በሕግ ሙያ ውስጥ ያሉ የካቶሊክ እህቶች ለትንቢታዊ ምስክርነት መጠራታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የጉባኤው ተሳታፊዎች የሕግ ባለሙያዎች በሃይማኖታዊ ሕይወት ውስጥ ጥበቃን፣ ፍትህን እና ተጠያቂነትን በማሳደግ ረገድ ባላቸውን ትንቢታዊ ሚና ዙሪያ እንዲነጋገሩ እድል መስጠቱ ተገልጿል።
ትንቢታዊ ምስክር
በኮንራድ ሂልተን ፋውንዴሽን የፕሮግራም ትግበራ ተባባሪ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የካቶሊክ እህቶች ክፍል ኃላፊ የሆኑት እህት ጄን ዋካሂው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የእንኳን ደህና መጣችው መልዕክት አስተላልፈው፣ ስብሰባውን በማደራጀት ረገድ ለተደረጉት ጥረቶች አድናቆታቸውን የገለጹ ሲሆን፥ ጉባኤውን በውይይት፣ በትብብር እና በአገልግሎት አማካኝነት በአፍሪካ ውስጥ የሃይማኖታዊ ሕይወትን ለማጠናከር ያለመ የጋራ ቁርጠኝነት እና ትርጉም ያለው የተስፋ ምልክት ነው ሲሉ ገልጸውታል።
“ትንቢታዊ ምስክርነት፡ ሰዎችን ከአደጋና ከጉዳት መጠበቅ እንደ ወንጌል መገለጫ” በሚለው የጉባኤው ጭብጥ ላይ ሃሳባቸውን ያካፈሉት እህት ዋካሂው፥ ትንቢታዊ ምስክርነት የተመሠረተው ለወንጌል እሴቶች ታማኝ በሆነ ሕይወት ላይ መሆኑን አስረድተው፥ ይህም ማለት ስቃይ ውስጥ ከሚገኙት ጋር በመተባበር መቆም፣ እውነትን በፍቅር መናገር እና በእግዚአብሔር ምሕረት፣ ርኅራኄ እና ፍትህ ኢፍትሃዊነትን መቃወም እንደሆነ ገልጸዋል።
የሁሉንም ሰው ክብር መጠበቅ
የመክፈቻ ንግግሩ ሰብዓዊ ጥበቃ ማድረግ አስተዳደራዊ መስፈርት ወይም ህጋዊ ግዴታ ብቻ ሳይሆን ‘ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ’ በማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን የወንጌል ግዴታ ስለመሆኑ አፅንዖት የሰጠ ሲሆን፥ እህት ዋካሂው የሃይማኖት ተቋማት እና የቤተክርስቲያን ማህበረሰቦች የሴቶችን፣ የህፃናትን እና ተጋላጭ የሆኑ አዋቂዎችን ሰብዓዊ ክብር የሚቀንሱ ተግባራትን እና ልማዶችን እንዲመረምሩ ጥሪ አቅርበዋል።
እህት ዋካሂው ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህፃናት ልጆች ጥበቃ ጉዳዮችን የሚከታተለው ጳጳሳዊ ኮሚሽን እ.አ.አ. በ 2024 ዓ.ም. ያወጣውን ሪፖርት በመጥቀስ፥ ደካማ የሆኑ ሀገራዊ መመሪያዎች፣ የተገደበ የተጎጂዎች ተደራሽነት፣ የጥበቃና ደህንነት ባለሙያዎች እጥረት፣ በቂ ያልሆኑ ሀብቶች እንዲሁም የተጠያቂነት ክፍተቶችን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሁኔታዎችን የሚነኩ የጥበቃ ተግዳሮቶችን አጉልተው አሳይተዋል።
እህት ዋካሂው በመጨረሻም ይህ ጉባኤ በቤተክርስቲያን ማህበረሰቦች ውስጥ ግንዛቤን ለማስጨበጥ እና ለማጠናከር፣ ሰዎችን ከአደጋ የመጠበቅ አሰራሮችን ለማዳበር እና ከተጎጂዎች ጋር በይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ አብሮ ለመጓዝ የሚያስችል ዕድልን እንደሚፈጥር በመግለጽ አጠቃለዋል።