ፈልግ

በታይቤ የሚገኘው የባይዛንታይን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በታይቤ የሚገኘው የባይዛንታይን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን  (AFP or licensors)

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ታይቤህን በጎበኙበት ወቅት በአከባቢው የክርስቲያኖች መገኘት ጥበቃ እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በፍልስጤም ግዛት ውስጥ የምትገኘውን የመጨረሻዋን የክርስቲያኖች መንደር የሆነችውን ታይቤህ መንደርን የጎበኙ ሲሆን፥ መንደሯ ከፍተኛ የመንቀሳቀስ እና የመግባት-መውጣት ጥብቅ ገደቦች ባጋጠሟት በዚህ ወቅት ጉብኝት ያደረጉት ካርዲናሉ “በዚህ እጅግ ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ የክርስቲያኖች ድምፅ ሆነን እንድንቀጥል የእናንተ አርአያነት ወሳኝ ነው” በማለት ለህዝቡ ንግግር አድርገዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የታይቤህ መንደር በፍልስጤም ግዛት ዌስት ባንክ ክልል ውስጥ የምትገኝና ሙሉ በሙሉ ክርስቲያኖች ብቻ የሚኖርባት የመጨረሻዋ የክርስቲያን መንደር በመሆን የምትታወቅ ታሪካዊ ቦታ ስትሆን፥ ይህች መንደር ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኝ እና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ የክርስትና ታሪክ እና ቅርስ ባለቤት እንደሆነች የሚታወቅ ቢሆንም፥ በአሁኑ ወቅት የአከባቢው ማህበረሰብ ስልታዊ ማስፈራራት፣ የንብረት መውረስ እና አዲስ ሠፈራን እየተጋፈጠ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ይሄንን ተከትሎ የታይቤህ መንደርን የጎበኙት በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትሪያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ “እዚህም ሆነ በመላው ቅድስት ሀገር፣ በሁሉም ደረጃ የቤተክርስቲያን መገኘትን ለመጠበቅ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋችንን እንቀጥላለን” ያሉ ሲሆን፥ በቅድስት ድንግል ማርያም ፍልሰታ በዓል ወቅት በዌስት ባንክ ግዛት ውስጥ የምትገኘውን ይህቺን አነስተኛ የክርስቲያኖች መንደር በመጎብኘት ከታይቤህ ሕዝብ ጋር ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል።

“በሰብዓዊ ወይም በዓለማዊ ደረጃ መልሶች ላይገኙ ይችላሉ” ያሉት ካርዲናሉ፥ “ነገር ግን በእግዚአብሔር ስለምናምን፣ በእርሱም አማካኝነት ታይቤህ ውስጥ ሕይወትን ማስቀጠል እንደምንችል እርግጠኛ ነኝ” ሲሉ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በታይቤ በሚገኘው የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ክርስቶስ ቤዛ ቤተክርስቲያን ውስጥ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ተናግረዋል።

“በሕዝባቸው ዘንድ” የተደረገላቸው አቀባበል

መስዋዕተ ቅዳሴው ከመጀመሩ ቀደም ብሎ የታይቤህ ህዝብ ለፓትርያርኩ ደማቅ አቀባበል ያደረገ ሲሆን፥ የታይቤህ ቁምስና ካህን የሆኑት አባ ባሻር ፋዋድሌህ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት የመንደሩ ነዋሪ በገዛ ወገኖቻቸው መካከል በደማቅ ሁኔታ ፓትሪያርኩን እንደተቀበላቸው ገልጸዋል።

 

ከኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት በተሰጠው መግለጫ መሠረት አባ ባሻር የካርዲናሉን መገኘት አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት ከልጆቹ ጎን እንደሚቆም አባት አድርገው የገለጹ ሲሆን፥ የብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በመንደሩ መገኘት ማህበረሰቡ ብቻውን እንዳልሆነ እና ቤተክርስቲያን "የዚህን ምድር መስቀል እና ተስፋ" በመሸከም ከልጆቿ ጎን እንደምትቆም እንዳስታወሳቸው አክለው ተናግረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በበኩላቸው የቅድስት ድንግል ማርያም የፍልሰታ በዓልን "የትንሣኤ ፍሬ" ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ ድንግል ማርያም ክርስቲያኖች እውነታውን በሰው ልጅ ስሌት ሳይሆን "በመለኮታዊ ዓይን" እንዲመለከቱ እንደምታስተምር ገልጸው፥ በመቀጠልም ይህንን መልዕክት በቀጥታ ከታይቤህ ጋር በማያያዝ፣ ሁኔታዎች የወደፊቱን ጊዜ አስቸጋሪ ወይም የማይቻል አድርገው በሚያሳዩበት ጊዜም እንኳን ቢሆን ሕዝቡ በእምነት እና በተስፋ ጸንቶ እንዲኖር አበረታተዋል።

ልብን ከፍርሃት መጠበቅ
ፓትርያርኩ አክለውም፣ ክርስቲያናዊ መገኘትን ለማስቀጠል ልብን ከፍርሃት፣ ከተስፋ መቁረጥ እና ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ተጽዕኖ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥተው የገለጹ ሲሆን፥ "ነገር ግን መብቶቻችንን፣ በተለይም የመኖር መብታችንን ሳንተው፣ ሕይወትን የሚያፈልቅ ማህበረሰብ ሆነን መቀጠል እንፈልጋለን" በማለት ህዝቡ የጸና እና ደፋር እንዲሆን መክረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ አክለውም ከአባ ባሻር በሚደርሷቸው መደበኛ መልዕክቶችና ወቅታዊ መረጃዎች አማካኝነት በታይቤህ እየተከናወኑ ያሉትን ሁኔታዎች በቅርበት እየተከታተሉ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፥ የአሁኑ የፓትርያርኩ ጉብኝት የተካሄደው፣ ባለፈው ሐምሌ ወር እስራኤል የታይቤህ እና የሪሞን አካባቢን “የተከለከለ ወታደራዊ ቀጠና” በማለት ማወጇን ተከትሎ፣ እስራኤላውያን እና የውጭ ሀገር ዜጎች ወደዚያ ክልል እንዳይገቡ ወይም እንዳይቆዩ ያገደችበትን ሁኔታ ተከትሎ እንደሆነ ተነግሯል።

ቀጣይነት ያለው ክርስቲያናዊ መገኘት አስፈላጊነት
“የተከለከለ ወታደራዊ ቀጠና” ተብሎ የተሰየመው አካባቢ የታይቤህን የመኖሪያ እና የግንባታ ቦታዎች፣ የግብርና መሬቶችን እንዲሁም ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ስፍራዎችን የሚያካትት ሲሆን፥ ትዕዛዙ ለሃይማኖታዊ ጉዞ አድራጊዎች፣ ጎብኚዎች፣ ጋዜጠኞች፣ በጎ ፈቃደኞች እና ሌሎች የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ታይቤህ መግባት መቻልን በተመለከተ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ ተመላክቷል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ፣ በታይቤህ እየተከናወነ ያለው ነገር ከከተማዋ አልፎ በሰፊው እየታወቀ መምጣቱን ገልጸው፥ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፓትርያርኩ፣ “በዚህ እጅግ ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ ክርስቲያናዊ ድምፅ ሆነን መቀጠል እንድንችል የእናንተ አርአያነት ወሳኝ ነው" ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

18 Aug 2026, 14:38