ፈልግ

የነፍስ አድን ሰራተኞች በኢንዶኔዥያ፣ በምሥራቅ ኑሳ ቴንጋራ ክልል፣ ማውሜሬ ከተማ የደረሰውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ የፈረሰ ሕንፃን ሲቃኙ የነፍስ አድን ሰራተኞች በኢንዶኔዥያ፣ በምሥራቅ ኑሳ ቴንጋራ ክልል፣ ማውሜሬ ከተማ የደረሰውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ የፈረሰ ሕንፃን ሲቃኙ 

ካሪታስ ኢንዶኔዥያ በፍሎሬስ ደሴት ለደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ምላሽ ለመስጠት እንቅስቃሴ መጀመሩ ተነገረ

በኢንዶኔዥያ ፍሎሬስ ደሴት አቅራቢያ ቅዳሜ ነሐሴ 9 ቀን 2018 ዓ.ም. በሬክተር ስኬል 7.7 ማግኒቲዩድ የሆነ እጅግ ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ተከትሎ፥ የካቶሊክ የእርዳታ ኤጀንሲ የሆነው ካሪታስ ኢንዶኔዥያ በአደጋው የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት በመላ ሃገሪቱ የእርዳታ ግብዓቶችን ማሰባሰብ መጀመሩ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በኢንዶኔዥያ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት ቢያንስ 53 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፥ ከ135 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገልጿል።

የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ (USGS) እንዳስታወቀው ቅዳሜ ዕለት የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በምስራቅ ኑሳ ቴንጋራ ግዛት ከምትገኘው ኤንዴ ከተማ በስተሰሜን ምዕራብ 68 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ በዚህ አደጋ የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የተራድዖ ተቋም የሆነው ካሪታስ ኢንዶኔዥያ በሃገሪቱ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሀገረ ስብከቶች ውስጥ የሚገኙ የሰብዓዊ እርዳታ ትስስሮችን የማስተባበር ሥራዎችን መጀመሩ ተነግሯል።

የምስራቅ ኑሳ ቴንጋራ ፖሊስ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን እና ህንፃዎችን ማፍረሱን ገልፆ፥ በከተሞች እና በገጠራማ አካባቢዎች የተከሰተው የመብራት መቋረጥ የመረጃ ፍሰቱን ማስተጓጎሉን፣ እንዲሁም የፍለጋ እና አደጋ ማዳን ሥራውን አስቸጋሪ ማድረጉን ገልጿል።

ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኤጀንሲ (BNPB) በናጌኬኦ መንደር የሚኖሩ ወደ 2,000 የሚጠጉ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን፣ 38 ሰዎች መሞታቸው እና በተለያዩ መኖሪያ ቤቶች፣ መጋዘኖች እና የመንግስት ተቋማት ላይ ውድመት መድረሱን ያስታወቀ ሲሆን፥ የኢንዶኔዥያ ሜትሮሎጂ፣ ክሊማቶሎጂ እና ጂኦፊዚክስ ኤጀንሲ (BMKG) በበኩሉ በሱናሚ ስጋት ምክንያት ነዋሪዎች ከባህር ዳርቻዎች እና ከወንዞች አቅራቢያ እንዲርቁ እና ወደ ከፍተኛ ቦታዎች እንዲሸሹ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ማስጠንቀቂያው መነሳቱ እና ስለጉዳቶቹ፣ ስለተፈናቀሉ ሰዎች እና ስለተጎዱ ቤቶች ይፋዊ እና የተጠናከረ መረጃ ለማግኘት አሁንም እየተጣራ መሆኑ ተነግሯል።

ካሪታስ የቤተክርስቲያን የተራድዖ ተቋማትን እያስተባበረ ይገኛል 
ይሄንን ተከትሎ ካሪታስ ኢንዶኔዥያ በመላው ቤተክርስቲያን የሚከናወን የአደጋ ጊዜ ምላሽ እርምጃዎችን ያስጀመረ ሲሆን፥ ከሩቴንግ፣ ላቡዋን ባጆ፣ ኩፓንግ፣ ማውሜሬ እና ኤንዴ ሀገረ ስብከት ጋር በመተባበር ስለአደጋው ሁኔታ ለመከታተል እና በየአካባቢያቸው ያለውን ተጽእኖ ለመገምገም ጥረት እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

ካሪታስ ኢንዶኔዥያ በኢንዶኔዥያ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሰብዓዊ ሥራዎች ኃላፊነት ሥር በሚገኘው በምስራቅ ኑሳ ቴንጋራ ለተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን የተናገሩት የካሪታስ ኢንዶኔዥያ ዋና ዳይሬክተር አባ ፍሬዲ ራንቴ ታሩክ፥ ካሪታስ ኢንዶኔዥያ ፈጣን ምላሽ መስጠት መቻሉን ለማረጋገጥ ከሀገረ ስብከት ካሪታስ ቡድኖች እና ከማህበራዊ ልማት ኮሚሽን ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

አደጋው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በመሬት መንቀጥቀጡ ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ መስጠትን እና ከቦታው የማስወጣት ጥረቶችን መደገፍን ጨምሮ በእያንዳንዱ ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙ በጎ ፈቃደኞችን እና የካሪታስ ቡድኖችን የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ የድጋፍ ሥራው የሚከናወነው “አንድ ቤተክርስቲያን፣ አንድ ምላሽ” በሚለው መርህ መሰረት መሆኑን እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የተለያዩ ክፍሎችን በወንድማማችነት እና በአንድነት መንፈስ በጋራ ለመስራት አንድ ላይ በማሰባሰብ መሆኑን ገልጸዋል።

አባ ፍሬዲ አክለውም ካሪታስ ኢንዶኔዢያ ለሰብአዊ ቀውሱ በፍጥነትና በብቃት ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል፣ የቤተክርስቲያኒቱን ክፍሎች በሙሉ በጋራ እንዲሰሩ፣ የተቀናጀ አቅም እንዲፈጥሩ እና እርስ በርስ እንዲደጋገፉ እያስተባበረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቁምስናዎች በትብብር እየሰሩ ነው
በተጎዱት ሀገረ ስብከቶች ውስጥ የሚገኙ የአካባቢው አብያተ ክርስቲያናት በብፁዓን ጳጳሶቻቸው ድጋፍ፣ በአደጋ ጊዜ ምላሽ ውስጥ ንቁ ሚና እንዲጫወቱ የተበረታቱ ሲሆን፥ ካሪታስ ሁኔታውን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ጉዳዩን በሀገረ ስብከት ደረጃ ሪፖርት ከማድረጋቸው በፊት በአካባቢያቸው በመቀናጀት በአደጋው ስለደረሰው ጉዳት መረጃ እንዲሰበስቡ መጠየቃቸው ተገልጿል።

ለአብነትም፣ ካሪታስ ሩቴንግ በአካባቢው ከሚገኘው ክልላዊ አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ የነበሩ ታካሚዎችን አስቀድሞ ማስወጣቱን እንዲሁም ከዋናው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በኋላ ሊከሰቱ ከሚችሉ ተከታይ ጉዳቶች እና በሆስፒታሉ ህንጻዎች ላይ ሊደርስ ከሚችለው ጉዳት ለመከላከል፣ ለታካሚዎች የአደጋ ጊዜ ድንኳኖችን ማዘጋጀቱ ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ካሪታስ ኢንዶኔዥያ የካሪና የአደጋ ጊዜ ምላሽ ትስስሩ ማህበራዊ መገናኛ የሆነውን የዋትስአፕ ቡድኑን በማስተባበር በካሪታስ ኔትወርክ መካከል የመረጃ መጋራት እና የአደጋ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል አድርጎ ማንቀሳቀሱ ተነግሯል።

ካሪታስ ኢንዶኔዥያ በምስራቃዊ ቴንጋራ ውስጥ ከሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ጋር በመተባበር የአደጋ ጊዜ ምላሹን በሀገር አቀፉ የካሪታስ ኢንዶኔዥያ ትስስር አማካኝነት ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑ እንዲሁም ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ የአብሮነት ፈንድን እና የአደጋ ጊዜ ድጋፍ ሰጪ ቡድኖችን ማንቀሳቀሱ ተገልጿል።

አስቸኳይ ፍላጎቶች
በካሪታስ ትስስር የተደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ግምገማ ከአደጋ ቀጠና የማስወጣትና የደህንነት ድጋፍ፣ ንጹህ ውሃ፣ ለመመገብ ዝግጁ የሆነ ምግብ፣ መጠለያና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ የጤና አገልግሎቶች፣ ብሎም ህጻናት፣ አረጋውያን፣ ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና መደበኛ መድሃኒት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ለመሳሰሉ ተጋላጭ ቡድኖች የሚደረግ ድጋፍን ጨምሮ በርካታ አስቸኳይ ፍላጎቶች መኖራቸውን ይፋ አድርጓል።

ካሪታስ በተለይም የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው በቀጠለበት እና የተሳሳተ መረጃ ለተጎዱ ማህበረሰቦች ተጨማሪ አደጋዎችን ሊፈጥር እንደሚችል በሚታወቅበት በአሁኑ ወቅት እስከ ቁምስናዎች ደረጃ ድረስ የሚዘልቅ አስተማማኝ መረጃ እና ቅንጅት አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት የሰጠ ሲሆን፥ አባ ፍሬዲ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት የቤተክርስቲያኗ ምላሽ እንደ ተቋም በካሪታስ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ መላውን የቤተክርስቲያን ማህበረሰብ የሚያካትት መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

ይህ በመሆኑም ምክንያት “አንድ ቤተክርስቲያን፣ አንድ ምላሽ” የሚለው መርህ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለሰብዓዊ ቀውሶች የምትሰጠውን ምላሽ የሚመራ መንፈስ እየሆነ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህም አግባብ ሀገረ ስብከቶች፣ ቁምስናዎች፣ የካሪታስ ቡድኖች፣ በጎ ፈቃደኞች እና ሌሎች የቤተክርስቲያኒቱ ክፍሎች እርዳታ በተቻለ ፍጥነት ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዲደርስ በጋራ እየሰሩ መሆኑ ተገልጿል።

የአከባቢው ሁኔታዎች ተለዋዋጭ ሆነው በቀጠሉበት እንዲሁም ከመንግስት አካላት እና ከካሪታስ ትስስሮች ፈጣን የሆኑ ግምገማዎች ብሎም ኦፊሴላዊ መረጃዎች በሚወጡበት በአሁኑ ወቅት ካሪታስ ኢንዶኔዥያ ትክክለኛ የሆኑ መረጃዎችን በጊዜ ማቅረቡን ይቀጥላል ተብሏል።

17 Aug 2026, 14:44