‘ማግኒፊካ ሂውማኒታስ’ አፍሪካን ከአዳዲስ የባርነት ዓይነቶች ለመጠበቅ ጥረት እንደሚያደርግ ተነገረ
ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም. እንደ አጋጣሚ የአፍሪካ ቀን ተብሎ በሚከበርበት ዕለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቅድስት መንበርን ወክለው ይቅርታ የጠየቁበት እና የመጀመሪያቸው የሆነውን ሃዋሪያዊ መልዕክታቸውን ይፋ ያደረጉበት ዕለት ሲሆን፥ ይሄንን አስመልክቶ ‘ምቢዩ’ በተሰኘው የካቶሊክ ሬድዮ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቁት እና በታንዛኒያ የቡኮባ ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሜቶድ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ ፈለግ
ከሃዋሪያዊ ሥራዎቻቸው በተጨማሪ የታሪክ ምሁር በመሆናቸው በትምህርት ቤቶች እንዲሁም በአካባቢው ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የቤተክርስቲያንን ታሪክ እንደሚያስተምሩ የገለጹት ጳጳሱ፥ ከሚያደንቋቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ አንዱ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ምክንያቱም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ በታሪክ ውስጥ በተሰጣቸው ጊዜ በወቅቱ የነበረውን መጥፎ አዝማሚያ በመቃወማቸው እና ቤተክርስቲያን በዘመናቸው ለነበሩት ሰዎች የኢንዱስትሪ አብዮትን በመሳሰሰሉ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንድታተኩር በማድረጋቸው እንደሆነ አስረድተዋል።
የአሁኑ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛም የእሳቸውን ሥም እና ፈለግ በመከተላቸው የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት ብፁዕ አቡነ ሜቶድ፥ ብፁዕነታቸው ግንቦት ወር ላይ ይፋ ባደረጉት የመጀመሪያ ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው ተመሳሳይ መንገድ መከተላቸውን አመላክተዋል።
‘ማግኒፊካ ሂውማኒታስ’ ወይም ‘የሰው ልጅ ታላቅነት’ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቀረበ የመጀመሪያቸው የሆነ ሃዋሪያዊ መልዕክት ሲሆን፥ ይህ ሃዋሪያዊ መልዕክት አሁን በምንገኝበት የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን የሰው ልጅን ለመጠበቅ የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ትኩረት ማድረጉ ይታወቃል።
ከዚህም በተጨማሪ ሃዋሪያዊ መልዕክቱ በካቶሊክ ማህበራዊ ትምህርት ገጽታዎች ላይ ዘመናዊ ማሻሻያ ሃሳቦችን ይዞ እንደመጣ የገለጹት ጳጳሱ፥ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት እና በዛሬው ዘመን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ወይም ሽግግር መካከል ያለውን ንፅፅር እንደሚያሳይ አስረድተዋል።
‘ማግኒፊካ ሂውማኒታስ’ ወይም ‘የሰው ልጅ ታላቅነት’ የተሰኘውን ሃዋሪያዊ መልዕክት በርካታ ጊዜ ማንበባቸውን ያስታወሱት ብፁዕ አቡነ ሜቶድ፥ በመልዕክቱ ላይ የተነሱት ጉዳዮች አስፈላጊ እና ወቅታዊ መናቸውን ጠቁመው፥ እንደ አንድ አፍሪካዊ የቤተክርስቲያን ታሪክ መምህር ስለ ባሪያ ንግድ ሲያስተምሩ ቤተክርስቲያኗ ቀደም ሲል ለባርነት በሰጠችው ድጋፍ ምክንያት ሁልጊዜ ምቾት እንደማይሰማቸው እና አንዳንድ ጊዜም እፍረት ይሰማቸው እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን፥ ቅዱስ አባታችን በዚያን ዘመን የነበረውን ኢፍትሃዊነት አምነው መቀበላቸው ትልቅ እፎይታ እና መጽናናትን እንደሰጣቸው ተናግረዋል።
ግለሰባዊ ክብርን ጎድቷል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሃዋሪያዊ መልዕክታቸው ውስጥ በባሪያ ንግድ ውስጥ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የነበራትን ታሪካዊ ሚና መግለፃቸውን ያስታወሱት ጳጳሱ፥ ያለፉ ክስተቶች የጊዜያቸውን ሞራላዊ መመዘኛዎች ከግምት ውስጥ ሳናስገባ ያለጊዜው ሊፈረድባቸው እንደማይገባ ግንዛቤው ቢኖራቸውም፣ ቤተክርስቲያኗ ይህንን ተግባር በማውገዝ ረገድ ያሳየችውን ከፍተኛ መዘግየት አሁንም መገንዘብ እንዳለባት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሃዋሪያዊ መልዕክታቸው ቁጥር 176 ላይ በወቅቱ ቤተ ክርስቲያን ስለነበራት አሉታዊ ሚና ይቅርታ መጠየቅን አስመልክተው ‘ብዙዎቹ በጌታ ዘንድ እጅግ የተወደዱ እንደመሆናቸው መጠን ሰብዓዊ ክብራቸው መጠበቅ የነበረበት ቢሆንም፥ እጅግ በርካታ ሰዎች የደረሰባቸውን ከፍተኛ ስቃይና ውርደት ስናስብ ጥልቅ የሆነ ሐዘን ላይሰማን አይችልም፥ ይህ በመሆኑም ምክንያት በቤተክርስቲያን ስም ከልቤ ይቅርታን እጠይቃለሁ” ማለታቸውን አስታውሰዋል።
ምንም እንኳን የሚገናኝ ጉዳይ ባይሆንም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ታሪካዊ የይቅርታ መልዕክት የቀረበው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የተካሄደው የባሪያ ንግድ በሰው ልጅ ላይ ከተፈጸሙት ከባድ ወንጀሎች መካከል እጅግ የከፋው መሆኑን ባወጀ ከሁለት ወራት በኋላ መሆኑ ተገልጿል።
ብፁዕ አቡነ ሜቶድ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የይቅርታ መልዕክት የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች እንዲሁም በዘመናት ሂደት ውስጥ የራሷ አገልጋዮችም ጭምር የገጠሟቸውን ፈተናዎችና የፈጸሟቸውን ስህተቶች መደበቅ እንደማያስፈልግ ለቤተክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች የሚያስታዉሱትን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛን አስተምህሮ እንደሚያስታውስ ጠቁመው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት እ.አ.አ. በ 1899 ዓ.ም. ‘ዴፒውስ ሌጆር’ በሚል ለካህናቱ ተገቢውን ሥነ-መለኮታዊ እና አእምሯዊ ትምህርት በተመለከተ የተወሰኑ መመሪያዎችን በማካተት ይፋ ባደረጉት ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው እንደሆነም ጭምር አስረድተዋል።
ከባርነት መጠበቅ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ‘ማግኒፊካ ሂውማኒታስ’ በተሰኘው ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው መልካም ነገርን የማከናወን እንዲሁም የማውደም አቅም ያለው ባለሁለት አፍ ሰይፍ ዓይነት ፈጠራ ሲያጋጥም የቀደሙትን የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ አባቶች ፈለግ መከተላቸውን ያመላከቱት ጳጳሱ፥ ከዚህም በተጨማሪ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ የፊልም፣ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ቴክኖሎጂ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ እ.አ.አ. በ1957 ዓ.ም. ‘ሚራንዳ ፕሮርሰስ’ የተሰኘውን ሃዋሪያዊ መልዕክት ይፋ ማድረጋቸውን፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በ2002 ዓ.ም. ስለ ኢንተርኔት መፃፋቸውን፣ እንዲሁም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ደግሞ ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን’ ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጥቀስ ስለ ማህበራዊ ተግባቦት መፃፋቸውን ጭምር አስታውሰዋል።
በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን የሰው ልጅ አርቴፊሻል በሆነ መንገድ ከመተሳሰር ይልቅ ክብሩን፣ እውነቱን እና ነፃነቱን መጠበቅ እንዳለበት ያሳሰቡት ብፁዕ አቡነ ሜቶድ በመጨረሻም፥ “ጥሩ ሕሊና ላይኖራቸው ከሚችሉ ጥቂት ሰዎች የሚፈጸሙ አዳዲስ የባርነት ዓይነቶች እና አገዛዝ ስለሚጠብቀን ለአፍሪካ ይህ ሃዋሪያዊ መልዕክት ትልቅ ስጦታ ነው” በማለት አጠቃለዋል።