ፈልግ

በሞዛምቢክ የሚገኙ ገዳማዊያን  እህቶች የጎርፍ አደጋ ተጎጂዎችን ሲረዱ በሞዛምቢክ የሚገኙ ገዳማዊያን እህቶች የጎርፍ አደጋ ተጎጂዎችን ሲረዱ  

በሞዛምቢክ ታይ-ታይ ክልል የሚገኙ ሚሲዮናዊያን እህቶች የጎርፍ አደጋ ተጎጂዎችን እያገዙ እንደሆነ ተነገረ

በሞዛምቢክ የሚገኙት "የክቡር ደም ሚስዮናዊያን እህቶች" በደቡባዊ ሞዛምቢክ ታይ-ታይ ከተማ በደረሰ አውዳሚ የጎርፍ አደጋ ምክንያት ለተፈናቀሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ምግብ እና መጠለያ በማቅረብ እንዲሁም ሰብዓዊ ክብራቸውን በመጠበቅ በጣም ተጋላጭ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍል በርህራሄ እያገለገሉ እንደሚገኝ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች በባህር ዳርቻ የሚገኙ አካባቢዎች ውድመትን ለሚያስከትሉ፣ ሰዎችን ለሚያፈናቅሉ እና የዕለት ተዕለት ኑሮን ለሚያውኩ ያልተጠበቁ የጎርፍ አደጋዎች የተጋለጡ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ ‘የክቡር ደም ሚስዮናዊያን እህቶች’ ለአስርት ዓመታት ያክል ሲያገለግሉበት በቆዩበት በሞዛምቢክ ዋና ከተማ እና በሊምፖፖ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች አብዛኛውን ጊዜ በጎርፍ አደጋ እንደሚጠቁ እና ገዳማዊያት እህቶቹ በዚህ አደጋ ለተጠቁ ሰዎች ተጨባጭ የሆነ ድጋፍ ለማድረግ በአስቸኳይ እርምጃ እንደሚወሰዱ ተገልጿል።

ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎችን ማገልገል
የክቡር ደም ሚስዮናዊያን እህቶች ባለፉት ዓመታት ማፑቶ፣ ጋዛ፣ ቴቴ እና ናካላን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ግዛቶች ውስጥ ያላቸው ተልዕኮ እየተስፋፋ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፥ ገዳማዊያን እህቶቹ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና አጠባበቅ፣ በማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እና የሃዋሪያዊ እንክብካቤን ጨምሮ በተለያዩ አገልግሎቶች በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኝ፣ እንዲሁም ወላጅ አልባ ህፃናት እና ተጋላጭ ለሆኑ ህፃናት፣ ለአረጋውያን፣ ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለተጋለጡ ሰዎች እና ለኤችአይቪ ህመምተኞች የተለያዩ የድጋፍ ፕሮግራሞችን እያካሄዱ እንደሚገኝ ተነግሯል።

ከዚህም ባሻገር ገዳማዊያት እህቶቹ ዘላቂ የሆነ የሰው ልጅ እድገትን ለማበረታታት እና ችግር ላጋጠማቸው ማህበረሰቦች ተስፋን ለማጎናጸፍ በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የታይ-ታይ የጎርፍ አደጋ ተጎጂዎች
በማህበረሰቡ ውስጥ እጅግ ተጋላጭ የሆኑት ክፍሎችን ለማገልገል እህቶቹ ያላቸው ቁርጠኝነት ከህብረተሰቡ የተገለሉትን ሰዎች በመድረስ እና የእያንዳንዱን ሰው ሰብዓዊ ክብር በማሳደግ የሚገለጥ ሲሆን፥ የማህበሩ የክልል የበላይ አለቃ የሆኑት እህት ሊጂያ አልቤርቶ ሙያንጋ ከቫቲካን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በጋዛ ግዛት አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የደረሰው ከባድ የጎርፍ አደጋ በርካታ ቤተሰቦችን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለ መሆኑን ጠቅሰው፥ በተለይም በታይ-ታይ ወረዳ ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ቤተሰቦች አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እና የውሃ መጠን መጨመር አካባቢያቸውን ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ በርካታ ማህበረሰቦች ቤቶቻቸውን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን አመላክተዋል።

ተፈናቃዮቹ ጊዜያዊ መጠለያ ማግኘታቸው
ለእነዚህ ቀውሶች ምላሽ ለመስጠት የክቡር ደም ሚስዮናዊያን እህቶች ጉባኤ አባላት በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚኖሩትን ለመደገፍ ሁልጊዜ ቁርጠኝነቱ እንዳላቸው የተነገረ ሲሆን፥ የአካባቢው ባለስልጣናት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለደህንነታቸው ሲባል ወደ ትምህርት ቤቶች እና ትላልቅ ማዕከላት ካዛወሯቸው በኋላ እህቶቹ በአካባቢያቸው ከፍተኛ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ቦታዎች በመለየት፥ መጠለያ ለሚፈልጉ 600 የሚሆኑት ህፃናት ለሚገኙበት ወደ 1,600 ለሚጠጉ ተፈናቃዮች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኝ ተገልጿል።

አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ወደዚህ ጊዜያዊ መጠሊያ ጣቢያ የደረሱት ቤቶቻቸውን፣ ንብረቶቻቸውን እና የኑሮ መሠረታቸውን በማጣታቸው ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ በመሆን፣ ከለበሱት ልብስ ውጪ ምንም ይዘው እንዳልመጡ ተነግሯል።

የነፍስ አድን ሥራ እና ርህራሄ
የጎርፍ አደጋው ያደረሰው ጉዳት ያለውን አጣዳፊነት በመረዳት፣ እህቶቹ ለተጎጂዎች በሳምንት ሶስት ጊዜ የምግብ እርዳታ የማደራጀት ሥራ መጀመራቸውን የገለጹት እህት ሊጂያ፥ በገዳማቸው ውስጥ ምግብ በማዘጋጀት ወደ መጠለያ ጣቢያዎቹ እንደሚያጓጉዙ እና ለተፈናቃይ ቤተሰቦች ያከፋፍሉ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባሻገር ይህ የሰብአዊ እርዳታ ሥራ በእህቶቹ ብቻ የተወሰነ እንዳልነበረ አስታውሰው፥ በእህቶቹ ቁርጠኝነት እና ርህራሄ በመነሳሳት፣ በርካታ የአካባቢው ሴቶች በፈቃደኝነት ጊዜያቸውን በመስጠት ምግብ በማዘጋጀት እና በማከፋፈል ሥራው ላይ መተባበራቸውን፣ ከዚህም በተጨማሪ እህቶቹ ከምግብ እና ከመጠለያ ባሻገር እንደ ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እና አልባሳትን የመሳሰሉ ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን በመለየት የተጎጂዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሥራ መስራታቸውን አመላክተዋል።

ስጋቶችን እና ችግሮችን ማዳመጥ
በእነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ፣ የጎርፍ ውሃው እስኪጎድል እና ህይወት ወደነበረበት እስኪመለስ ድረስ ቤተሰቦች እረፍት እንዲያደርጉ የሚያስችሉ ፍራሾች መዘጋጀታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ገዳማዊያት እህቶቹ በአካባቢው ማህበረሰቦች እና በአጋሮች ዘንድ ግንዛቤን በመፍጠር እጅግ አስቸኳይ ፍላጎቶችን ለማሟላት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ማቅረባቸው ተነግሯል።

“ገዳማዊያቱ ወደ መጠለያ ጣቢያዎቹ በሚያደርጉት ጉብኝት ወቅት የተፈናቃይ ቤተሰቦችን ስጋቶች እና ችግሮች ለማዳመጥ እንዲሁም በጣም አስቸኳይ ፍላጎቶቻቸውን ለመለየት ጊዜ ይወስዳሉ” ያሉት እህት ሊጂያ፥ የእህቶቹ መገኘት መጽናናትን እንደሚያመጣ እና ተፈናቃዮቹ የሚያጋጥማቸውን ፈተና ቀላል እንደሚያደርገው አስረድተዋል።

በመከራ ውስጥ ያለ ተስፋ
በዚህ የመከራ ወቅት የእህቶቹ መገኘት የተስፋ ብርሃን መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊዋ፥ ገዳማዊያቱ ከተገለሉ እና መከራ ከሚደርስባቸው ሰዎች ጎን በመቆም እንዲሁም ተስፋ በሌለበት ቦታ ሰብዓዊ ክብርን በመመለስ ያላቸው ቁርጠኝነት የልዩ ጥሪያቸውን ዋና ይዘት እንደሚያንጸባርቁ አመላክተዋል።

ምግብ በማዘጋጀት፣ ጊዜያዊ መጠለያዎችን በመጎብኘት እና ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች ድጋፍ በመስጠት በሚያደርጉት ቀላል በሚመስል፣ ነገር ግን ከፍተኛ ተጽእኖ ባለው የአገልግሎት ሥራቸው ገዳማዊያት እህቶቹ በሞዛምቢክ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ሲመራቸው የቆየውን ተልዕኮ በተግባር መግለፃቸውን የቀጠሉ ሲሆን፥ በተገለሉ ሰዎች መካከል የሚያሳዩት ርህራሄ የተሞላበት መገኘት፣ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ ለደረሰው ቁስል ፈውስን እንደሚያመጣም ጭምር ተገልጿል።

24 Jul 2026, 14:22