ሊቀ ጳጳስ ንዋቹኩ ለወንጌል አገልግሎት የሚውል የዲጂታል መድረክ መበረታታት አለበት ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ሊቀ ጳጳስ ፎርቹናተስ ንዋቹኩ “ዲጂታል መገናኛዎች ለባሕሎች መግባባት እና ለአካባቢ ደህንነት” በሚል ርዕሥ በተካሄደው የዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ባለሙያዎች ማህበር የ 2026 ዓ.ም. ጉባኤ የመጀመሪያው ክፍል ስብሰባ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር ሰብዓዊነት መንታ መንገድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፥ የመጀመሪያው ምርጫ ግራ መጋባት፣ ራስን ብቻ ማዕከል ማድረግ እና ጫጫታ በሚታይበት ዓለም ውስጥ መቆየት ወይም እግዚአብሔርና የሰው ልጅ በአንድነትና በኅብረት ሊኖሩባት የሚችሉትን የአንዲት ከተማ ቅጥሮች በጋራ እንደገና መገንባት መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህ ፈተና ምላሽ ለመስጠት የፍቅር ስልጣኔን መገንባት እንደሚገባ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ያቀረቡትን ጥሪ በማስተጋባት፥ ይህ ስልጣኔ ካሜራዎችን፣ ማይክሮፎኖችን እና ላፕቶፖችን የያዙ ደቀ መዛሙርት “እግር በእግር” ሊያከናውኑት የሚችሉት ተግባር መሆኑን ገልጸው፥ ይሄንንም የሚያከናውኑት ተጽዕኖ ፈጣሪ ከመሆን በፊት ደቀ መዝሙርነት መቅደም እንዳለበት የሚያምኑ ወንዶች እና ሴቶች ናቸው ብለዋል።
ስለ ክርስቲያን የመገናኛ ባለሙያዎች ማንነት እና ተልዕኮ ላይ በተነሳው በዚህ ሃሳብ ላይ በመመስረት ሊቀ ጳጳሱ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ውይይት፥ በመገናኛ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ጥሪ እና ሚናን በተመለከተ ተጨማሪ ግንዛቤን ሰጥተዋል።
የመገናኛ ባለሙያዎች በአዲሱ የወንጌል ስርጭት መስኮች ውስጥ ያሉ ሐዋርያት መሆናቸው
የወንጌል ስርጭት ተልዕኮን በሚያከናውኑ የመገናኛ ባለሙያዎች ዘንድ ሊኖሩ ስለሚገቡ በጎ ባህሪያት የተጠየቁት ሊቀ ጳጳስ ንዋቹኩ፣ የመዳን መንገድ የሚሆን የመግባቢያ ዓይነትን እንዲለማመዱ፣ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ፍቅር ለማስተላለፍ እና የኢየሱስ ክርስቶስን መገኘት ለማወጅ የሚያስችል የመገናኛ ዘዴን እንዲለማመዱ ተጠርተዋል ብለዋል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጉ” በማለት ያዘዘውን ትእዛዝ በማስታወስ፣ ይህ በተነገረበት ወቅት ህዝቡ በዋናነት እንደ አካላዊ ቦታዎች ተደርገው ይታዩ እንደነበር ጠቅሰው፥ ሆኖም ግን፣ በአሁኑ ወቅር ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ፣ ዩቲዩብ እና ሌሎች ዲጂታል መድረኮችን ጨምሮ ሰዎች የሚገናኙባቸው፣ የሚወያዩባቸው እና ማህበረሰቦችን የሚገነቡባቸው አዳዲስ መድረኮች ብቅ ማለታቸውን የገለጹ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት የወንጌሉ ቃል በአካላዊ ቦታዎች ብቻ ተወስነው እንዲቀሩ ሳይሆን ይልቁንም ወደ ዲጂታሉ ዓለም መድረስ እንዳለበት አሳስበዋል።
ከዚህም ባሻገር ይህንን ሙያ ሙሉ ግንዛቤ በተሞላበት ሁኔታ የመቀበልን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፥ ጽሑፍ፣ ምስል ወይም የኦዲዮ-ቪዥዋል ውጤትን ጨምሮ ዬትኛውም ዓይነት ይዘት ታትሞ ሲወጣ ከሌላው የመረጃ ማስተላለፊያ መንገድ የተሻለ ስለሚሆን ዘመኑን የሚመጥን መንገድ መከተል መልካም እንደሆነ አሳስበዋል።
በዚህም ምክንያት የዲጂታሉ ዓለም ህብረትንና ተስፋን ማጎልበት፣ የግንኙነት ድልድዮችን መገንባት፣ የእርስ በርስ ግንኙነትን ማበረታታት እንዲሁም የወንጌል መልዕክት የሰዎችን ልብ መያዝ የሚችልባቸውን አዳዲስ መንገዶች መክፈት አለበት ብለዋል።
የመገናኛ ባለሙያ ከመሆን በፊት ጠንካራ ማንነት ያስፈልጋል
ለመጪው ዘመን የመገናኛ ባለሙያዎች የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ የተጠየቁት የቅድስት መንበር የወንጌል ስርጭት ጽህፈት ቤት አስተባባሪው በዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ባለሙያዎች ማህበር የ 2026 ዓ.ም. ጉባኤ ወቅት ያካፈሏቸውን አንዳንድ አስተያየቶች በማስታወስ፥ በተለይ ለወጣት የሚዲያ ባለሙያዎች ባስተላለፉት ቀላል ግን መሠረታዊ መልዕክት “የመገናኛ መድረካቸውን ከመገንባታቸው በፊት አእምሮአቸውን በሚገባ መገንባት ወይም ማበልጸግ” እንዳለባቸው መክረው፥ በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ ተጽዕኖ ከመፍጠር በፊት የውስጥ ዝግጅት፣ ሰብዓዊ ምስረታ እና መንፈሳዊ ብስለት መምጣት እንዳለባቸው አብራርተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የመገናኛ ባለሙያዎች እያንዳንዱ የዲጂታል ጉዞ የጎሰኝነት፣ የጽንፈኝነት ወይም የመከፋፈል መንገድ ሳይሆን የግንኙነት መንገድ እንዲሆን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ያበረታቱ ሲሆን፥ በዚህ አውድ ውስጥ ለጋራ ቤታችን መስጠት የሚገባንን እንክብካቤ በትረካዎቻቸው ውስጥ ማዋሃድ አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት በመስጠት፥ “ስለፍጥረት እንክብካቤ የሚናገሩ ታሪኮች እጅግ አስፈላጊ ናቸው” በማለት አስታውሰዋል።
ሊቀ ጳጳስ ንዋቹኩ በመጨረሻም የመገናኛ ባለሙያዎች ተልዕኮ በጥልቅ ማንነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን በማስታወስ፥ ዋና ተዋናዮች ከመሆን በፊት ደቀ መዛሙርት መሆን፤ የልዩነት አቀንቃኞች ከመሆን ይልቅ የግንኙነት ድልድይ ገንቢዎች መሆን እንደሚገባ፣ እንዲሁም በዛሬው ጊዜ ባሉ አዳዲስ የዲጂታል መድረኮችም ጭምር እግዚአብሔርን ማግኘት በሚያስፈልግበት ዓለም ውስጥ የወንጌል ተስፋ ምስክሮች መሆን እንደሚገባ በመምከር አጠቃለዋል።