ፈልግ

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት (SECAM) ፕሬዝዳንት የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት (SECAM) ፕሬዝዳንት የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ  

በመላው አፍሪካ አድማጭ የሆነች ቤተክርስቲያንን ለመገንባት ጥሪ መደረጉ ተነገረ

ከመላው አፍሪካ፣ ከማዳጋስካር እና ከአካባቢው ደሴቶች የተውጣጡ ሰባት የክልል ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎችን የሚወክሉ ከ50 በላይ ልዑካን የተሳተፉበት እና እ.አ.አ. በ 2028 ዓ.ም. በሮም ለሚደረገው አጠቃላይ የቤተክርስቲያን ጉባኤ የተዘጋጀው የመጀመሪያ የዝግጅት ጉባኤ ረቡዕ ሃምሌ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ልዑካኑ በዚህ ጉባኤ በመላው አህጉሪቱ ይበልጥ ሲኖዶሳዊ እና ሚስዮናዊ የሆነች ቤተክርስቲያንን ለማጎልበት ያላቸውን ቁርጠኝነት ማደሳቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“በአፍሪካ የምትገኘው ሲኖዶሳዊት ቤተክርስቲያን፡ እ.አ.አ. በ2028 ዓ.ም. ወደሚካሄደው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ የአብሮነት ጉዞ” በሚል መሪ ሃሳብ ሃምሌ 28 እና 29 በአዲስ አበባ የተካሄደው ይህ ሴሚናር፣ እ.አ.አ. ጥቅምት ወር 2028 ዓ.ም. በሮም ለሚካሄደው የቤተክርስቲያን ጉባኤ የአፍሪካን ዝግጅት የአህጉራዊ ምዕራፍ በይፋ ያስጀመረ እንደነበር ተገልጿል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኪንሻሳ ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት (SECAM) ፕሬዝዳንት የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ በጉባኤው የመዝጊያ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ‘በጉባኤው የሁለት ቀናት ቆይታ ወቅት ለነበሩት የጸሎት፣ የማዳመጥ፣ የውይይት እና የማስተዋል’ ጊዜያት እግዚአብሔርን ያመሰገኑ ሲሆን፥ በዚህ ጉባኤ የሥራ ሂደቶች ብቻ የተገመገሙበት ሳይሆን በአፍሪካ ቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የመንፈስ ቅዱስን ሥራ የተስተዋለበት አጋጣሚ እንደነበር ገልጸው፥ “መንፈስ ቅዱስ ይበልጥ ሲኖዶሳዊ እና ሚስዮናዊ እንድንሆን እንዴት እየጠራን እንደሆነ በጋራ ለመለየት ሞክረናል” ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የብፁዓ ጳጳሳት ጉባኤ እና የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ላደረጉት ጉልህ ሚና ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር አህጉራዊ እና ክልላዊ የሲኖዶስ ቡድኖች፣ ጽሁፍ አቅራቢዎች እና ተሳታፊዎች ለነበራቸው ቁርጠኝነት እና ጠቃሚ አስተዋጽዖ ከፍ ያለ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ ውይይቱን አስመልክተው እንደተናገሩት የጉባኤ ተሳታፊዎች በመላው አህጉሪቱ የሚታዩትን አበረታች የተስፋ ምልክቶችን ለይተው እንዳወቁ እና በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የቤተክርስቲያኒቱን ጉዞ የሚመሩ የአፍሪካ ሲኖዶስ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች እንዳስተዋሉ የጠቀሱ ሲሆን፥ እነዚህን ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች የጋራ የማስተዋል ሂደት ፍሬ እንደሆኑ ገልፀው፥ በአካባቢው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ማዳመጥን፣ ውይይትን እና ሚስዮናዊ ተሃድሶን ለማጠናከር "የጋራ አድማስ" ይሰጣል ብለዋል።

የሴካሙ ፕሬዝዳንት በማከልም እ.አ.አ. ከ 2027 ዓ.ም. ጀምሮ የአህጉራዊ ሲኖዶስ ሂደቱን የሚመራውን ፍኖተ ካርታ የዘረዘሩ ሲሆን፥ በአፍሪካ የምትገኘው ቤተክርስቲያን በሀገረ ስብከት እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚካሄዱ የግምገማ ጉባኤዎች ወደ አህጉራዊው የሲኖዶስ ጉባኤ በመሸጋገር፣ በመጨረሻም እ.አ.አ. ጥቅምት 2028 ዓ.ም. በሮም በሚካሄደው የቤተክርስቲያን ጉባኤ የሚጠናቀቅ የሂደት ደረጃ የሆኑ አራት ተከታታይ ደረጃዎች ማለትም የግንዛቤ፣ የትርጓሜ፣ የአቅጣጫ እና የአከባበር ወቅቶችን እንደምታሳልፍ ጠቁመዋል።

ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ ሴሚናሩ ስብሰባ ብቻ ሳይሆን የክልል ቡድኖችን ለሚጠብቃቸው ቀጣይ ሥራ ለማዘጋጀት የታሰበ የአቅም ግንባታ ሂደት መሆኑን ለተሳታፊዎቹ አስታውሰው፥ እነዚህ ክልላዊ ቡድኖች ወደየሃገሮቻቸው ሲመለሱ ብሔራዊ የሲኖዳል ቡድኖችን እንዲያቋቁሙ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ ብሔራዊ ቡድኖቹም በተራቸው የሀገረ ስብከት ሲኖዶሳዊ ቡድኖችን እንደሚመሰርቱ እና በዚህ መንገድ፣ እነዚህን ጉባኤዎች በየደረጃው ለማክበር በሚገባ እንዘጋጃለን ብለዋል።

ልዑካኑ የአካባቢያቸው አብያተ ክርስቲያናት የመንፈስ ቅዱስን ተግባር ለይተው ማስተዋል እንዲችሉ መርዳት እንደሚገባቸው እንዲሁም የአፍሪካ ስጦታዎች እና ልምዶች በሲኖዶሳዊ ሂደት አማካኝነት ሁለንተናዊቷን ቤተክርስቲያን እንዲያበለጽጉ ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ያሳሰቡት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ መንፈስ ቅዱስ የሚያሳየንን መንገድ ለመከተል የሚያስችል ድፍረት፥ እንዲሁም በኅብረት፣ በተሳትፎ እና በተልዕኮ አብሮ የመጓዝ ልግስና እንዲኖረን መጸለይ አለብን ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ ሴሚናሩን በይፋ ከመዝጋታቸው በፊት፣ የአህጉሪቱን የሲኖዶሳዊ ጉዞ የቤተክርስቲያኒቱ እናት የሆነችው የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲያገኘው በመጸለይ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ እ.አ.አ. በ 2028 ዓ.ም. ለሚካሄደው የቤተክርስቲያን ጉባኤ እየተዘጋጁ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ቅድስት ድንግል ማሪያም አብራ እንድትጓዝ ጸልየዋል።

በአዲስ አበባ የተደረገው ጉባኤ የሲኖዶሳዊ ጉዞ የአፈጻጸም ምዕራፍ አካል መሆኑ እና አፍሪካ በሮም ለሚካሄደው የ 2028ቱ ጉባኤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ላለው የቤተክርስቲያን የመለየትና የማስተዋል ሂደት ውስጥ የአፍሪካን አስተዋጽዖ በተመለከተ የተወሰደ የመጀመሪያውን አህጉራዊ እርምጃን እንደሚወክል ተገልጿል።

07 Aug 2026, 14:31