የዓለም አቀፉ የታሊታ ኩም ትስስር የጎረጎሳዊያኑ 2025 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርት የዓለም አቀፉ የታሊታ ኩም ትስስር የጎረጎሳዊያኑ 2025 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርት  

የታሊታ ኩም ዓለም አቀፍ አስተባባሪ “ማንኛውም ሰው እንደ ንብረት ወይም ሸቀጥ ሊቆጠር አይገባም” ማለታቸው ተነገረ

በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚሰራው “ታሊታ ኩም” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም የጎረጎሳውያኑን የ 2025 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ ይህ ሪፖርት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንዴት እያደገ እንደመጣ በማሳየት፣ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚፈጸሙ ብዝበዛዎች እና ማጭበርበሮች በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰዎችን ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት የሚያገለግሉ መንገዶች መሆናቸውን አመላክቷል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ምንም እንኳን "ልማዳዊው" የባርነት አሰራር በህግ የተከለከለ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በዘመናዊ ባርነት ወጥመድ ውስጥ እንደሚገኙ የሚነገር ሲሆን፥ ከዚህም በላይ፣ በዓለም አቀፍ የሰራተኞች ድርጅት እና በዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ዘገባ መሰረት እነዚህ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሌሎች የብዝበዛ ዓይነቶች በየዓመቱ ከ 236 ቢሊዮን ዶላር በላይ ህገ-ወጥ ገቢ የሚያስገኙ እጅግ ትልቅ የገቢ ምንጭ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል።

በየጊዜው እያደገ በመጣው ዘመናዊ ዓለም ውስጥ ይህ ችግር ከመቀነስ ይልቅ ‘በተወሳሰበ መልኩ እየተባባሰ መጥቷል’ ሲሉ የ"ታሊታ ኩም" ዓለም አቀፍ አስተባባሪ የሆኑት እህት አቢ አቬሊኖ፣ ሐምሌ 23 ቀን የሚከበረውን "ዓለም አቀፍ የሰዎች ዝውውርን የመከላከል ቀንን" አስመልክተው ለቫቲካን ኒውስ የገለጹ ሲሆን፥ የዘንድሮው የዕለቱ መሪ ቃል "የማጭበርበር ወጥመድ ውስጥ መውደቅ" የሚል እንደሆነም ጭምር ገልጸዋል።

የዓለም ቀን ከመከበሩ ቀደም ብሎ በገዳማዊያት እህቶች የሚመራው ዓለም አቀፍ ትስስር የሆነው ‘ታሊታ ኩም’ የአውሮፓዊያኑን የ 2025 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርቱን ያወጣ ሲሆን፥ ሪፖርቱ ይህ ዓለም አቀፍ ትስስር ባለፈው ዓመት ብቻ በመላው ዓለም የሚገኙ 1.21 ሚሊዮን ሰዎችን በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ ማገዙን ጠቅሶ፥ ይህ አሃዝ ከ 2024 ዓ.ም. ጋር ሲነፃጸር በ29.6 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ገልጿል።

ሆኖም ግን፣ የታሊታ ኩም እንቅስቃሴ እየጨመረ በመጣ ቁጥር፣ በአውሮፓ እና በኢስያ የሚታዩ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር እየጨመረ በመምጣቱ፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የማስቆም ተልዕኮ አሁንም አስቸኳይ እርምጃ እንደሚፈልግ ተመላክቷል።

የቴክኖሎጂ ጥቅሞች እና ጉዳቶች
የጎረጎሳዊያኑ የ 2025 ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን ተከትሎ እየተስፋፋ መምጣቱን ያመላከተ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር በኢንተርኔት የሚፈጸሙ ብዝበዛዎችና ማጭበርበሮች፣ ሰዎችን ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት የሚያገለግሉ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዘዴዎች መሆናቸውን ገልጿል።

"እኛ የምናገኛቸው በርካታ ተጎጂዎች በዲጂታል መድረኮች ውስብስብነት ምክንያት ወጥመድ ውስጥ የገቡ ናቸው” ያሉት እህት አቢ፥ በኦንላይን በርካታ ነገር ቃል እንደሚገባላቸው እና ስለ ምልመላ ሂደቶቹ ተጎጂዎቹን ማነጋገራቸውን ጠቅሰው፥ ነገር ግን በተጠቀሰው ቦታ ሲደርሱ ቃል የተገባላቸው ሥራ ውሸት ሆኖ እንደሚያገኙት እና ፓስፖርታቸው እንደሚወሰድባቸው፣ እንዲሁም ነፃነታቸው እንደሚነጠቅ አስረድተዋል።

“ይህ በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ያለ እውነታ ነው” ያሉት እህት አቢ፥ ወጣቶች የተሻለ የወደፊት ዕድል እና የተሻለ ሥራ ለማግኘት ስለሚፈልጉ፣ የወንጀል ድርጅቶች ይህንን ዲጂታል መድረክ በመጠቀም ወጣቶችን ወደ ወጥመድ ውስጥ እንደሚያስገቡ የገለጹ ሲሆን፥ በኦንላይን የሚፈጸሙ የማጭበርበሪያ መንገዶች መካከል ያለውን ግንኙነት የመለየት ሥራ የሚሰሩት ብቻቸውን እንዳልሆነ አክለው ጠቁመዋል።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኤሚ ፖፕ ሐምሌ 21 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ በተለይም በመላው ኢስያ የሚገኙ ተጎጂዎችን ጨምሮ ከ80 በላይ የተለያዩ ሀገራት ውስጥ ወንጀሉ እንደሚፈጸም ጠቅሰው፥ የኦን ላይን የማጭበርበሪያ ማዕከላት ቁጥር መጨመሩን አመላክተዋል።

ዳይሬክተሯ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መጠን እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፥ አዲስ የተቋቋመው የተባበሩት መንግስታት የአደንዛዥ ዕፅ እና የወንጀል መቆጣጠሪያ ቢሮ በበኩሉ፣ በማጭበርበር ወንጀሎች ምክንያት በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ኪሳራ እንደሚደርስበት ሪፖርት በማድረግ፥ በምስራቅ ኢስያ፣ በደቡብ ምስራቅ ኢስያ፣ በአውስትራሊያ እና በኒውዚላንድ በሚገኙት የማጭበርበር ሥራዎች የሚከናወኑባቸው ማዕከላት ውስጥ፣ በህገ-ወጥ መንገድ የተወሰዱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች እንደሚገኙ ያለውን ግምት አስቀምጧል።

የማጭበርበሪያ መንገዶችን መከላከል 
ታሊታ ኩም እነዚህን የማጭበርበር ተግባራት ለመዋጋት የሚሰራበት አንዱ መንገድ በኢንተርኔት የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ኢላማ የሆኑትን ሰዎች፣ በተለይም ወጣቶችን ማስተማር እንደሆነ ያመላከቱት እህት አቢ፥ ወጣቶችን ብቻ ሳይሆን በእነዚህ ዲጂታል መድረኮች ላይ ወጥመድ ውስጥ ሊወድቅ የሚችል ማንኛውንም ሰው ለማስተማር የታሊታ ኩም እንቅስቃሴን ለማጠናከር እየሞከሩ መሆኑን አስረድተዋል።

የታሊታ ኩም ዓለም አቀፍ አስተባባሪዋ አክለውም በታሊታ ኩም የወጣት አምባሳደሮች ፕሮግራም አማካኝነት ወጣቶች ስለ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ እንዴት መለየት እንደሚችሉ እና እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ ስልጠና እና ትምህርት እንደሚያገኙ ገልጸው፥ ከስልጠና በኋላም እነዚህ አምባሳደሮች እኩዮቻቸው ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ወደየአካባቢያቸው ማህበረሰቦች እና ሃገሮች እንደሚላኩ አስረድተዋል።

ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮችን መጠቀም በመጀመራቸው ምክንያት፣ ታሊታ ኩም በበኩሉ ይሄንን ተመሳሳይ መንገድ በመከተል የመከላከል ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ ትስስሩ ህዝቡን ስለ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋዎች ለማስተማር የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶችን መክፈቱን፣ እንዲሁም የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ፕሮግራሞችን መጀመሩን አመላክተዋል።

የመፍትሔው አካል
ይህ ዓመታዊ ሪፖርት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከመከላከል እና ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ከመደገፍ ጀምሮ እስከ ፍትህን ስለማግኘት፣ አጋርነት እና ተሟጋችነትን የመሳሰሉ ስለ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በርካታ ዘርፎችን ማካተቱን የገለጹት እህት አቢ፥ በተለይ ከአደጋው ለተረፉ ሰዎች የሚደረገውን ድጋፍ አጉልተው አንስተዋል።

“ከአደጋው የተረፉ ሰዎች የመፍትሔው አካል ናቸው” ያሉት አስተባባሪዋ፥ ጉዳዩ ሰለባዎቹን ከችግር ማውጣት ብቻ ሳይሆን፥ ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ፍላጎቶች ለማሟላት፣ ለተለያዩ ዕድሎች እንዲሁም ዘላቂ በሆነ መንገድ ከጎናቸው በመሆን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል መድረክ ማመቻቸት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከዚህ “ለተጎጂዎች ቅድሚያ ከሚሰጥ አካሄድ” ጎን ለጎን፥ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ዋና ዋና ምክንያቶች የሚለይ፣ ሰዎች ለምን በዚህ ወጥመድ ውስጥ እንደሚወድቁ እና ለምን እንደሚሰደዱ በማጥናት መፍትሄዎችን የሚሰጥ ሥርዓታዊ ለውጥ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡት እህት አቢ፥ ሰዎች ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱት በድህነት፣ በኢፍትሃዊ አሰራር፣ በግጭት እና በተለያዩ ምክንያቶች እንደሆነ ጠቅሰው፥ በዚህም ምክንያት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሌለበት ዓለም ለመገንባት አብሮ መጓዝ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዓለም አቀፍ አስተባባሪዋ በማከልም ይህንን ወንጀል ለማስቆም የሚደረገው ሥራ የሚጀምረው ከመሠረታዊ ደረጃ እንደሆነ ጠቁመው፥ በተለይም የህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ዓለም አቀፍ አዝማሚያ ውስብስብ እየሆነ በመምጣቱ የቅድመ መከላከል እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን ማስፋፋት፣ እንዲሁም ከአደጋው ለተረፉ ሰዎች ድጋፍ እና ጥበቃ ማድረግ አስፈላጊ ጉዳዮች መናቸውን አስረድተዋል።

ከዚህም ባሻገር፣ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ እና ከተለያዩ የሕይወት ዘርፎች የተውጣጡ ሰዎች ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚያስቀጥሉ መሰረታዊ ምክንያቶችን እንዲፈቱ የአካባቢ እና የዓለም መሪዎችን መወትወት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

ትምህርት ወሳኝ ሚና አለው
“ይህንን ወንጀል ማስቆም የሚቻል ቢሆንም፣ በአንድ ግለሰብ፣ በአንድ ሀገር ወይም በአንድ ተቋም ብቻ ሊከናወን የሚችል አይደለም” ያሉት እህት አቢ፥ ትምህርት ለዚህ ችግር መፍትሄ ከሚሆኑ ቁልፍ ነገሮች መካከል አንዱ እንደሆነ ጠቁመው፥ በጣም በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ህፃናት እንኳን ሳይቀሩ፣ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጉዳይ በዓለም አቀፍም ሆነ በአካባቢያዊ ሁኔታዎች ብቻ ሳይሆን፣ በማንኛውም መልኩ እና ደረጃ እንዴት እየተስፋፋ እንደሆነ መማር እንዳለባቸው መክረዋል።

የታሊታ ኩም ዓለም አቀፍ አስተባባሪዋ በመጨረሻም ‘ይህንን ዓለም አቀፍ ወንጀል ለማስቆም ወሳኝ የሆነው ሌላው ጉዳይ ከቁጥሮችና ከመረጃዎች ባሻገር፤ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች፣ ታሪኮችና ህይወቶች እንዳሉ መገንዘብ ነው’ ያሉ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት በጋራ መስራት የ«ታሊታ ኩም» ተልዕኮ ዋና መሰረት መሆኑን ጠቁመው፥ “ማንም ሰው እንደ ንብረት ወይም እንደ ሸቀጥ ሊታይ አይገባም” በማለት አጠቃለዋል።

30 Jul 2026, 15:34