በቬንዙዌላ የተከሰተው አሰቃቂ የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው ውድመት በቬንዙዌላ የተከሰተው አሰቃቂ የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው ውድመት  (Ricardo Arduengo)

በቬንዙዌላ የማኪታ የድሆች ትናንሽ እህቶች ጉባኤ የመስክ ሆስፒታል አቋቁመው እያገለገሉ እንደሆነ ተነገረ

ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በቬንዙዌላ የተከሰተውን አሰቃቂ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ በሃገሪቱ የሚገኘው በማኪታ የድሆች ትናንሽ እህቶች ጉባኤ የሚተዳደረውና በላ ጓይራ ከተማ የሚገኘው የሳን ሆሴ ሆስፒታል ከባድ መዋቅራዊ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት በሃገሪቷ የደረሰው ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ላደረሰው ጉዳት የአደጋ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት ጉባኤው ለተጎዱት ሰዎች እንክብካቤ የሚሰጥ የመስክ ሆስፒታል ማቋቋሙ ተነግሯል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“የሳን ሆሴ ሆስፒታል በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት መዋቅራዊ ጉዳት ስለደረሰበት ከአሁን በኋላ አገልግሎት ለመስጠት ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም” ያሉት በጤና አጠባበቅ አገልግሎት የቬንዙዌላ ከተሞች በሆኑት የላ ጓይራ እና ካራካስ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ማህበረሰቦችን የሚያገለግለው የማኪታ የድሆች ትናንሽ እህቶች ማህበር ዋና ሃላፊ እህት ማሪያ ሬይዳ ሞራ ሳንቼዝ፥ በዚህም ምክንያት ከመንገዱ ባሻገር ባለው ስፍራ የመስክ ሆስፒታል አቋቁመው በአደጋው የተጎዱ ሰዎችን ማገልገል መጀመራቸውን አስረድተዋል።

እንደሌላው ህዝብ ሁሉ የእሳቸው ትልቁ ተስፋ ከአደጋው የተረፉ ተጨማሪ ሰዎችን ማግኘት እንደሆነ የጠቆሙት እህት ማሪያ፥ የአከባቢው ባለስልጣናት ከ3,500 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ይፋ ባደረጉበት ሰዓት ብዙም ሳይቆይ በላ ጓይራ ፍርስራሽ ስር ከአደጋው የተረፉ ሰዎች በተአምር መገኘታቸው ተስፋ የሚሰጥ ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል።

በአገልግሎታቸው ወቅት ከሚያገኟቸው አንዳንድ ሰዎች ጋር በሚነጋገሩበት ጊዜ ሁሉም ሰዎች በአደጋው አንድ ጓደኛቸውን፣ ዘመዳቸውን ወይም ልጃቸውን ማጣታቸውን እንደሚናገሩ ያስታወሱት እህት ማሪያ፥ ሌሎች ደግሞ በአደጋው ምክንያት የሚሠሩባቸው አካባቢዎች በመውደማቸው ቤታቸውን ወይም መተዳደሪያቸውን ማጣታቸውን እንደሚገልጹ አስታውሰው፥ በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት መናጋቱን አስረድተዋል።

በሰብዓዊ ቀውስ ወቅት መጠለያዎችን መንከባከብ

እህት ማሪያ በመስክ ሆስፒታሉ ከሚሰጠው እንክብካቤ በተጨማሪ ሶስት የአደጋ ጊዜ መጠለያዎችን አዘውትረው እንደሚጎበኙ ጠቁመው፣ እዚያ ያለው ሁኔታ እጅግ በጣም ከባድ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ በተለይም አብዛኛው ዓለም አስቀድሞ እንደሚያውቀው ቬንዙዌላ ቀድሞውኑ ከባድ የኢኮኖሚ እና የሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ስለነበረች ሁኔታውን ፈታኝ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

በመሬት መንቀጥቀጥ በተጎዳው አካባቢ እርዳታ በማቅረብ ላይ የሚገኙ ገዳማውያት
በመሬት መንቀጥቀጥ በተጎዳው አካባቢ እርዳታ በማቅረብ ላይ የሚገኙ ገዳማውያት

ባለፈው እሁድ ‘ፓድሬ ማቻዶ’ በተሰኘው አደባባይ በላ ጉዌይራ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፓብሎ ሞዴስቶ የተመራ የቅዱስ ቁርባን ስግደት ማክበራቸውን ያስታወሱት እህት ማሪያ፥ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ ያለው እምነትና ጽናት በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥም ጠንካራ ሆኖ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በድንኳኖች እና በጊዜያዊ መጠልያዎች ሥር የሚሰጥ የጤና አገልግሎት

በላ ጉዌይራ ከተማ የሚገኘውን እና በማኪታ የድሆች ትናንሽ እህቶች ጉባኤ የሚተዳደረው የሳን ሆሴ ሆስፒታል ሰፊ የሕክምና አገልግሎቶች ያሉት፣ ደረጃ ሁለት የጤና እንክብካቤ ተቋም ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ይህ ጉባኤ በማኪታ የሚገኘውን የማድሬ ኤሚሊያ ትምህርት ቤትን፣ በካራካስ የሚገኙ ተጨማሪ የጤና እንክብካቤ ማዕከላትን እና የአረጋውያን ማረፊያ ማዕከልን እንደሚያስተዳድር ተገልጿል።

ይሁን እንጂ የሳን ሆዜ ሆስፒታል በአደጋው ምክንያት ከፍተኛ የሆነ መዋቅራዊ ጉዳት ስለደረሰበት ከአሁን በኋላ አገልግሎት መስጠት እንደማይችል የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት ከሕንፃው ፊት ለፊት ባለው አደባባይ ላይ የመስክ ሆስፒታል በማቋቋም አገልግሎት መስጠት እንደጀመሩ የገለጹት እህት ማሪያ፥ በአሁኑ ወቅት ከጣሊያን ቀይ መስቀል ማህበር፣ ከቬንዙዌላ የክርስቲያን-ተኮር የጤና አገልግሎቶች ማህበር (AVESSOC) እንዲሁም በፓድሬ ማቻዶ ክሊኒክ እና በሳን ሆሴ ሆስፒታል ከሚያገለግሉ የራሳቸው ጉባኤ ሐኪሞች ድጋፍ እያገኙ እንደሆነ አስታውሰዋል።

እህት ማሪያ ማዕከላቸው ከመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው በኋላ ከደረሰበት ጉዳት አገግሞ አገልግሎት መስጠት የሚጀምርበት መንገድ በተስፋ በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ አስረድተው፥ “በአሁኑ ወቅት በድንኳኖችና በጊዜያዊ መጠለያዎች ሥር የጤና አገልግሎቶችን እየሰጠን እንገኛለን” ያሉ ሲሆን፥ በዚህ ቦታ ሁሉንም አገልግሎት ለመስጠት የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነ ጠቁመው፥ ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ ሰራተኞቻቸው እና በጎ ፈቃደኞቻቸው በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው ጉዳት ቢደርስባቸውም የሕክምና እንክብካቤ የሚያቀርቡት እዚሁ ስፍራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ በየዕለቱ የተፈናቀሉ ቤተሰቦች የሚኖሩባቸውን የድንኳን ካምፖችን እንደሚጎበኙ፤ እንዲሁም ውሃ፣ ምግብ፣ መድኃኒት እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን እንደሚሰጧቸው ገልጸው፥ በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ መካከል የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ ወይም የሚጥል በሽታን የመሳሰሉ ሥር የሰደደ ሕመም ያለባቸውን ታካሚዎች መዘንጋት እንደማይችሉ፥ የጤና ሁኔታቸው ከዚህ የበለጠ እንዳይባባስ ዘላቂ እንክብካቤ እና መድሃኒቶቻቸውን ማግኘት እንደሚታስፈልጋቸው አመላክተዋል።

የሕዝብ ጤና ድንገተኛ የአደጋ ስጋት

ስለ ድንገተኛ በሽታ ወረርሽኝ ስጋቶች የተጠየቁት እህት ማሪያ ‘በሚያሳዝን ሁኔታ የሃገሪቱ የጤና አጠባበቅ ሁኔታ ከመሬት መንቀጥቀጡ በፊትም አስጊ እንደነበር አስታውሰው፥ የቫርጋስ ግዛት እጅግ ሞቃታማ ክልል ስለሆነ እና የውሃ መጠን ስለሚቀንስ በአሁኑ ወቅት የሃገሪቷ የጤና አጠባበቅ ከቀድሞውኑ በባሰ ሁኔታ አስጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት መድሃኒት እና ፀረ-ፈንገስ ክሬሞች ፍላጎት መኖሩን ጠቁመው፥ ይህ እጥረት ማለቂያ እንደሌለው እና አሁንም ድረስ በፍርስራሹ ውስጥ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ለሚፈልጉ የህይወት አድን ሰራተኞች ወይም ከአደጋው የቀሩትን ጥቂት ንብረቶች ለማግኘት ለሚሞክሩ ሰዎች የሚያስፈልግ ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ ፍላጎት መኖሩን አመላክተዋል።

የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎችን ሥራ በተመለከተ በቫርጋስ ግዛት የሚገኙ አብዛኛዎቹ ፋርማሲዎች በመውደማቸው እና በመዘጋታቸው ምክንያት የሆስፒታሉ ዶክተሮች በተገቢው ሁኔታ መድኃኒቶችን ማከፋፈል እንዲችሉ ታካሚዎቻቸውን እያደራጁ መሆኑን የገለጹት እህት ማሪያ፥ በጣም ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ታካሚዎች በካራካስ ወደሚገኙ ሆስፒታሎች እንደተዛወሩ ጠቁመው፥ “በዋና ዋና የጤና አጠባበቅ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን፣ ብሎም ቁስሎችን በማከም እና ብቅ ማለት የጀመሩ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል።

ለ138 ዓመታት የዘለቀ አገልግሎት

እህት ማሪያ በሳን ሆሴ ሆስፒታል ላይ በደረሰው ጉዳት ምክንያት የማህበረሰቡን ጥልቅ ሀዘን እንደሚጋሩ ጠቁመው፥ ይህ አከባቢ ጉባኤያቸው የተመሰረተበት ቦታ መሆኑን ያስታወሱ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ የመስራቾቻቸው የአባ ማቻዶ እና የእማሆይ ኤሚሊያ ቅሪቶች የተቀበሩበት ጸሎት ቤት እዚህ ስፍራ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ ይህ ሆስፒታል ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለመላው የቫርጋስ ግዛት ልዩ ምልክት እንደሆነ እና ማህበረሰቡን ለ138 ዓመታት ያገለገለ መሆኑን አስረድተዋል።

“ሆስፒታሉ የግድግዳና የኮንክሪት ውህድ ብቻ አይደለም” ያሉት እህት ማሪያ በመጨረሻም፥ አደጋው ቢከሰትም ሆስፒታሉ ዳግመኛ አገልሎት መስጠት እንደሚጀምር ያላቸውን ብሩህ ተስፋ በመግለጽ፥ ይህ ሆስፒታል በየቀኑ የተቻላቸውን ሁሉ ለማበርከት የሚተጉ እያንዳንዱ እህቶች፣ ነርሶች እና ዶክተሮችን ጨምሮ የሁሉም ሰው ንብረት እንደሆነ በማመላከት አጠቃለዋል።

 

 

 

 

09 Jul 2026, 16:26