ኦስማን፥ ጽሕፈት ቤቱ ከተቋማቸው ጋር ያለውን ዘላቂ ትብብር አስታውሰው፥ በሲኖዶሳዊነት መንፈስ ትብብር እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል። “በዓለም አቀፍ ጫናዎች መካከል ክርስቲያናዊ አንድነትን እና ትብብርን የሚያመጣ ጠንካራ የመገናኛ መረብ ያስፈልገናል” ሲሉም አክለዋል።

አባ ኢሄጂሪካ በንግግራቸው፥ በካቶሊክ የሚዲያ ድርጅቶች እና በቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ቢሮዎች መካከል የበለጠ አንድነት እንዲኖር ጥሪ አቅርበው፥ ይህም አብረው በመሥራት ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ዘመናዊውን ማኅበረሰብ ማገልገል የሚችል ተዓማኒ የካቶሊክ ሚዲያ ለመገንባት ያስችላል” ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2026 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ጉባኤ እስከ ነሐሴ 2/2018 ዓ. ም. ድረስ የሚቆይ ሲሆን በማኅበራዊ መገናኛ አገልግሎቶች ውስጥ ብቅ ያሉ ጉዳዮችን ለመመልከት፣ ለመማር፣ ለመገናኘት እና ለመወያየት ከመላው ዓለም የመጡ የካቶሊክ መገናኛ ባለሞያዎችን በማሰባሰብ በባሕሎች እና በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ተስፋ እንደሚሰጥ ታውቋል።

ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መገናኛዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች
ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መገናኛዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች
05 Aug 2026, 15:46