የአሜሪካ ብፁዓን ጳጳሳት በኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪ ተቋም ውስጥ ያለው የዘር አድልዎ እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የአሜሪካ የኢሚግሬሽን አስከባሪ አካል (Immigration Enforcement) ህገ-ወጥ ስደተኞችን ለመቆጣጠር፣ ድንበር ለማስከበር እና የሀገር ውስጥ ህጎችን ለመተግበር እንዲሁም በአገር ውስጥ የሚኖሩ ህገ-ወጥ ስደተኞችን በመለየት፣ በመያዝ እና ወደየሀገራቸው የመመለስ (Deportation) ሥራዎችን በዋናነት የሚሰራ በፌዴራል መንግስት ሥር የሚንቀሳቀስ የፍትህ አካል እና ተቋማት ስብስብ ሲሆን፥ ይህ ስርዓት በዋናነት ድንበር ጥበቃን እና የውስጥ አገር ስደተኞችን ቁጥጥር እንደሚመለከት ይታወቃል።
በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በህግ ማስከበር ሂደት የተፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ተከትሎ የአሜሪካ ብፁዓን ጳጳሳት “እንደ ካቶሊካዊያን ሁሉም ሰው በእግዚአብሔር መልክ እና አምሳል የተፈጠሩ መሆናቸውን እናምናለን” ያሉ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት በሰው ልጅ ሕይወት ላይ እየደረሱ ያሉትን ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት በጽኑ እንደሚቃወሙ በአጽንዖት ገልጸዋል።
የአሜሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ የፍትህ እና እርቅ ማስተባበሪያ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ጋርቺያ እንዲሁም በጉባኤው ጽህፈት ቤት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት ብፁዕ አቡነ ብሬንዳን ካሂል በቅርቡ በአሜሪካ ውስጥ የስደተኞች ቁጥጥር እርምጃዎችን ተከትሎ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት በሆኑ በርካታ ክስተቶች ዙሪያ ያወጡትን የእረኝነት (መንፈሳዊ) አስተያየት በማስመልከት ማብራሪያ መስጠታቸው ተነግሯል።
ሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ድረ ገጽ ላይ የታተመው የጳጳሳቱ ሃዋሪያዊ አስተያየት ለጠፋው ክቡር የሰው ልጅ ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸው፥ ምንም እንኳን የህግ ማስከበር ሂደቱ አስፈላጊ ተግባር ቢሆንም፥ የህግ አስከባሪ አካላት የሰውን ክብር ወይም የሰውን ህይወት አደጋ ላይ መጣል እንደሌለባቸው አፅንዖት በመስጠት አሳስበዋል።
'የመንግስት ስልጣን በሥነ ምግባር ህጉ ገደብ ውስጥ ሊተገበር ይገባል’
ብፁዓን ጳጳሳቱ በሰጡት መግለጫ ላይ ‘ህግን በሰብዓዊ መንገድ ማስፈጸም እንዲሁም በሕይወት የመኖር እና የፍትሃዊ የሕግ ሂደት መብቶችን ጨምሮ መሰረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር የሲቪል ባለስልጣናት ህጋዊ ሚና እንደሆነ ማረጋገጣችንን እንቀጥላለን’ ብለዋል።
“የመንግስት ስልጣን ሁልጊዜ በሥነ ምግባር ህጉ ገደብ ውስጥ መተግበር አለበት” ሲሉ አጥብቀው ያሳሰቡት ብፁዕ አቡነ ጋርቺያ እና ብፁዕ አቡነ ካሂል፥ ይህ በመሆኑም ምክንያት ለኢሚግሬሽን ስርዓታችን ትርጉም ያለው ማሻሻያዎች እንዲደረጉ የሚያስችሉ ተጠያቂነት፣ ግልጽነት እና ፍትህ እንዲሰፍን ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል።
በዘር ላይ የተመሠረተ አድልዎ የሚያስከትለው ስጋት
ባለፈው ህዳር ወር የአሜሪካ ብፁዓን ጳጳሳት የተናገሩትን በማስታወስ፣ “ሰዎች በዘር ላይ የተመሠረተ አድልዎ እና የስደተኞች ህግ አፈጻጸም ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በፍርሃት እና በጭንቀት ውስጥ መሆናቸውን በማየታችን ያሳስበናል” ሲሉ በድጋሚ የገለጹ ሲሆን፥ በዘር ላይ የተመሠረተ አድልዎ “ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ክብር የሚጥስ ብቻ ሳይሆን፣ ፍርሃትን በመፍጠር፣ መተማመንን በማዳከም እንዲሁም ፍትሃዊ ያልሆኑ እና አሳዛኝ ውጤቶችን የማስከተል አደጋን በመጨመር በግለሰቦች፣ በቤተሰቦች እና በማህበረሰቦች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል” ሲሉ ካስረዱ በኋላ ብፁዓን ጳጳሳቱ ያላቸው የእረኝነት ስጋት የሲቪል ህጉ ከሚፈቅደው ነገር የተለየ መሆኑን እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
የሰውን ክብር ማሳነስ ወይም ችላ ማለት እንደ መደበኛ ነገር ሊወሰድ አይገባም
“የማንኛውንም ሰው ወይም የሰዎች ቡድን ክብር የሚቀንሱ ወይም ችላ የሚሉ ድርጊቶችን” እንደሚቃወሙ የገለጹት ብፁዕ አቡነ ጋርቺያ እና ብፁዕ አቡነ ካሂል “እነዚህ ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት በህብረተሰባችን ውስጥ እንደ መደበኛ ነገር ሊወሰዱ አይገባም” ያሉ ሲሆን፥ እንደ መደበኛ ነገር ሊወሰዱ የማይገባቸውን አመለካከቶች በተመለከተ፣ “ህጋዊ ሁኔታቸው ምንም ይሁን ምን ስደተኞችን እንደ ሰው አለመቁጠር ወይም ክብርን መንፈግ” እና “የህግ አስከባሪዎችን መጥፎ አድርጎ መሳል” የሚሉትን ሁለት ምሳሌዎች ጠቅሰዋል።
ብፁዓን ጳጳሳቱ በመጨረሻም ለሞቱት ሰዎች ነፍስ፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለሀገሪቱ እና የህዝብ አገልግሎት ኃላፊነት ለተሰጣቸው ሁሉ በጋራ የጸለዩ ሲሆን፥ “የሰውን ልጅ ክብር የሚያሳጡ ንግግሮች፣ በዘር ላይ የተመሠረተ አድልዎ እና ጥቃት እንዲቆሙ፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ እንደመሆኑ መጠን ያለውን ተፈጥሯዊ ክብር ለመገንዘብ የሚያስችል አዲስ ቁርጠኝነት እንዲኖር” የጸለዩ ሲሆን፥ “በሀዘን፣ በችግር እና እርግጠኛ ባልሆኑ ጊዜያት ፍጹም እምነትን በተግባር ያሳየችው የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲታከልበት እንማጸናለን” ሲሉ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።