በኦሃዮ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ወጣቶችን በመቅረጽ ረገድ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የዓለም የትምህርት ቀን የኢዩቤሊዩ በዓልን እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “አዳዲስ የተስፋ መንገዶችን ማዘጋጀት” በሚል ርዕስ ይፋ ያደረጉትን ሐዋርያዊ መልዕክት ተከትሎ ብፁዕ አቡነ ፈርናንዴዝ በአዲሱ የትምህርት ዘመን መጀመሪያ ላይ "ካቶሊካዊ ትምህርት፡ የተስፋ ተግባር" በሚል ርዕስ ጽሑፍ ማዘጋጀታቸው የተነገረ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ የኮሎምቦሱ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፈርናንዴዝ ከቫቲካን ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ሀገረ ስብከታቸው በካቶሊክ ትምህርት ቤቶቹ ረገድ "እጅግ አስደናቂ እድገት" እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገረ ስብከታቸው ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአዲሱ የትምህርት ዘመን እየከፈተ መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህም በተጨማሪ አዲስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት ማቀዱንም ይፋ አድርገዋል።
ብፁዕ አቡነ ፈርናንዴዝ ይህ እድገት ትልቅ የሚስዮናዊነት ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው፥ “የወጣቶቻችንን ልብ፣ አእምሮ እና ነፍስ የማስተማርና የመቅረጽ ዕድል እጅግ ታላቅ ነው” ያሉ ሲሆን፥ የወንጌልን ደስታ ለሁሉም ለማድረስ እና ወጣቶችን በእምነት ጉዞአቸው ወቅት አብረን ለመጓዝ እንፈልጋለን ብለዋል።
የጋራ ጥሪ
ብፁዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ የትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን፣ መምህራን እና ቤተሰቦች ሁሉም ወጣቶችን ወንጌል የማስተማር ኃላፊነት እንደሚጋሩ የገለጹት ብፁዕ አቡነ ፈርናንዴዝ፥ ወላጆች በእምነት መንገድ የልጆቻቸው የመጀመሪያ አስተማሪዎች መሆናቸውን አመላክተው፥ መምህራንም ሥራቸውን እንደ አንድ የተቀደሰ ጥሪ ሊመለከቱት እንደሚገባ አሳስበው፥ በእርግጥም፣ ወጣቶችን ወንጌል በማስተማር ረገድ የጋራ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ክርስቶስን ማቅረብ
ህብረተሰቡ በፍጥነት እየተለወጠ ባለበት በዚህ ወቅት በዓመፅ ወይም በምርታማነት ላይ ሳይሆን፣ ወጣቶች በክርስቶስ ሙሉ ሰው ሆነው እንዲያድጉ ልባቸውን በማስተማር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ ያቀረቡት ጳጳሱ፥ የእሳቸው ሀሳብ ዋና ይዘት በክርስቲያናዊ የሕይወት ራዕይ ላይ የተመሰረተ ግልጽ እምነት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት ነው” ያሉት ብፁዕ አቡነ ፈርናንዴዝ፤ “እኛ እርሱን ልናስገድድ ባንችልም፤ ነገር ግን ክርስቶስን እና እርሱ የሚያመጣቸውን አዳዲስ ነገሮች ሁሉ ማቅረብ ይገባናል” ያሉ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የ"ኮሙኒዮን ኤንድ ሊበሬሽን" ሃሳብ መስራች የሆኑትን ሞንሲኞር ሉዊጂ ጁሳኒ ያስተዋወቁት ዘዴ፣ በአሁኑ ወቅት በተለየ ሁኔታ ውጤታማ እንደሆነ አቅርበው፥ የሕይወት ችግሮች መፍትሔ የሚገኘው ትናንት፣ ዛሬ እና ለዘላለም ህያው በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ነው” በማለት ደምድመዋል።