ፈልግ

በላይቤሪያ የሚገኙት የቅድስት ቤተሰብ እህቶች በማህበረሰቡ ውስጥ በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሆነ ተነገረ በላይቤሪያ የሚገኙት የቅድስት ቤተሰብ እህቶች በማህበረሰቡ ውስጥ በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሆነ ተነገረ 

በላይቤሪያ የሚገኙት የቅድስት ቤተሰብ እህቶች በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሆነ ተነገረ

የቅድስት ቤተሰብ እህቶች ማህበር አባል የሆኑት እህት ፊሎሜና ጃፓህ በላይቤሪያ ባላቸው ተልዕኮ በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ‘ትምህርት እውቀትን ለትውልድ ከማስተላለፍ እጅግ የላቀ’ መሆኑን ያስረዱ ሲሆን፥ ከዚህም ይልቅ ትምህርት የወንጌል ስርጭት፣ የፈውስ፣ የተስፋ እና የሀገር ግንባታ አገልግሎት እንደሆነ በማስታወስ፥ የዕለት ተዕለት ሥራቸው በእምነት፣ በትምህርት እና በማህበራዊ ለውጥ አገልግሎቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በላይቤሪያ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተለይም በሃገሪቱ ገጠራማ እና በቂ አገልግሎት በማያገኙ ማህበረሰቦች ውስጥ ትምህርትን በማስፋፋት ረገድ ለበርካታ ዓመታት ወሳኝ ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ብዙውን ጊዜ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች እና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በሚገኙ ማህበረሰቦች ዘንድ መረጋጋትን እንደሚያመጡ ተነግሯል።

በዚህም ረገድ እህት ፊሎሜና በዚህ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አገልግሎት በመነሳሳት፣ እንዲሁም በመምህራን ቤተሰብ ውስጥ በማደጋቸው እና ባላቸው ሃይማኖታዊ ጥሪ በመበረታታት ትምህርትን እንደ ጥሪም ሆነ እንደ ተልዕኮ መመልከት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በእምነት እና በታሪክ ላይ የተመሰረተ

ሐዋርያዊ አገልግሎቱን በልጆች ትምህርት እና ስልጠና አማካኝነት የቤተሰብ አገልግሎት ላይ ያተኮረው የቅድስት ቤተሰብ እህቶች ጉባኤን ከዓመታት በፊት መቀላቀላቸውን የተናገሩት እህት ፊሎሜና፥ እነዚህ እህቶች ‘የናዝሬት ቅድስት ቤተሰብ’ በመባል በሚጠሩት ኢየሱስ፣ ማርያም እና ዮሴፍ በመነሳሳት የክርስቲያን ቤተሰብን ለማስፋፋት፣ የሰውን ክብር ለመጠበቅ እና በጣም ተጋላጭ የሆኑትን የኅብረተሰብ ክፍልን ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፥ በጸሎት፣ በማኅበረሰብ ሕይወት እና በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የተመሠረተው ይህ ጉባኤ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ወደ መኖሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ቁምስናዎች እና የአካባቢ ማህበረሰቦች ለማምጣት ጥረት እንደሚያደርግ ተነግሯል።

ከዚህም ባሻገር ገዳማዊያን እህቶቹ በጤና አጠባበቅ እና በሃዋሪያዊ አገልግሎት ላይም መሰማራታቸው የተነገረ ሲሆን፥ እህት ፊሎሜና ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት ይህ አገልግሎት በቀለም ትምህርት ጠንካራ የሆኑ፣ በመንፈሳዊነት ላይ የተመሰረቱ እና ለኅብረተሰቡ ፍላጎቶች ምላሽ የሚሰጡ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝነት መምራቱን እንደቀጠለ ገልጸዋል።

በመላ ሃገሪቱ የካቶሊክ ትምህርትን ማጠናከር

የኬፕ ፓልማስ ሀገረ ስብከት የትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ እንደመሆናቸው መጠን ያላቸው ኃላፊነቶች በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ያሉትን የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች መቆጣጠር፣ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራንን እና መምህራንን መደገፍ እንዲሁም ተቋማቶቹ የቤተክርስቲያን እና ብሔራዊ የትምህርት ደረጃዎችን ማሟላታቸውን ማረጋገጥን እንደሚያካትቱ ያስረዱት እህት ፊሌሞና፥ ከዚህም ባሻገር ይህ ሥራ የትምህርት ቤት ክትትልን፣ የመምህራን ስልጠናን፣ የሥርዓተ ትምህርት ድጋፍን እንዲሁም ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር መሥራትን እንደሚያካትት አክለው ገልጸዋል።

እህት ፊሌሞና እንደ ብሔራዊ አስተባባሪነት ሚናቸው አንድ ወጥ የሆነ የካቶሊክ ትምህርት ራዕይን ለማሳደግ በመላ ሃገሪቱ ከሚገኙ የሀገረ ስብከት የትምህርት ጽህፈት ቤቶች ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ ጠቁመው፥ በጋራ በመሆን የአስተዳደር መዋቅሮችን በማጠናከር፣ የትምህትት ጥራትን በማሻሻል፣ ለህፃናት ጥበቃ በማድረግ እና የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ውስን የገንዘብ አቅም ላላቸው ቤተሰቦች ተደራሽ እንዲሆኑ የማረጋገጥ ሥራዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ትምህርትን ማስፋፋት

ላይቤሪያ ለዓመታት በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ችግር እና ውስን መሠረተ ልማት ምክንያት በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተግዳሮቶች ውስጥ እንደምትገኝ የጠቆሙት እህት ፊሌሞና፥ በርካታ ትምህርት ቤቶች በቂ ያልሆኑ መገልገያዎች፣ የብቁ መምህራን እጥረት እና በቂ የማስተማሪያ ቁሳቁሶች ባለመኖራቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቸገሩ አስረድተው፥ የእሳቸው ሀገረ ስብከት የሆነው እንደ ኬፕ ፓልማስ ባሉ ገጠራማ ሀገረ ስብከቶች እነዚህ ተግዳሮቶች የበለጠ ጎልተው እንደሚታዩ አስታውሰዋል።

በእነዚህ ችግሮች መካከል የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች የመቋቋሚያ ቦታዎች ሆነው መቀጠላቸውን ጠቁመው፥ እነዚህ ትምህርት ቤቶች አብዛኛው ጊዜ በገጠራማ አከባቢዎች በሚገኙ ማህበረሰቦች ውስጥ ለሚኖሩ ህፃናት ብቸኛ የተዋቀሩ የትምህርት ተቋማት መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፥ ለትምህርት ቤት መሪዎች ቀጣይነት ያለው ድጋፍ፣ የታቀደ የመምህራን ስልጠና እንዲሁም ተማሪን ማዕከል ያደረገ እና እሴቶችን መሰረት ያደረገ ትምህርትን በማበረታታት ረገድ ቤተክርስቲያኗ ጥራት ያለው ትምህርት ለጥቂቶች ብቻ ሳይሆን የሁሉም መብት መሆኑን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኗን አመላክተዋል።

የእያንዳንዱን ተማሪ ክብር መጠበቅ

ሲስተር ፊሎሜና በዋናነት ቅድሚያ ከሚሰጧቸው ነገሮች አንዱ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ሁሉን አቀፍ የመማሪያ አካባቢዎችን ማጎልበት እንደሆነ ጠቁመው፥ ‘የካቶሊክ ትምህርት ሁልጊዜ የእያንዳንዱን ሰው ክብር መጠበቅ እንዳለበት’ ያሳሰቡ ሲሆን፥ ጠንካራ የህፃናት ጥበቃ ፖሊሲዎች፣ በሥነ ምግባር እና በሙያዊ ባህሪ የታነፀ የመምህራን ምስረታ እና በጣም ተጋላጭ ለሆኑ ህጻናት ትምህርት ልዩ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

ከመማሪያ ክፍሎች ባሻገር በቁምስናዎች እና በገጠራማ አከባቢ ከሚገኙ ማህበረሰቦች ውስጥ ካሉ ሴቶች እና ልጃገረዶች ጋር እንደሚሰሩ የጠቆሙት እህት ፊሎሜና፥ ቤተሰቦች ዘላቂ የሆነ መተዳደሪያ እንዲያገኙ የሚረዱ ተነሳሽነቶችን እንደሚደግፉ ገልጸው፥ ቤተሰቦች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ሲያገኙ ህፃናት ልጆች በትምህርት ቤት የመቆየት እንዲሁም በትምህርት፣ በስብዕና እና በግል የማደግ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ አስረድተዋል።

የመጪው ጊዜ ተስፋ

እህት ፊሌሞና የትምህርት ስርዓቱ ጠንካራ ሲሆን እና ልጆች ጥራት ያለው ትምህርት ሲያገኙ የላይቤሪያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የበለጠ ብሩህ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፥ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች የአካዳሚክ ብቃት ያላቸውን ብቻ ሳይሆን፣ በሥነ-ምግባር እሴቶች ላይ በጥብቅ የተመሰረቱና ለጋራ ጥቅም መሻሻል ቁርጠኛ የሆኑ ተማሪዎችን በመቅረጽ ረገድ ለዚህ ራዕይ አስተዋጽኦ ለማድረግ ልዩ ቦታ እንዳላቸው ያስታወሱ ሲሆን፥ በርካታ ተግዳሮቶች ቢኖሩም መጪውን ጊዜ በተስፋ እንደሚያዩ አመላክተው፥ ትምህርት ቤቶቹ ምንም እንኳን በጣም ውስን ሀብቶች ቢኖሯቸውም ያላቸውን ሁሉ ለመስጠት ዝግጁ የሆኑ መምህራን ቁርጠኝነትን ሲያዩ የተሻለ ነገ እንደሚመጣ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር ማህበረሰባቸውን ለማገልገል በሚጓጉ ወጣቶች ጉጉት እንዲሁም ቤተክርስቲያን ለትምህርት ባላት ዘላቂ ቁርጠኝነት እና የወንጌል ተልዕኮዋ እንደሚበረታቱ ጠቁመው፥ እምነታቸውን በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ፣ በቤተክርስቲያን እና በመንግስት መካከል ባለው ትብብር፣ በገዳማዊያት እና በምዕመናን መካከል፣ በአካባቢው ማህበረሰቦች እና በዓለም አቀፍ አጋሮች መካከል ባለው ትብብር ላይ፣ እንዲሁም ሥራቸውን በሚደግፉ አካላት በሙሉ ላይ እንደሚጥሉ ጠቁመው፥ በዚህም በላይቤሪያ የሚገኙ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ለሃገሪቷ የተሻለ የወደፊት ጊዜ ብርሃን ሆነው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

እህት ፊሎሜና በመጨረሻም የቅድስት ቤተሰብ እህቶች ጉባኤ በበርካታ ሐዋርያዊ ምዕመናን አማካኝነት ጸጥ ያለ ግን ጥልቅ የሆነ ለውጥ የሚያመጣውን የእምነት፣ የትምህርት እና የርህራሄ አገልግሎት ተልዕኮውን እንደሚቀጥል ጠቁመው ወቅታዊ ሁኔታዎችን እያገናዘበ ለችግሮች በፍቅር ምላሽ መስጠቱን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

 

06 Jul 2026, 15:20