ፈልግ

ስደተኞች ወደ ላምፔዱሳ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ስደተኞች ወደ ላምፔዱሳ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ  

አባ ጆን ሊዶን፥ “ከመርከብ አደጋ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ስደትን መለወጥ ይገባል” ሲሉ ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጣሊያን የወደብ ከተማ ላምፔዱሳ ሐዋርያዊ ጉብኝት ከማድረጋቸው ቀደም ብሎ ለድንገተኛ አደጋ ከሚሰጡ ምላሾች በተጨማሪ ስልታዊ እና ርህራሄ የተሞላበት የውህደት፣ የውይይት እና የወንድማማችነት መንገዶችን መገንባት እንደሚያስፈልግ ባቀረቡት ጥሪ ላይ በማሰላሰል አባ ጆን ሊዶን በስደት ቀውስ ላይ የሚከተለውን አስተያየት አጋርተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን መምራት በጀመሩበት በአጭር ጊዜ ውስጥ የጊዜውን ሁኔታ በማጤን፥ ለአንዳንድ ስጋቶች እና ተግዳሮቶች ቤተ ክርስቲያን ምላሽ መስጠት የምትችልበትን የእግዚአብሔር ጥበብ ሲያስገነዝቡ ተመልክተናል።

ከተግዳሮቶቹ መካከል አንዱ የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ ሲሆን ይህ ርዕሥ በብዙ የአውሮፓ አገራት እና ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ዋና የፖለቲካ አጀንዳ ሆኗል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መልዕክትም ለዚህ ዓለም አቀፍ ክስተት ምላሽ ለመስጠት መንገድ የሚጠቁም ነው።

ቅዱስነታቸው በቅርቡ ወደ ካናሪ ደሴቶች፣ ሰኔ 27/2017 ዓ. ም ወደ ጣሊያ የወደብ ከተማ ላምፔዱሳ እና ወደ እናት ካብሪኒ የትውልድ ቦታ ያደረጉት ጉዞ በቤተ ክርስቲያኗ በወንጌል ተልዕኮ ጠቀሜታ ላይ የሚያተኩር ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቴኔሪፍ፥ ‘ስደተኞችን ያሳፈረ መርከብ ወደብ ላይ ባጋጠመው አደጋ ምክንያት በከተማው ተበታትነው የሚገኙ ስደተኞችን ሳያነጋግሯቸው እና ሥራ ሳይሰጧቸው መተው ደህንነት የማጣት ስሜት ከመፍጠሩ በተጨማሪ ተጋላጭነታቸውን ለሚጠቀሙ ሰዎች ዕድል መስጠት ነው’ በማለት መፍታት ያለበት ችግር እንደሆነ ተናግረዋል።

አደጋ ሲከሰት ብቻ ምላሽ መስጠት ፈታኝ ቢሆንም፥ በጊዜያዊ መፍትሄ ላይ ብቻ ከመገደብ ይልቅ ርህራሄ የተሞላበት የሥርዓት ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል። የስደት መንስኤዎችን መመልከት እና ችግሩን ማስወገድ እንዲሁም ፊታቸውም የተሠቃየውን የክርስቶስ ፊት ለማስታወስ የሚመጡ ስደተኞችን በርህራሄ መያዝ ያስፈልጋል።

ከሚሰቃዩ ስደተኞች ጀርባ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው በርካታ ውስብስብ ችግሮች አሉ። ስደተኞችን በመቃወም ከሚደረጉ ፖለቲካዊ ንግግሮች ጀርባ በጥልቀት መሄድ እና እምነታችን ከሚጠየቀን በላይ ምላሽ እንዳንሰጥ የሚከለክለንን ፍርሃት መመልከት አለብን።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ‘ዓለም አቀፍ ግዴለሽነት’ እንዲሁም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ስለ ‘ዓለም አቀፍ ኃይል አልባነት’ ተናግረዋል። እነዚህ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። እንደ አንድ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ምላሽ እንድንሰጥባቸው፣ እንድንነጋግርባቸው፣ እንድንመረምራቸው፣ እንድንተባበር እና እንድንራራ ጥሪ የሚያቀርቡ ናቸው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካናሪ ደሴቶች ቴኔሪፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በጥብቅ እንዳስታወሱን፥ ‘የሰው ሕሊና በተለይም ክርስቲያናዊ ሕሊና በእነዚህ የባሕር ውስጥ መቃብሮች ግድየለሽ መሆን አይችልም። በዚህ መንገድ የሚጠፋ እያንዳንዱ ሕይወት የሰው ልጅ ውድቀትን የሚያመላክት  ነው’ (ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ቴኔሪፍ)።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ‘የሰዎች አስደናቂነት’ ባሉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ለለውጡ ሞራላዊ አቅጣጫን ለማመላከት እንዲህ ብለዋል፥ ‘ዛሬ የማኅበራዊ ፍትህ ፈተና ስደተኞችን፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና በድህነት፣ በዓመፅ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በአካባቢ አደጋዎች ምክንያት ለስደት ለተጋለጡት ሰዎች የሚደረግ አያያዝ ነው። አንድ ማኅበረሰብ ስደተኞችን የሚይዝበት መንገድ ፍትሃዊነቱ በፍርሃት ወይም በወንድማማችነት መንፈስ የሚመራ መሆኑን ያሳያል’ ብለዋል።

በተጨማሪም ‘የቆሰለ ዓለምን መልሶ መገንባት ማለት በብዙ ድምጾች እና ራእዮች... ውስጥ ብሩህ ዕድል መኖሩን መገንዘብ ማለት ነው’ ብለው፥ አንድ ላይ መገንባት፣ ልዩነትን ወደ ሃብት መለወጥ፣ ማዳመጥ እና መወያየት፣ ፍትህን እና ወንድማማችነትን ማሳደግ የጋራ መሠረት ነው’ ብለዋል (ማግኒፊካ ሂውማኒታስ፣ ቁ. 10)።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አካዳሚያዊ ተቋማት አንድ ላይ መሰባሰብ በማስመልከት እንደተናገሩት፥ ‘የተስፋ ብርሃን ለመሆን የሞራል ግዴታ መኖሩን አምነን፥ የስደት መንስኤዎችን ለመፍታት እና ስደተኞችን ከአዲስ የመኖሪያ አካባቢ ማኅበረሰብ ጋር ለማዋሃድ የሚያግዝ ትክክለኛውን መንገድ አንድ ላይ መፈለግ አለብን’ ብለው፥ ‘የተሰቃዩ ሰዎች ጩኸት ወደ ተግባር መለወጥ አለብን’ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደዚሁም፥ ‘የተስፋ መልዕክተኞች’ ያሏቸውን የስደተኞች ጩኸት መስማት እና ይህ ተስፋ የሰው ፊት እንዳለው ተናግረዋል።

አካዳሚያዊ ማኅበረሰብን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ስደተኞችን እና አጋርነታቸውን ማሳደግ ስደተኞች ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲዋሃዱ የሚያበረታቱ እና ለውጦችን የሚያመጡ የውይይት መንገዶችን መገንባት እና የእነርሱ መኖር በረከት ሆኖ ይታያል።

ከፊታችን ያለው ፈተና ከካናሪ ደሴቶች ዳርቻ በላይ ስለሆነእነዚህን መንገዶች በተቀናጀ ሁኔታ መገንባት የዩኒቨርሲቲ አጋሮች ሊሰጡን የሚችሉት ልዩ ስጦታ ነው።

ቴነሪፍ በአሁኑ ወቅት የሕመም ማዕከል ብትሆንም በሰብዓዊ ክብር ላይ የሚደርስ አደጋ በጋራ መኖሪያ ምድራችን ድንበሮች ላይ በየቀኑ ይከሰታል። ለዚህ ዓለም አቀፍ ቀውስ መፍትሄ የሚገኘው በተበታተነ ጥረት ሳይሆን በጋራ ኃላፊነት የተሳሰረ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብን በማሰባሰብ ነው።

በእነዚህ ቀናት ውስጥ በካናሪ ደሴቶች የተሰጡት ምስክርነቶች ተነሳሽነትን አግኝተዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቃላት ሁላችንንም የሚያነቃቁ እና ፈታኝ ነበሩ። በብዙ የስብሰባው ተሳታፊዎች የተደረጉት ንግግሮች በአሁኑ ማኅበረሰባችን ውስጥ ብዙውን ጊዜ ጨለማ የሆነው ጉዳዮችን በድምቀት የሚያበሩ ‘ከዋክብት’ ናቸው። ሁላችንም ጭፍን ጥላቻን በማፍረስ ወደ ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ የወደፊት ጊዜ የሚመሩንን ስልታዊ ድልድዮችን መንደፍ ክቡር እና አስፈላጊ ተግባር እንደሆነ እናምናለን።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፔን ባደረጉት የመሰናበቻ ንግግራቸው፥ ‘ዓይናችሁን አንሱ! አዎ ዓይኖቻችንን ወደ ክርስቶስ እናዙር፣ በእመቤታችን ማርያም እንመራ፣ በተስፋ ጉዞአችንን እንቀጥል!’ በማለት አሳስበዋል።

የወቅቱን ሁኔታ እና አስተሳሰብን በመቀየር ለስደተኞች፣ ለጥገኝነት ጠያቂዎች እና ለመላው ማኅበረሰባችን የተሻለ ጊዜን ለማምጣት የምናደርገው ጥረት ገና መጀመሩ ነው።”

(የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር አባል አባ ጆን ሊዶን፥ በአሜሪካ ቪላኑቫ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ የእናት ካብሪኒ የስደት ተቋማ ዳይሬክተር)

 

02 Jul 2026, 15:38