ፈልግ

የቅድስት ሞኒካ በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ለሚሰቃዩ ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ለህጻናት፣ ለወጣቶች እና ለተጋቡ ጥንዶችም ጭምር የምሕረት ቤት ሆኗል የቅድስት ሞኒካ በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ለሚሰቃዩ ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ለህጻናት፣ ለወጣቶች እና ለተጋቡ ጥንዶችም ጭምር የምሕረት ቤት ሆኗል   (Foto Credit Catherine McWilliams)

የቅድስት ሞኒካ ማዕከል ከአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ጋር ለሚታገሉ ሰዎች የተስፋ ጉዞ መሆኑ ተነገረ

ለልጆቻቸው በሚጨነቁ እናቶች የጸሎት ቡድንነት በመነሳት ‘ሳንታ ሞኒካ’ በሚል ስያሜ የተጀመረው ተነሳሽነት በደቡባዊ አሜሪካ በምትገኘው ቲዬራ ዴል ፊጎ ከተማ ውስጥ በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ለተጎዱ ወጣቶችና ቤተሰቦች ድጋፍ የሚሰጥ ተቋም በመሆን አገልግሎቱን ማስፋፋቱ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

‘የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እህቶች’ የተሰኙት ገዳማዊያት፣ ልጆቻቸው በተለያዩ ሱሶች ለተጎዱ እናቶች ጸሎት ለማድረግ ብለው የጀመሩት የጸሎት ተነሳሽነት፣ በአሁኑ ወቅት ‘ሳንታ ሞኒካ’ በሚል ስያሜ በከተማው ውስጥ የሚገኙ እና በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ለሚሰቃዩ ወጣቶች ድጋፍ የሚሰጥ ድርጅት በመሆን እንቅስቃሴውን ከፍ ማድረጉ ተገልጿል።

የኢንዱስትሪ ከተማ የሆነችው ሪዮ ግራንዴ በደቡብ አሜሪካ አህጉር ደቡባዊ ጫፍ ላይ የምትገኝ ሲሆን፥ ከአርጀንቲና የተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች ለሥራ ዕድል እና ለተሻለ ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ተስፋ ሰንቀው ወደዚህች ከተማ እንደሚጎርፉ ይነገራል።

ሆኖም፣ ከዚህ ተለዋዋጭ እንቅስቃሴ በስተጀርባ በአከባቢው ያለው በጣም ቀዝቃዛው የአየር ንብረት፣ ነፋስ እና የመገለል ስሜት ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል ለድብርት፣ ለሀዘን እና ለአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ማጋለጡ የተነገረ ሲሆን፥ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እህቶች አገልግሎታቸውን የጀመሩት በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ እና የመጀመሪያዎቹ እህቶች ደሴቲቱ ላይ የደረሱት እ.አ.አ. በ 2012 ዓ.ም. እንደነበር ተገልጿል።

የተቋሙ ዋና ኃላፊ የሆኑት እህት ቨርጂኒያ ሚሼል እና እህት ሮዚዮ ፓርሚጂያኒ የ ‘ጄሱስ ዴ ላ ዲቪና’ የተሰኘ ሃዋሪያዊ አገልግሎት ማዕከል መስራች በሆኑት አባት ፌሊሲሞ ቪሴንቴ ጥሪ አማካይነት ይህንን አገልግሎት የጀመሩ ሲሆን፥ ማዕከሉ በዋናነት የተቋቋመው በተለይም በብቸኝነት፣ በድብርት እና በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ለሚሰቃዩ እና በጣም ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ማገገሚያ እና ድጋፍ መስጫ ቦታ እንዲሆን ታስቦ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ይሄንን በማስመልከት እማሆይ ቪኪ እንደተናገሩት “ልዩ መንፈሳዊ ስጦታችን የሰዎችን ቁስል መፈወስን የመሳሰሉ አስቸኳይ ፍላጎቶች ጋር መላመድ እንዳለበት ተገንዝበን ነበር” በማለት አስታውሰዋል።

‘ሳንታ ሞኒካ’ የተጀመረው ልጆቻቸው በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ወጥመድ ውስጥ በገቡ እናቶች ዘንድ እንደ አንድ የጋራ ድጋፍ ሰጪ ቡድን በመሆን እንደተጀመረ የተገለጸ ሲሆን፥ እናቶቹ ከፍተኛ የሆነ የልብ ስብራት ይዘው ወደ ሃዋሪያዊ አገልግሎት ማዕከሉ ይመጡ እንደነበር እና ያሉበትን ሁኔታ ለማሸነፍ መጽናኛ እና መንፈሳዊ እርዳታ ይፈልጉ እንደነበር ተመላክቷል።

መጀመሪያ ላይ ወደዚህ ማዕከል ለሚመጡ እናቶች መንፈሳዊ ድጋፍ ይሰጣቸው እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፥ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ጸሎት በተጨባጭ ግብዓቶች እና ድጋፎች መታገዝ እንዳለበት ግልጽ መሆኑ ሲረጋገጥ፥ እንደ ትንሽ የጸሎት ቡድን የተጀመረው እንቅስቃሴ ሕይወትን ወደሚቀይር ተቋምነት መሸጋገሩ ተነግሯል።

ከጊዜ በኋላ፣ እናቶችን ብቻ ሳይሆን ልጆቻቸውንም ለመርዳት የሚፈልጉ በጎ ፈቃደኞች ወደ ተቋሙ መምጣት መጀመራቸውን ተከትሎ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሚሰጥ አሰራር እንዲዘረጋ መንገድ መክፍቱ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህ ማዕከል የሚሰጠው አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ነፃ እንደሆነ እና ለመላው ቤተሰብ ነፃ የሆነ ሃይማኖታዊ እና የስነ-ልቦናዊ ወይም የህክምና ድጋፍ የሚሰጥ በክልሉ ውስጥ ብቸኛው ተቋም መሆኑ ተገልጿል።

ይህ ጉዞ ቀላል እንዳልነበር የሚገልጹት ገዳማዊያት እህቶቹ፥ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ቀውሶች ለመረዳት እና ለመጋፈጥ ጥናትና ምርምር ማድረግ እንዲሁም አዳዲስ ዘዴዎችን መፈለግ እንዳስፈለጋቸው ጠቁመው፥ “ቴክኒካዊ የሆኑ ሥራዎችን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ ከክርስቲያናዊ አስተምህሮ እና ከማርያማዊ መንፈሳዊነታቸው ጋር ማዋሃድን” እንደተማሩ በማስታወስ፥ በሳንታ ሞኒካ ውስጥም ለውጥ ያመጣው ትልቁ ነገር ይህ እንደነበር እማሆይ ቪኪ አረጋግጠዋል።

በእናቶች ጽናት የተነሳሳ ተልዕኮ
የመጀመሪያው ሀሳብ፣ በጎዳና ላይ ለወደቁ፣ ለተጎዱ እና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሚደረገውን እንክብካቤ ለመግለጽ ሲባል ተቋሙን ‘The Good Samaritan’ ወይም 'ደጉ ሳምራዊ' ብሎ መሰየም አስፈላጊ እንደነበር የገለጹት እማሆይ ቪኪ፥ ሆኖም የፕሮጀክቱን መነሻ የተመለከቱት ገዳማዊያት እህቶቹ ለልጆቻቸው ህይወት ያለማቋረጥ የታገሉትን ደፋር እናቶች በማስታወስ፣ ለዓመታት ለልጇ ለቅዱስ አውገስጢኖስ መለወጥ የጸለየችውን፣ የጽናት እና የእምነት ተምሳሌት የሆነችውን የቅድስት ሞኒካን ሥም ለተቋሙ ለመስጠት መወሰናቸውን ገልጸዋል።

ይህ ሥም ለወጣቶች የሚደረገውን ድጋፍ እንዲሁም እናቶች በማገገም እና ተስፋን መልሶ ለማግኘት በሚደረገው ሂደት ውስጥ ያላቸውን ወሳኝ ሚና እንደሚያንጸባርቅ የተገለጸ ሲሆን፥ የሳንታ ሞኒካ ማዕከልን ጉዞ ለየት የሚያደርጉ በርካታ ታሪኮች መኖራቸውና ከእነዚህም መካከል አጠቃላይ ህይወቷ እረፍት አልባ ይመስል የነበረውን ማሪሴል የተባለች ወጣት ታሪክ እንደሚገኝበት ተነግሯል።

የማሪሴል ታሪክ
ማሪሴል ስትወለድ በወላጆቿ ችላ በመባሏ ምክንያት በተለያዩ የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከላት ውስጥ ያደገች ሲሆን፥ በልጅነቷ ያጋጠማት ከፍተኛ የፍቅር እና የእንክብካቤ እጦት ወደ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት እንደገፋፋትና ለዓመታት የተለያዩ የማገገሚያ ህክምናዎችን እንደተከታተለች፥ ነገር ግን በጣም ከባዱ ጊዜ የመጣው መንግስት ልጆቿን በመውሰድ እንክብካቤ ወደሚደረግላቸው ሌላ ስፍራ ሲወስዳቸው እንደሆነ ታሪኳ ይገልፃል።

ልጆቿን መልሳ ለማግኘት ብቸኛው መንገድ ህክምናውን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ የነበረባት ሲሆን፥ ይህ ደግሞ ለእሷ የማይቻል እንደሚመስል እና ወደ ሳንታ ሞኒካ በደረሰችበት ቀን ህይወቷን ለማጥፋት ወስና እንደነበር፤ ነገር ግን ያልጠበቀችውና የገዳማዊያቱ ርህሩህ እንክብካቤ በማዕከሉ ውስጥ እንድትቆይ እንዳደረጋት፥ በዚህም ለረጅሙ እና አስቸጋሪ ለሆነው ሂደት በር እንደከፈተ ታሪኳ ያስረዳል።

ለገዳማዊያት እህቶቹም ቢሆን ይህ ወቅት እንቅፋቶች የበዙበት፣ የተስፋ መቁረጥ ጊዜያት እና የጭንቀት ምሽቶች እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን፥ ሆኖም ለማሪሴል የተደረገው ጽኑ የሆነ የአብሮነት መንፈስ፣ የማዳመጥ እና የባለሙያ ድጋፍ፣ አዲስ የህይወት ዕድልን መለማመድ እንድትጀምር ማስቻሉን ገዳማዊያቱ ይናገራሉ።

እማሆይ ቪኪ በተለይ በአንድ ወቅት ጸሎት ቤት ውስጥ ሆነው ሲጸልዩ ያጋጠማቸውን ነገር በመጥቀስ፥ በወቅቱ፣ በመንገድ ላይ ያገኘውን የተጎዳ ሰው ትቶ እንዳላለፈው እንደ ደጉ ሳምራዊ፣ እግዚአብሔር ማሪሴልን በግል ለእርሳቸው አደራ እየሰጠ እንደሆነ ተሰምቷቸው እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን፥ ይህ ተሞክሮ ትዕግሥታቸውን እና ተስፋቸውን ሳይቀንሱ ከሁሉም ሰው ጋር ለመጓዝ ያላቸውን ቁርጠኝነት ማደሱን ገልጸዋል።

ከጥቂት ቆይታ በኋላ ማሪሴል ወደዚህ ልዩ ማዕከል ለመግባት መስማማቷን እና ህክምናዋ ፍሬ ማፍራቱን፣ እንዲሁም ቀደም ሲል ለተደረገላት መንፈሳዊ ድጋፍና አጋርነት ምስጋና ማቅረቧን ያስታወሱት እማሆይ ቪኪ፥ በማዕከሉ ውስጥ ማገገሟ እና መረጋጋቷ ከታየ በኋላ፣ ልጆቿን የማሳደግ መብት እንደተፈቀደላት ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እህቶች በቲዬራ ዴል ፊጎ ከተማ ውስጥ እራስን የመስጠት እና የተስፋ ምስክር ሆነው መቀጠላቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር የሳንታ ሞኒካ ማዕከል በርካታ ሰዎች ብቻቸውን እንዳልሆኑ እና ሁልጊዜ ሕይወታቸውን እንደገና መገንባት እንደሚችሉ የሚረዱበት ቦታ መሆኑ ተነግሯል።

እማሆይ ቪኪ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲናገሩ በዚህ ማዕከል ውስጥ እያንዳንዱ ወጣት በማህበረሰቡ ውስጥ ከሚፈጠሩ የተለያዩ የብቸኝነት ስሜቶች የሚላቀቅበት ማዕከል መሆኑን አስረድተው፥ ማንኛውም ሰው በዚህ ማዕከል ውስጥ ቆይታ ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የብቸኝነት መንፈሱ ጨርሶ እንደሚጠፋ በመግለጽ አጠቃለዋል።

28 Jul 2026, 14:37