ፈልግ

በኮሎምቢያ ማኒዛሌስ ከተማ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት የፈራረሰ ሕንፃ ፍርስራሽ ውስጥ፣ የአደጋ ጊዜ የማዳን ቡድኖች በሕይወት የተረፉ ሰዎችን በመፈለግ ላይ በኮሎምቢያ ማኒዛሌስ ከተማ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት የፈራረሰ ሕንፃ ፍርስራሽ ውስጥ፣ የአደጋ ጊዜ የማዳን ቡድኖች በሕይወት የተረፉ ሰዎችን በመፈለግ ላይ   (AFP or licensors)

የኮሎምቢያ ሊቀ ጳጳስ በሃገሪቱ የደረሰው "የመሬት መንቀጥቀጡ እጅግ አውዳሚ እንደነበር" ገለጹ

በኮሎምቢያ የማኒዛሌስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጆሴ ሚጌል ጎሜዝ ሮድሪጌዝ ነሃሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በኮሎምቢያ የደረሰው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥን ተከትሎ ከቫቲካን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት እንደተናገሩት የእግዚአብሔር ጥበቃና እርዳታ ህዝቡ ወደፊት እንዲራመድ፣ ችግሮችን እንዲያሸንፍ እና ጉዳት የደረሰባቸው ድጋፍ እንዲያገኙ እንደሚያስችል ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ በሃገሪቱ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ እጅግ ከፍተኛ ኃይል እንደነበረው እና በመሬት ላይ የተገነባውን ማንኛውንም ነገር የሚያፈርስ ይመስል እንደነበር ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ነሃሴ 4 ኮሎምቢያ ውስጥ በተከሰተ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያንስ የ200 ሰዎች ሕይወት ማለፉ እና በርካታ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን፣ እንዲሁም በርካታ ሕንጻዎች መፍረሳቸው የተነገረ ሲሆን፥ በሕንጻዎች ፍርስራሽ ሥር ሰዎች ተቀብረዋል የሚል ስጋት በመኖሩ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ተገልጿል።

ባለፉት ዓመታት ኮሎምቢያ ውስጥ ካጋጠመው ከባድ ተፈጥሯዊ ክስተቶች አንዱ የሆነው ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 7.4 ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፥ በኮሎምቢያ ቾኮ ግዛት የታየው የመሬት መንቀጥቀጥ ከመሬት በ103 ኪሎ ሜትር በታች የተከሰተ እንደሆነ የአገሪቱ የጂኦሎጂካል አገልግሎት አስታውቋል።

ይሄንን ተከትሎ የማኒዛሌስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጆሴ ሚጌል ጎሜዝ አደጋውን አስመልክተው ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‘የዚህ አጠቃላይ ሁኔታ ዋና ገላጭ ምስል የክልሉ መለያ በሆነው የማኒዛሌስ ካቴድራል ላይ የደረሰው ጉዳት’ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ይህ የ 'ኒዮ-ጎቲክ' የአርክቴክቸር ዘይቤ ያለው ህንጻ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት እና ከህንጻው ማማዎች አንደኛው በአደጋው መፍረሱን ገልጸዋል።

“በመሬት መንቀጥቀጡ ወቅት ያጋጠመን ነገር እጅግ አስደንጋጭ ነበር” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ጎሜዝ፥ ይህ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭነት ያለበት አከባቢ በመሆኑ፣ አልፎ አልፎ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱ የተለመደ ነገረ መሆኑን ጠቅሰው፥ ነገር ግን ይሄኛው እጅግ ከፍተኛ ኃይል የነበረው እና በመሬት ላይ የተገነባውን ማንኛውንም ነገር የሚያፈርስ ይመስል እንደነበር” ተናግረዋል።

በመሬት መንቀጥቀጡ የተጎዱ አብያተ ክርስቲያናት
ሊቀ ጳጳስ ጎሜዝ ጉዳቱን አስመልክተው ከቫቲካን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአካባቢው በነበሩ “መኖሪያ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት” እንደደረሰና በዚህም ምክንያት በርካታ ሰዎችም ቤት አልባ እንደሆኑ ገልጸው፥ አብያተ ክርስቲያናትንና ሌሎች የቤተክርስቲያን ሕንጻዎችን በተመለከተ “ከእነዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል” የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በተለይም የዚህ ሁሉ ጉዳት ዋና ማሳያ የሆነውና የሃገሪቱ ትልቅ ምልክት በሆነው የማኒዛሌስ ካቴድራል ላይ የደረሰው ጉዳት መሆኑን ያነሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ በዚህ ካቴድራል ሕንጻ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን እና ከዋናው ሕንጻ ጎን ከሚገኙት ማማዎች አንዱ፣ ማለትም ሁለተኛ ደረጃ ማማ ወድቆ በቤተክርስቲያኗ ዋና ሕንጻ ላይ ተደግፎ መቅረቱን አመላክተው፥ በአሁኑ ወቅት አካባቢው ለሕዝብም ሆነ ለካህናት ዝግ ሆኖ የባለሙያዎችን ግምገማ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የበጎ አድራጎት እና የአንድነት መንፈስ
ከመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው በኋላ የተሰጠው ምላሽ ፈጣን እንደነበር ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ ቤተክርስቲያኗ ወዲያውኑ ‘የምግብ ባንክ’ በተሰኘው የካቶሊክ ተቋም በኩል እርዳታ ማቅረቧን ጠቅሰው፥ “በክርስቲያናዊ የልግስና እና የአብሮነት መንፈስ የተነሳሱ በርካታ ሰዎችም እርዳታ ለመጀመር ዝግጁ እና ፈቃደኛ እንደነበሩ፥ እንዲያውም ሰዎች አስቸኳይ እና ፈጣን የሆነ ልገሳ ለማድረግ ወደ ተቋሙ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

የማኒዛሌስ ሊቀ ጳጳስ እንደገለጹት የህዝቡ እጅግ አጣዳፊ ፍላጎትቶች ከመኖሪያ ቤት ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰው፥ አንዳንድ ሰዎች ንብረታቸውን ሙሉ በሙሉ ማጣታቸውን፣ ሌሎች ደግሞ ወደ ቤታቸው ከመመለሳቸው በፊት ህንጻዎቹ ለደህንነት ሲባል እንዲገመገሙ መጠበቅ እንደነበረባቸው የገለጹ ሲሆን፥ ሁለተኛው ዋና ፍላጎት የምግብ እጥረት ስለሚኖር ለእነዚህ የመጀመሪያ ቀናት የሚሆን የምግብ አቅርቦት እንደሆነ ጠቅሰው፥ በቀጣይም “ሁሉንም ነገር ላጡ ሰዎች የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች እና መሰረታዊ ፍላጎቶች” አስፈላጊ እንደሆኑ አሳስበዋል።

ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አጋርነት ምስጋና
ከዚህም በተጨማሪ ሊቀ ጳጳስ ጎሜዝ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ላስተላለፉት የአብሮነት መልዕክት ምስጋናቸውን ገልጸው፥ “ይህ መልዕክት በተለይም ለኮለሚቢያ ህዝብ አባታዊ ደግነትን እና ቅርበትን እንደሚያንጸባርቅ ገልጸው፥ እነዚህ የአብሮነት መልዕክቶች የቤተክርስቲያኑ እረኛ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የሚያደርገው እርዳታ እና አብሮነት እንደሆኑ፣ እንዲሁም ወደፊት ለመቀጠል የሚያበረታታ ድጋፍ ሆኖ ይታያሉ ብለዋል።

መልሶ የመገንባት ቁርጠኝነት
የማኒዛሌሱ ሊቀ ጳጳስ በመጨረሻም በእርግጥም አስፈሪ በሆኑ ሁኔታዎችና ጊዜያት ውስጥ፣ እንደዚህ ዓይነት ክስተት ከተከሰተ በኋላ ወዲያውኑ በነፍስ ውስጥ የሚቀረው ስሜት፥ በአካል፣ በንብረት ወይም በቤተሰብ ረገድ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ፈጣን እርዳታ እንዲያገኙ የመሻት ስሜት እንደሆነ አስረድተው፥ በሁለተኛ ደረጃ መልሶ የመገንባት ሥራን ወዲያውኑ የመጀመር ፍላጎት መኖሩን ጠቁመው፥ የፍርስራሽ ክምር ገና እየተወገደ ባለበት ወቅትም እንኳን ቢሆን ወደፊት የመራመድ፣ ነገሮችን እንደገና የማስተካከል እና የማጠናከር ቁርጠኝነት መኖሩን በማመላከት የተስፋ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ “በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳን ቢሆን እግዚያብሔርን ለማመስገንና ለማምለክ እየሞከርን እንገኛለን” ሲሉ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።

14 Aug 2026, 14:45