በአውሮፓ ረጅም የተባለለት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሐውልት በፖላንድ ተባረከ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ለመንፈሳዊ ነጋዲያን የተዘጋጀ የጸሎት ቦታ
የእመቤታችን ማርያም የምሕረት እናት ሐውልት በአቅራቢያው ወደሚገኝ የሐዘንተኛይቱ እመቤታችን ማርያም ጸሎት ቤት ምዕመናንን ለረጅም ጊዜ ሲጋብዝ በቆየ ቦታ ላይ የቆመ ሲሆን አዲሱን ሐውልት ከነባር የጸሎት እና የንግደት ልማድ ጋር እንደሚያገናኝ ታውቋል።
በፖላንድ የዎልዝላዌክ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ክሪዝስቶፍ ዎትኮቭስኪ በመስዋዕተ ቅዳሴው እና በሐውልቱ የቡራኬ ሥነ-ሥርዓት ወቅት ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ “የቆምንበት ቦታ ተራ ቦታ ሳይሆን በምዕመናን ጸሎት የተቀደሰ ሥፍራ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል። የእመቤታችን ማርያም የምህረት እናት ሐውልት ለብዙ አሥርተ ዓመታት የጸሎት እና የንግደት ሥፍራ ሆኖ በቆየበት ቦታ ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመው፥ ከጸሎት እና ከአምልኮ ሥፍራ ጋር የቆየ ግንኙነት እንዳለው አፅንዖት ሰጥተዋል።
“ዓይኖቻችንን ወደ ማርያም እናነሳለን”
ብጹዕ አቡነ ውትኮቭስኪ ስለ እመቤታችን ማርያም የምህረት እናት ሐውልት ሲናገሩ፥ በስፔይን ባርሴሎና በሚገኘው “ሳግራዳ ፋሚሊያ” ባሲሊካ ውስጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ጠቅሰው፥ “የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ መቅደስ የሚገኝበትን ግንብ በምንደንቅበት ወቅት ስለ እግዚአብሔር እና ስለ ራሳችን እውነት የሚገልጥልን እርሱ ብቻ ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል።
“በኮኖቶፒ ዓይኖቻችንን ወደ እግዚአብሔር ወደምትመራን እመቤታችን ማርያም እናነሳለን፤ የምህረት እናት እመቤታችን ማርያም እግዚአብሔርን እንድናስታውስ ታደርገናለች፤ በዚህ ምስል ላይ እመቤታችን ማርያም ወደ እኛ ጎንበስ ብላ እጆቿን ከፍታ ሁላችንን ትቀበለናለች፣ ዓይኖቻችንን ወደ እግዚአብሔር እና ወደ ሰማይ እንድናነሳ ትጋብዘናለች” ብለው፥ አክለውም፥ “ዛሬ ብዙ ሰዎች ዓይኖቻቸውን በምድር እና በራሳቸው ላይ ብቻ ያተኩራሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
ከመለኮታዊ ምሕረት ጋር በቅርበት የተቆራኘ ሀገረ ስብከት
ብጹዕ አቡነ ውትኮቭስኪ “የምሕረት እናት እመቤታችን ማርያም” የሚለውን የሐውልቱን ስም በመጥቀስ፥ የመለኮታዊ ምሕረት ሐዋርያ የሆነች ቅድስት ፋውስቲና ኮዋልስካ በዊሎክላውክ ሀገረ ስብከት ውስጥ መወለዷን፣ መጠመቋን እና የመጀመሪያ ቁርባን መቀበሏን አስታውሰዋል።
የምስጋና ቃል
ብጹዕ አቡነ ውትኮቭስኪ በኮኖቶፒ በሚገኘው የምህረት እናት እመቤታችን ማርያም የሐውልት ቡራኬ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር፥ “ይህ ሐውልት ከመሥራቹ የቀረበ የምስጋና ቃል ነው” ብለው፥ የምህረት እናት እመቤታችን ማርያም ሐውልት እንዲቆም ላደረጉት እንዲሁም ለዲዛይነሮች፣ ለአርክቴክቶች እና ለግንበኞች በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ከ55 ሜትር በላይ ቁመት ያለው የምህረት እናት እመቤታችን ማርያም ሐውልት ከሌሎች በተጨማሪ በሪዮ ዴ ጄኔሮ ከሚገኘው ታዋቂው የክርስቶስ ቤዛዊ ሐውልት የበለጠ ርዝመት ያለው ሲሆን፥ የመመልከቻ ሰገነቱ ከመሬት 15 ሜትር በላይ እንደሆነ ታውቋል።