አባ ፋልታስ ዌስት ባንክ ውስጥ ደም እየፈሰሰ መሆኑን ጠቅሰው ሁከቱን ለማስቆም ር.ሊ.ጳ. ሊዮ ያቀረቡትን ጥሪ ማዳመጥ ያስፈልጋል አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በቅድስት ሀገር ውስጥ ሁከት ዳግም እየተባባሰ መሆኑን የጠቆሙት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ ይህ ከዚህች ምድር ፈጽሞ ሊጠፋ ያልቻለው ሁከት ወደ ተከታታይ የበቀል እርምጃዎች እየተስፋፋ እንደሚሄድ፥ የሟቾችን እና የጥፋትን መጠን እንደሚጨምር፣ የሰላም ተስፋዎችን እንደሚያጠብ፣ እንዲሁም የሰውን አእምሮዎችን እና ልቦችን በእሾህ አጥር ውስጥ እንደሚቆልፋቸው ጠቅሰው፥ ዌስት ባንክ እየተቃጠለች፣ በደም እየተጨማለቀች እንዲሁም በህመም እና በመከራ እያቃሰተች መሆኑን አሳስበዋል።
ልክ እንደ ጋዛ ሁሉ፣ ዌስት ባንክም መጠኗን እና ቦታዎቿን ያጣች፣ ከዚህ በፊት ከነበረችበት ሁኔታ በመቀየሯ መጠኗን ለመለየት አስቸጋሪ የሆነች ግዛት መሆኗን ያመላከቱት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ በአካል እና በማህበራዊ ሁኔታ የተከፋፈለች፣ ጥልቅ በሆኑ ቁስሎች የተጎዳች እና ታሪካዊ ማንነቷ የተዋረደ ምድር ሆናለች ብለዋል።
ፍራንቺስካዊው ካህን በዚህች ምድር እያንዳንዱ ክፍል ላይ በየቀኑ ሁከት እና ጥፋት እንደሚደርስ ጠቁመው፥ እያንዳንዱ የአከባቢው ነዋሪ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ በሚሄድ የአስፈላጊ ቁሳቁሶች እጥረት፣ ገደቦች፣ መከራ እና ውርደት ውስጥ እንደሚኖር የገለጹ ሲሆን፥ ሰዎች ይፋ ባልሆነ ነገር ግን ቀጣይነት ባለው፣ የማያቋርጥ እና በስፋት በሚካሄድ ጦርነት እየሞቱ መሆኑን አሳስበዋል።
በመኖርያ ቤቶች እና በእርሻዎች ላይ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የእሳት አደጋዎች በየጊዜው እንደሚከሰት የገለጹት ካህኑ፥ ከተሞቹ እርስ በርስ በጣም የተቀራረቡ ቢሆኑም እንኳን በአሁኑ ወቅት ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ መጓዝ ፈጽሞ እንደማይቻል ጠቅሰው፥ ለድንገተኛ አደጋዎች ህክምና፣ ለሥራ፣ ዘመዶቻቸውን ለመርዳት፣ ወይም በአጥቂ እና በኃይለኛ ሰፋሪዎች በህገ-ወጥ መንገድ በተያዙ እና በተወሰዱ ትናንሽ የቤተሰብ ንብረቶች ላይ መብትን ለማስከበር ቢሆን እንኳን ከቦታ ቦታ መጓጓዝ እንደማይቻል ገልጸዋል።
አባ ኢብራሂም ፋልታስ አሳሳቢ፣ አደገኛ እና ለመፍታትም ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪ እየሆኑ የመጡ ችግሮችን በተመለከተ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የእርዳታ ጥያቄዎች እንደሚደርሷቸው አስታውሰው፥ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺህ በላይ የደረሱት በርካታ የፍተሻ ጣቢያዎች እና በአንድ ወቅት የፍልስጤም ህዝብን ታሪክ እና የዕለት ተዕለት ኑሮ ይወክሉ የነበሩት ቦታዎች ማለትም የለሙ መሬቶች፣ በጣም ሰፋፊ የወይራ እርሻዎች፣ መስክ ላይ የተሰማሩ ከብቶች፣ እንዲሁም በድምፅ፣ በቀለም እና በህይወት የተሞሉ ከተሞችና መንደሮች ላይ የሚገኙት በርካታ ጊዜያዊ የመንገድ መዝጊያ ኬላዎች የአካባቢው ገጽታ አካል ሆነው አዲስ እና አስከፊ ገጽታ መፍጠራቸውን ጠቅሰዋል።
ባለፉት ዓመታት እየተካሄዱ ያሉት የአይሁድ ሰፈራዎች የእያንዳንዱ መንደር እና የማህበረሰብ ህይወት መገለጫ የሆኑ ምልክቶችን አደጋ ላይ እንደጣሉ ያሳሰቡት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ እነዚህ ሰፈራዎች የፍልስጤማውያንን ህይወት የሚቃረኑ እና የሚያፈርሱ እንጂ የሚያቅፉ እንዳልሆነ የገለጹ ሲሆን፥ እነዚህ ህገ ወጥ ሰፈራዎች የወደፊት ህይወታቸውን እንኳን መገመት ያልቻሉ ወጣቶችን ተስፋ እንደሚያጨናግፉ፣ እንዲሁም የልጅነት ህልማቸውን እና የአሁኑን ህይወታቸውን ለመገንባት ጠንክረው የሚሰሩ ሰዎችን ተስፋ እንደሚያጨልሙ የጠቆሙት ካህኑ፥ ከዚህም ባሻገር መሬታቸው ሲቃጠል፣ እንቅስቃሴያቸው ሲገደብ እና ህይወታቸው ትርጉም ሲያጣ የሚመለከቱ ህፃናትን ፈገግታ እና ህልም እንደሚያጠፉ አስረድተዋል።
“በአከባቢው በተከሰተው ችግር ምክንያት ወላጆች መደበኛ የህክምና ክትትል የሚያስፈልጓቸው ልጆቻቸውን ወደ ሆስፒታል መውሰድ አልቻሉም” ያሉት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ ወንዶች እና ሴት ልጆች በእድሜ የገፉ እና በህመም ላይ የሚገኙ ወላጆቻቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ የገለጹ ሲሆን፥ በተዘጉ መንገዶች ምክንያት አባቶች ወደ ሥራ መሄድ እንዳልቻሉ አስታውሰው፥ እነዚህ በዌስት ባንክ ውስጥ ለወራት አልፎ ተርፎም ለዓመታት የቆዩ ሁኔታዎች መሆናቸውን አመላክተዋል።
በዚህም የተነሳ ህዝቡ ተስፋ በመቁረጥ እና በፍርሃት ውስጥ እንደሚገኝ አሳስበው፥ ይህ ሁኔታ የተከሰተው ያለምንም ተጠያቂነት ፍርሃትን እና ሽብርን በሚዘሩ ሰፋሪዎች በሚፈጸሙ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ወረራዎች ምክንያት እንደሆነ አስረድተው፥ እነዚህ ምስኪን ሰዎች በገዛ ቤታቸው ውስጥ እንኳን መጠለያ ወይም ደህንነት ማግኘት እንዳቃታቸው ገልጸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ግጭትን ለማስቆም ያቀረቡት ተደጋጋሚ እና ጠንካራ ጥሪ በሁሉም ዘንድ ሊሰማ ይገባል ያሉት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ ይህ ጥሪ ሁከቱን በሚፈጽሙትም ሆነ ይህንን ማለቂያ የሌለውን የሁከት ዑደት ለማስቆም ጣልቃ በማይገቡት ዘንድ ሊሰማ እንደሚገባ መክረዋል።
በእስራኤል እና በፍልስጤም በመጪዎቹ ወራት እንደሚካሄዱ የተገለጹት ምርጫዎች ለሁለቱም ህዝቦች አዲስ ሚዛን እና እውነተኛ ፍትህን ሊያመጡ እንደሚገባ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ “የታሪክ አካሄድ ሊለወጥ ይችላል የሚለው ተስፋ በእግዚያብሄር ላይ እምነት እና ተስፋ ባላቸው ሰዎች ልብ ውስጥ ሁሌም ይኖራል” በማለት አጠቃለዋል።