አቡነ ኮሎምቦ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የአርጀንቲና ጉብኝት የሰላም መልዕክት ያመጣል ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የአርጀንቲና ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት እና የሜንዶዛ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማርቼሎ ዳንኤል ኮሎምቦ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ቅዱስነታቸውን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር እና የምስራቹ ቃል አብሳሪ አድርገን በአገራችን ለመቀበል እጅግ ደስተኞች ነን፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሲመጡ የተስፋ መልዕክት እና የወንጌል ደስታ እንደሚያመጡልን እናውቃለን” ሲሉ ገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማርቼሎ ኮሎምቦ ይህን ለዜና አገልግሎቱ የተናገሩት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከጥቅምት 27 እስከ ኅዳር 8/2019 ዓ. ም. ድረስ በሦስት የደቡብ አሜሪካ አገራት ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የቅድስት መንበር መግለጫ ሐምሌ 29/2018 ዓ. ም. ካሳወቀ በኋላ ነው።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከጥቅምት 29 እስከ ኅዳር 2/2019 ዓ. ም. በአርጀንቲና ቦይነስ አይረስን፣ ኮርዶባን እና ሉያን የሚጎበኙ ሲሆን በስድስተኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር መሠረት አርጀንቲና ከኡራጓይ ቀጥላ ሁለተኛዋ የጉብኝት አገር ትሆናለች።
ጠንካራ ሐዋርያዊ ትኩረት የተደረገባቸው ዝግጅቶች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የላቲን አሜሪካ አገራትን እንደሚጎበኙ ከተረጋገጠ በኋላ ዝግጅቶች መጀመራቸውን የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኮሎምቦ፥ የጉብኝቱን ተግባራዊ አወቃቀር የሚከታተሉ፣ የቅዱስነታቸውን የቅርብ ጊዜ ጉብኝቶች የሚያጠኑ እና በማስተባበር ሥራ የተሳተፉ የቤተ ክርስቲያን ባለስልጣናትን የሚያማክሩ ቡድኖች መቋቋማቸውን ተናግረው፥ “የዚህ ሂደት አካል የሆኑ የቅርብ ጊዜ ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ተሞክሮዎችን በማጥናት እና በማስተባበር የተሳተፉ የቤተ ክርስቲያን ባለስልጣናትን አማክረናል” ሲሉ ተናግረዋል።
የአርጀንቲና ቤተ ክርስቲያን ብዝሃነት እና ሕያውነት
ከሎጂስቲክ ዝግጅቶች በተጨማሪ ለዝግጅቶቹ ጠንካራ ሐዋርያዊ ትኩረት አፅንዖት የሰጡት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኮሎምቦ፥ “አስፈላጊ ብለን የምናስበው ቅዱስነታቸውን የምትቀበል ቤተ ክርስቲያን ሕያውነት፣ የዚያች ቤተ ክርስቲያን ሕይወትን የሚወክሉት ብጹዓን ጳጳሳት እንደሆኑ እና በዚህም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝት በአርጀንቲና ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ ማዕከላዊ የውይይት ርዕሥ እንደ ነበር አስረድተዋል።
ብጹዓን ጳጳሳቱ አገሪቱ በሀገረ ስብከቶች እና በአውራጃዎች ውስጥ ካሉት ልዩ ልዩ እውነታዎች ባሻገር አስተያየታቸውን እና ግምታቸውን ያካፈሉት ሲሆን፥ ይህም ጉብኝታቸው በአርጀንቲና ውስጥ የቤተ ክርስቲያኗን ብዝሃነት እና ሕያውነት የሚያንፀባርቅ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሆነ ታውቋል።
የሰላም አብሳሪ መሆን
የአርጀንቲና ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የሜንዶዛ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማርቼሎ ኮሎምቦ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በመልካም እረኝነታቸው በሚናገሯቸው ቃላት እና በሚያሳዩአቸው ምልክቶች አገልግሎታቸውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ከቤተ ክርስቲያኗ እና ከምእመናን ጋር አብረው መጓዛቸውን ተናግረዋል።
“አሁን በአርጀንቲና የወንጌላዊነት ጉብኝት በማድረግ እና ጠንካራ የሰላም መልዕክት፣ ለሰው ልጅ ክብር ቁርጠኛ እና ቀጣይነት ያለውን የቤተ ክርስቲያን ተሃድሶ ሲያዳርሱ በሕዝቦቻችን መካከል እናገኛቸዋራለን” ብለው፥ “ሲኖዶሳዊነት እና ተልዕኮ በቅርበት የተሳሰሩ የቅዱስነታቸው መልዕክቶች እና ሃሳቦች ተደጋጋሚ ጭብጦች ናቸው” ሲሉ አክለዋል።
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ብዙ ጊዜ በሚጸልዩበት በሉያን የሚዘጋጅ በዓል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አርጀንቲናን ከመልቀቃቸው በፊት ወደ ሉያን በመጓድ የአገሪቱ ባልደረባ በሆነች በሉያን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ውስጥ ጸሎት የሚያቀርቡ ሲሆን፥ “በዓሉ የደስታ ምንጭ እና የሁሉም አርጀንቲናውያን ደጋፊ የሆነች እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ለማግኘት ዕድል ይሰጣል” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኮሎምቦ ተናግረዋል።
“ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ከክኅነት እስከ ካርዲናልነት ማዕረግ ድረስ ብዙውን ጊዜ እንዲሁም በአንድ ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን እንደተቀበልን ሁሉ በአንድነት እና በእግዚአብሔር ልጆች መንፈስ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ሐዋርያዊ ጉብኝት ማየት ውብ እና በእውነት አስደናቂ አጋጣሚ ይሆናል” ሲሉ የአርጀንቲና ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት እና የሜንዶዛ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቼሎ ኮሎምቦ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር የነበራቸውን ቆይታ አጠቃልለዋል።