ሞዛምቢካዊያኑ ገዳማዊያት "ሰላምን ለማስፈን የእርቅና የሰላም ሰዎች እንሁን" ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ገዳማዊያት እህቶቹ ለሞዛምቢክ ወጣቶች በተለየ ሁኔታ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በተለይም ችግር በሚከሰትበት ጊዜ ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባ፣ በእግዚአብሔር መታመን እና ጸሎት ማድረግ አስፈላጊ መሆናቸውን አጽንዖት ሰጥተው የገለጹ ሲሆን፥ ሆኖም ግን ይሄንን ማድረግ የሚቻለው እያንዳንዱ ሰው የራሱን ድርሻ በመወጣት እንደሆነ ገልጸው፥ በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ሰላም በሃገሪቷ ላይ እውን እንዲሆን እያንዳንዱ ሰው የሰላምና የእርቅ ሰው መሆን እንዳለበት እነዚህ ሞዛምቢካውያን ሚስዮናውያን እህቶች ጠቁመዋል።
ቀጣይነት ያለው ስልጠና አስፈላጊነት
ሚስዮናውያኑ በማከልም በሮም ስለሚከታተሉት የስልጠና መርሃ ግብር የተናገሩ ሲሆን፥ ስልጠናው የመጨረሻውን ቃለ-መሐላ ለመግባት ለሚዘጋጁም ሆነ ቀደም ብለው የመጀመሪያ ደረጃ ቃለ መሃላ ለፈጸሙት እህቶች ያለውን ጠቀሜታ አጉልተው አሳይተዋል።
ጊዜያዊ ወይም የመጀመሪያ ደረጃ ቃለ-መሐላ የገቡት እህት አሜሊያ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት፣ የስልጠና ክፍለ-ጊዜዎቹ ስለወደፊቱ ጊዜ ትክክለኛውን ምርጫ ለማድረግና ለመወሰን ስለሚረዱ እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ ገልጸው፥ ወደፊትም ገና የሚማሩት እና ጥናት የሚያደርጉባቸው ነገሮች መኖራቸውን ጠቁመው፥ “የምንወስነው ውሳኔ የምንፈልገው ነገር መሆኑን ወይም አለመሆኑን ለመወሰን ስልጠናው ይረዳናል” ሲሉ አስረድተዋል።
ለዘመኑ ምልክቶች ትኩረት መስጠት
ይህ ስልጠና የመጀመሪያ ደረጃ ቃለ-መሐላ ለፈጸሙት ለሁለቱም የክቡር ደም ማኅበር ሚስዮናውያን እህቶች አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ ምክንያቱም ደግሞ ሁለቱም ገዳማዊያት እህቶች እራሳቸውን ማደስ እና ማዋሃድ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ከዚህም ባሻገር ሁልጊዜ ለዘመኑ ምልክቶች ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
የማኅበሩ ልዩ መንፈሳዊ ተልዕኮ የዘመኑን ፍላጎቶች ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን እንደሚገባው የገለጹት እህት ማሪያ፥ የክቡር ደም ሚስዮናውያን አባላት ከውጫዊ ሁኔታዎች ማለትም ከቁምስናዎች እና ከምዕመናን ጋር ከመዋሃድ ባሻገር፣ እንደ አንድ የሃይማኖት ማህበረሰብ ሁልጊዜ ራሳቸውን መጠየቅ እንዳለባቸው የገለጹ ሲሆን፥ የማህበሩ መንፈሳዊ ተልዕኮ ለዛሬው ዓለም ፍላጎቶች ምላሽ መስጠቱን ማረጋገጥ እና የዛሬውን ሰው በተሻለ ሁኔታ ለመርዳት በማህበሩ ውስጥ መታደስ የሚገቡ ነገሮችን ማጤን እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
ለአገልግሎት የተሰጠ ሕይወት
የአባላት ሥልጠና ኃላፊ የሆኑት እህት ማሪያ እና እህት አሜሊያ አሌክሳንደር በአሁኑ ወቅት የሚኖሩት እና የሚያገለግሉት በሞዛምቢክ የሚስዮናዊነት አገልግሎት ላይ ለተሰማሩ እህቶች እንዲሁም ለተጨማሪ መንፈሳዊ ትምህርት ወደ ፖርቹጋል ለሚመጡ የሞዛምቢክ እህቶች ማረፊያ እንዲሆን እ.አ.አ. በ 1960 ዓ.ም. ፖርቱጋር፣ ሊዝበን ከተማ ውስጥ በሃይማኖታዊ ማህበሩ የተቋቋመ ቤት ውስጥ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ እህት አሜሊያ በሊዝበን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እየተከታተሉ የሚገኙት በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ ጠቅሰው፥ በተመሳሳይ ጊዜም በአካባቢው በሚገኝ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበረሰብ ውስጥ እያገለገሉ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ከዚህም ባሻገር ለመጨረሻ ቃለ መሃላ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የገለጹት የሞዛምቢክ ተወላጅ የሆኑት እህት አሜሊያ፥ በዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ በመሆናቸው ደስተኛ እንደሆኑ፤ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ማኅበራቸው እና ተልዕኮዋቸው የሚጠይቃቸውን ተግባር እንደሚፈጽሙ ለቫቲካን ዜና ገልጸዋል።
ይህ በመሆኑም ምክንያት ከፍተኛ ፍላጎት እና እጥረት ያለባት ሃገራቸውን ትተው በመውጣት፣ በማኅበሩ ተልዕኮ መሠረት ሌላ ሀገር ውስጥ ማገልገል ጊዜን በከንቱ ማባከን ሳይሆን፣ ‘እዚህ በሚያገኙት ጉልበትና አቅም፣ በሃገራቸው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ለመርዳት እንደሚጠቀሙበት’ እህት አሜሊያ በአጽንዖት የገለጹ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ሁል ጊዜ ድጋፍ ለሚሹ በእድሜ የገፉ ገዳማዊያት እህቶችን ለመርዳት ይህ ስልጠና ጉልበት እንደሚሆናቸው አስረድተዋል።
ተስፋ እና ጸሎት
ሁለቱ ሚስዮናዊያን እህቶች በተለይም ሥራ አጥነትን፣ ግጭትን፣ ወንጀልን እና ሌሎች በርካታ ተግዳሮቶችን እና ችግሮችን ለሚጋፈጡት የሞዛምቢክ ወጣቶች የተስፋ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ ‘ምንም እንኳን በየቀኑ የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢገጥሙም፣ ተስፋ አለመቁረጥ እንደሚገባ፥ ምክንያቱም ለተሻለ ነገ መኖር የሚሰጠው ተስፋ ቤተሰቦችን እና ሀገራትን የሚገነባ ኃይል መሆኑን አመላክተዋል።
ጸሎት በእርግጥም ለወደፊቱ ጊዜ ቁልፍ ነገር ስለሆነ ወጣቶች ሁልጊዜ በእግዚአብሔር መታመን እና መጸለይ እንዳለባቸው የመከሩት ገዳማዊያት እህቶቹ፥ “ሆኖም ግን በመጀመሪያ የራሳችንን ድርሻ መወጣት እንደሚገባ፣ ለሀገራችን የምንመኘውን ሰላም በውስጣችን በመያዝ፣ የእርቅና የሰላም ሰዎች መሆን ይገባናል” በማለት አጠቃለዋል።