የእንክርዳዱ ምሳሌ የእንክርዳዱ ምሳሌ 

የሐምሌ 26/2018 ዓ.ም 16ኛው መደበኛ እለተ ሰንበት ንባባትና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.      መ. ጥበብ 12፡13.16-19

2.     መዝሙር 85

3.     ሮም 8፡26-27

4.    ማቴዎስ 13፡ 24-43

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የእንክርዳዱ ምሳሌ

ኢየሱስም ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻው ቦታ ጥሩ ዘር የዘራን ሰው ትመስላለች። ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ፣ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ስንዴው በቅሎ ማፍራት ሲጀምር እንክርዳዱም አብሮ ብቅ አለ። “የዕርሻው ባለቤት አገልጋዮችም ወደ እርሱ ቀርበው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ በዕርሻህ ቦታ ጥሩ ዘር ዘርተህ አልነበረምን? እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። “እርሱም፣ ‘የጠላት ሥራ ነው’ አላቸው። “አገልጋዮቹም፣ ‘እንክርዳዱን ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ ብለው ጠየቁት። “እርሱ ግን፣ ‘አይሆንም፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውንም አብራችሁ ልትነቅሉ ትችላላችሁ፤ ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ። በዚያን ጊዜ ዐጫጆቹን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳትም እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን ሰብስባችሁ በጐተራዬ ክተቱ እላቸዋለሁ’ አላቸው።”

የሰናፍጭና የእርሾ ምሳሌ

ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ አንድ ሰው ወስዶ በዕርሻው ቦታ የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች። የሰናፍጭ ዘር ከሌሎች ዘሮች ሁሉ ያነሰች ብትሆንም፣ ስታድግ ግን ከቍጥቋጦዎች ሁሉ በልጣ፣ የሰማይ ወፎች መጥተው በቅርንጫፎቿ ላይ እስኪያርፉ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።” አሁንም ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ ሴት ወስዳ ሊጡ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ በመደባለቅ የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።” ኢየሱስ ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ ምሳሌም ሳይጠቀም የነገራቸው አንድም ነገር አልነበረም። በዚህም በነቢዩ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤ “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ።”

የእንክርዳዱ ምሳሌ ትርጕም

ከዚያም ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፣ “በዕርሻው ውስጥ ስላለው እንክርዳድ የተናገርኸውን ምሳሌ ትርጕም ንገረን” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ጥሩውን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ ዕርሻውም ይህ ዓለም ነው፤ ጥሩው ዘር የእግዚአብሔርን መንግሥት ልጆች ያመለክታል፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፤ ዘርቶት የሄደው ጠላትም ዲያብሎስ ነው፤ መከሩ የዓለም መጨረሻ ሲሆን፣ ዐጫጆቹም መላእክት ናቸው።

“እንክርዳዱ ተነቅሎ በእሳት እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም ለኀጢአት ምክንያት የሆኑትንና ክፉ የሚያደርጉትን ሁሉ ለቅመው ከመንግሥቱ ያወጣሉ። 42ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ እቶን እሳት ይጥሏቸዋል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሓይ ያበራሉ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳቹ!

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል (ማቴዎስ 3፡24-43) ውስጥ አሁንም ቢሆን ኢየሱስ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌዎችን ለሕዝቡ የመናገር ፍላጎት እንዳለው እንመለከታለን። በዛሬው አስተንትኖ ትኩረቴን የማደርገው ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ትዕግሥት እንድናውቅ አስቦ ልባችን ለተስፋ ክፍት እንዲሆን በማሰብ በተናገረው በእንክርዳዱ ምሳሌ ላይ ትኩረቴን አደርጋለሁ።

መልካሙ ስንዴ በተዘራበት ማሳ ውስጥ እንክርዳድ እንደበቀለ የምናገረው ይህ ቃል በአፈሩ ውስጥ ያሉትን ጎጂ እፅዋቶች በሙሉ የሚያጠቃልል መሆኑን ኢየሱስ ነግሮናል። በመካከላችን በአሁኑ ጊዜም ቢሆን አፈሩ በብዙ የእፅዋት አረም እና ፀረ-ተባዮች ጉዳት ደርሶበት በመጨረሻም ዕጽዋትን፣ መሬትን እና ጤናን እየጎዳ ይገኛል። ከዚያም አገልጋዮቹ እንክርዳዱ ከየት እንደመጣ ለማወቅ ወደ ጌታው ሄደው በጠየቁት ወቅት ጌታው “ይህንን ያደርገው ጠላት ነው!” (ማቴ 13፡28) በማለት ይመልስላቸዋል። ምክንያቱም "እኛ ጥሩ ዘር ነበረ የዘራነው" በማለት አክሎ ይገልጽላቸዋል። የሚገዳደረን ጠላት ይህንን ለማድረግ መጣ። እያደገ የመጣውን እንክርዳድ ወዲያውኑ ነቅሎ ለመጣል ይቻል ነበር። ይልቁንስ ባለቤቱ አይሆንም “ምክንያቱም እንክርዳዱን ስትነቅሉ መልካሙን ዘር አብሮ ሊነቀል ይችላል” በማለት ይከለክላቸዋል። እኛ የመከር ጊዜ እስኪደረስ ድረስ መጠበቅ አለብን፣ ከዚያም መልካሙን ፍሬ ከእንክርዳዱ በመለየት፣ እንክርዳዱን ማቃጠል ይቻላል ብሎ የመልስላቸዋል። በመልካም መንፈስ የተተረከ ታሪክ ነው። የታሪክ ራእይ በዚህ ምሳሌ ውስጥ ሊነበብ ይችላል። ሁልጊዜም ቢሆን መልካም ዘር ብቻ ከሚዘራው የማሳው ባለቤት ከሆነው ከእግዚአብሄር ቀጥሎ - የጥሩ ስንዴ እድገት ለመግታት እንክርዳዱን የሚዘራ ጣላት አለ። የማሳው ባለቤት የሆነው ጌታ በፀሐይ ብርሃን በግልጽ ይሠራል፣ ዓላማውም በጥሩ መከር እንዲበቅል ማድረግ ነው። ሌላኛው ተቃዋሚ በሌላው በኩል ደግሞ የሌሊቱን ጨለማ ይጠቀማል፣ እናም በቅናት፣ በጠላትነት መንፈስ ሁሉንም ነገር ያጠፋል። ኢየሱስ የጠራው የባላጋራው ስም ዲያብሎስ ነው፣ የእግዚአብሔር ተቃዋሚ ነው፣ ዓላማውም የእግዚአብሔርን የደህንነት ሥራ ማደናቀፍ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፍትሐዊ ያልሆኑ መሰናክሎችን በመደቀን የእግዚአብሔር መንግሥት መዘጋቱን ማረጋገጥ ነው። በእርግጥ የመልካሙ ዘር እና የእንክርዳዱ ምሳሌ በጥቅሉ መልካም እና መጥፎ የሆኑትን ነገሮች ብቻ የሚወክል ምሳሌ አይደለም፣ ነገር ግን እግዚአብሔርን ወይም ዲያቢሎስን መከተል የምንችል እኛን የሰው ልጆችን የሚወክል ምሳሌ ነው። ብዙ ጊዜ ሰላም የሰፈነበት ቤተሰብ ውስጥ ጦርነት እና ምቀኝነት ሲፈጠር እንመለከታለን፣ ሰላም በሰፈነበት ሰፈር ውስጥ መጥፎ ነገሮች ሲከሰቱ ብዙ ጊዜ ሰምተናል። “አንድ ሰው እንክርዳድ ሊዘራ ወደ እዚያ ስፍራ እንደ ሄድ አድርገን እንናገራለን፣ ወይም “ይህ የቤተሰቡ አባል የሆነ ሰው በንግግሩ እንክርዳድ ዘራ” ብለን እንናገራለን። ሁልጊዜ አጥፊ የሆነ ክፉ ዘር እየዘራን ነው። ይህንን የሚያደርገው ደግሞ ሌሎችን ለማጥፋት በማሰብ ዲያቢሎስ ወይም እኛን የሚፈትኑ ነገሮች ግፊት የተነሳ በምናወራቸው ወሬዎች ሊሆን ይችላል።



የአገልጋዮች ዓላማ ክፋ የሆነውን የእንክርዳዱን ዘር ወዲያውኑ ማስወገድ ነበር፣ ይህ ማለት ደግሞ ክፉ ሰዎችን ማስወገድ ማለት ነው፣ ነገር ግን ጌታው ብልህ የሆነ ሰው ነበር፣ አርቆ ይመለከታል፣ እንዴት በትዕግስት መጠባበቅ እንዳለባቸው ማወቅ አለባቸው ፣ ምክንያቱም ስደት እና ጥላቻ የክርስቲያን ሕይወት አካል ናቸውና። በእርግጥ ክፋት ውድቅ መደረግ አለበት ፣ ነገር ግን ክፉ የሚያደርጉ ሰዎች በመሆናቸው የተነሳ በትዕግስት መጠባበቅ ያስፈልጋል። ይህ ትዕግስት አሻሚ በሆነ መልኩ ያሰብነውን ነገር ደብቀን በግብዝነት መንፈስ የመቻቻል ጥያቄ አይደለም ፣ ነገር ግን በምሕረት መንፈስ የሚደረግ የፍትህ ተግባር ነው። ኢየሱስ ከጻድቃን ይልቅ ኃጢአተኞችን ለመፈለግ ፣ ከጤናማ ይልቅ የታመሙትን ለመፈወስ ( ማቴዎስ 9፣12-13) እንደ መጣ መጽሐፍ ቅዱስ የምናገር ሲሆን፣ እኛ የእርሱ ደቀመዛሙር የሆንን ሰዎች ተግባር ክፉዎችን ማጥፋት ሳይሆን ክፉዎችን መገሰፅ እና ማዳን ሊሆን ይገባል። እዚያ ላይ ነው እንግዲህ ትዕግስት የሚያስፈልገው።

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል የአሰራር እና የሕይወት ታሪክ ሁለት መንገዶችን ያቀርባል ፣ በአንድ በኩል አርቆ ማየት የሚችለውን የጌታውን ታሪክ እንመለከታለን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ችግሩን የሚያዩ የአገልጋዮቹን እይታ እናገኛለን። በአገልጋዮቹ ልብ ውስጥ እንክርዳድ የሌለበት እርሻ የመንከባከብ መንፈስ አለ፣ በጌታው ልብ ውስጥ ደግሞ መልካም የሆነ የስንዴ ዘር አለ። ጌታ በጥሩ የስንዴ ዘር ላይ ትኩረቱን በማድረግ በእንክርዳድ መካከል ያለውን መልካም ዘር እንዴት መንከባከብ እንደምቻል እንድንማር ይገብዘናል። የሌሎችን ውስን መሆን እና ጉድለት የሚሹ ሰዎች ሁሉ ከእግዚአብሄር ጋር በጥሩ ሁኔታ አይተባበሩም፣ ነገር ግን በቤተክርስቲያን እና በታሪክ መስክ በጸጥታ የሚያድጉትን መልካምነት እንዴት እንደሚገነዘቡ የሚያውቁ እነዚያ ሰዎች መልካሙ ዘር እስከ መከር ጊዜ ድረስ እንዲያድግ ማድረግ ይችላሉ። ያኔ ለመልካሙ ወሮታ የሚከፍል ክፉዎችንም የሚቀጣው እግዚአብሔር እና እርሱ ብቻ ይሆናል ማለት ነው። በአባትነት ፍቅር ከሚወዳቸው ልጆቹ ማንም እንዳይጎድል የሚፈልገው የእግዚአብሔርን ትዕግሥት እንድንረዳ እና ያንን ትዕግስት እንድንላበስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትረዳን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል።

የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ (ላዛሪስት)-ቫቲካን

02 Aug 2026, 11:01