ፈልግ

የነሐሴ 17/2018 የ19ኛው መደበኛ ሳምንት ንባባትና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የነሐሴ 17/2018 የ19ኛው መደበኛ ሳምንት ንባባትና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የነሐሴ 17/2018 የ19ኛው መደበኛ ሳምንት ንባባትና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

"ቅዱስ ወንጌል ማዕበል ውስጥ በምንገባበት ወቅት በእግዚአብሔር እንድንታመን የመክረናል"

የእለቱ ንባባት

1.      1ኛ ነገሥት 19፡9.11-13

2.     መዝሙር 84

3.     ሮሜ 9፡1-5

4.    ማቴዎስ 14፡22-33

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ በባሕር ላይ እንደሔደ

ወዲያውም ሕዝቡን እስኪያሰናብት ድረስ ደቀመዛሙርቱ ወደ ጀልባ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያው ነበር። በዚህ ጊዜ ጀልባዋ ከምድር በጣም ርቃ ሳለች፥ ነፋስ በተቃራኒው አቅጣጫ ነበርና በማዕበል ትንገላታ ጀመር። ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ መጣ። ደቀመዛሙርቱ በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ “ምትሐት ነው” ብለው ደነገጡ፤ ከፍርሃትም የተነሣ ጮኹ። ወዲያው ኢየሱስ ተናገራቸው፥ “አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ፤” አላቸው።

ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! አንተስ ከሆንህ በውሃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” ሲል መለሰለት። እርሱም “ና” አለው። ጴጥሮስም ከጀልባዋ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ለመሄድ በውሃው ላይ ተራመደ። ነገር ግን የነፋሱን ብርታት አይቶ ፈራ፤ መስጠም በጀመረም ጊዜ “ጌታ ሆይ! አድነኝ” ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም ወዲያው እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ፥ ለምን ተጠራጠርህ?” አለው። ወደ ጀልባዋ በወጡ ጊዜ ነፋሱ ፀጥ አለ። በጀልባዋ የነበሩትም “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት (ማቴዎስ 14፡22-33)።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ

ኢየሱስ በባሕር ላይ መሄዱን በሚገልጸው በዛሬው እለት ቅዱስ ወንጌል ውስጥ በዋነኝነት አራት ዋና ዋና ጭብጦችን እናገኛለን።

በመጀመርያ ደረጃ መሻገር እና ፍርሃት፣ የምሉትን እናገኛለን። በሐይቁ መካከል ያለው ጀልባ የዕለት ተዕለት ሕይወትን ችግሮች እና አለመተማመን ይወክላል። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን በባህር ላይ ሲራመድ ሲያዩት ይፈራሉ እና ምትሐት መስሎዋቸው ይደነግጣሉ።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ "አይዞአችሁ፣ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!"፥ የምለው የሚያረጋጋን የኢየሱስ ድምፅ እናገኛለን።መገኘቱ አውሎ ነፋሱን አያስወግድም፣ ነገር ግን ለድንጋጤ ሳንሸነፍ እንድንጋፈጥ ጥንካሬ ይሰጠናል።

በሦስተኛ ደረጃ "የጴጥሮስ ተግባር" እናገኛለን፥ ጴጥሮስ ኢየሱስን በውሃ ላይ እንደ እርሱ እየተራመደ ወደ እርሱ እንዲሄድ ጠየቀው። መራመድ ጀመረ፣ ነገር ግን ተጠራጠረ፣ ዓይኑን ከክርስቶስ አዞረና መስመጥ ጀመረ፣ "ጌታ ሆይ፣ አድነኝ!" እያለ ጮኸ (ማቴ 14፡30)።

በአራተኛ ደረጃ ደግሞ "የተዘረጋው እጅ" የምለውን ጭብጥ እናገኛለን፥ ኢየሱስ ወዲያውኑ እጁን ዘርግቶ ያዘው። ኢየሱስ ጴጥሮስ ደካማነቱን በማሳየቱ ሳይሆን በምሕረቱ ላይ ስላለው ጥርጣሬ እንደሚገሥጸው አፅንዖት ሰጥተትን ማስተዋል ይኖርብናል። በእርሱ መታመን ማለት ፍርሃትን ማሸነፍ እና እንደገና መነሳት ማለት ነውና።

ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደ ሞከርነው የዛሬው ቅዱስ የወንጌል ምንባብ (ማቴ. 14፡22-33) ኢየሱስ በማዕበል በሚናወጠው ሐይቅ ላይ ስለመራመዱ ይናገራል። ባለፈው እሁድ እንዳየነው ሕዝቡን በአምስት ዳቦና በሁለት ዓሣ ከመገባቸው በኋላ - ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ጀልባው እንዲገቡ እና ወደ ሌላኛው የባህር ዳርቻ እንዲጓዙ አዘዘ። ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ ከዚያም ለመጸለይ ብቻውን ወደ ኮረብታማ ስፍራ ወጣ። ከአብ ጋር ያለውን ሕብረት በእዚያው ያጠናክራል።



በሌሊት ሐይቁ በሚሻገሩበት ጊዜ የደቀ መዛሙርቱ ጀልባ በድንገት በከባድ ዐውሎ ነፋስ መናወጥ ይጀምራል። በእዚያን ወቅት በድንገት አንድ ሰው በውሃው ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ ሲመጣ አዩ። እነርሱ ያዩት ነገር ምትሃት መስሎዋቸው በጣም ደንግጠው ስለነበረ በፍርሃት ጮኹ። ኢየሱስ “አይዞአችሁ እኔ ነኝ አትፍሩ” የሚል ማረጋገጫ ሰጣቸው። ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ ፣ አንተ ከሆንክ በውኃው ላይ እየተራመድኩኝ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም “ና” አለው። ጴጥሮስ ከጀልባው ወርዶ ጥቂት እርምጃዎችን በውሃ ላይ መራመድ በጀመረበት ወቅት ከዚያም በወቅቱ የተነሳው ነፋስ እና ማዕበል ከፍተኛ ስለነበረ እጅግ በጣም ስለፈራ መስመጥ ይጀምራል። “ጌታ ሆይ አድነኝ” እያለ ጮኸ ከእዚያም በኋላ ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ ለምን ተጠራጠርክ?” ይለዋል።

ይህ ታሪክ በሁሉም የሕይወት ዘመናችን በተለይም በፈተና እና በችግር ጊዜ እራሳችንን በታማኝነት ወደ እግዚአብሔር እንድናቀርብ የቀረበልን ጥሪ ነው። ጠንካራ የጥርጣሬ እና የፍርሀት ስሜት ሲኖረን እና እየሰመጥን ያለን ሲመስለን እንደ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ አድነኝ” ብለን ለመጮህ ማፈር የለብንም። እሱ የሚያምር ጸሎት ነው! እናም ወዲያው እጁን ዘርግቶ የጴጥሮስን እጅ የያዘው የኢየሱስ የእጅ ምልክት ለረጅም ጊዜ በጥልቀት መታሰብ አለበት። እርሱ ፈጽሞ የማይተወን የአብ እጅ ነው ። ሁልጊዜ ጥሩ እና መልካም የሆነውን ለእኛ የሚፈልገውን የአብ ጠንካራ እና ታማኝ አባት የሚወክ እጅ ነው። ስለ ነብዩ ኤልያስ የተነገረው በዛሬው በመጀመርያው ምንባብ (1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 19:11-13) ላይ የተጠቀሰው ታሪክ እግዚአብሔር አውሎ ነፋስ ፣ እሳት ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ የሚወክለው አምላክ ሳይሆን በዝምታ ለእኛ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጠ አምላክ እንደ ሆነ ያሳያል። እግዚአብሄር የማያስገድድ እና ለመስማት የሚጠይቅ የብርሃን እስትንፋስ ነው። እምነት ማለት በማዕበል ውስጥ በምንሆንበት ወቅት ልባችንን ወደ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ፍቅር፣ ወደ አባቱ ወደ ርኅራኄው መመለስ ማለት ነው። ኢየሱስ ይህንን ለጴጥሮስና ለደቀመዛሙርቱ እንዲሁም ለእኛም ዛሬ ለማስተማር ፈለገ። እምነታችን ጎደሎ እንደ ሆነና መንገዳችንም በተጋላጭ ኃይሎች ሊደናቀፍ እንደሚችል በሚገባ ያውቃል። እርሱ ግን ወደ ደኅንነቱ እንድናመራ ለማድረግ አስቦ ወደ ሞት የገባው ጌታ ነው። እሱን መፈለግ ከመጀመራችን በፊት እንኳን እርሱ አጠገባችን ይገኛል። ከውድቀታችን በኋላ እኛን በማስነሳት በእምነት እንድናድግ ይረዳናል።

ማዕበሉ በተናወጠበት ወቅት የነበረችው ጀልባ በየትኛውም ዘመን የምትገኘው እና እርሷን በመቃረን የሚነፍሱ ንፋሶችን የምትጋፈጠው፣ አንዳንድ ጊዜ በጣም ከባድ ፈተናዎች የምያጋጥማት የቤተ ክርስቲያን ምስል ነው።  በዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ቤተ ክርስቲያን በምትገባበት ወቅት  "እግዚአብሔር ትቶኛል" ብላ የማሰብ ፈተና ሊገጥማት ይችል ይሆናል። ነገር ግን በተጨባጭ በእነዚያ ጊዜያት የእምነት ፣ የፍቅር እና የተስፋ ምስክርነት እጅግ የሚበራ ሆኖ በእነዚያ ጊዜያት ውስጥ ይታያል። አዳዲስ ክርስትያኖች በዓለም ሁሉ ላይ እንዲፈልቁ፣ ሰላም እና እርቅ በማውረድ ሂደት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ለሚሳተፉ ሰዎች ስማዕት እስከመሆን ድረስ የሚያደርስ ጸጋ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ እንዲከናወን የሚያደርገውን የትንሳኤውን ክርስቶስ የመገናኛ መስመር ነው።

ጨለማ እና የሕይወት ማዕበል በያጋጥመን ወቅት በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት ወደ ቀውስ ውስጥ ሲገባ በእምነት እና በተስፋ ፍቅር እንድንጸና ትረዳን ዘንድ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን  አማላጅነት እንማጸን።

የእዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ (ላዛሪስት)- ቫቲካን 

22 Aug 2026, 08:54