የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የካሜሩን ሐዋርያዊ ጉብኝት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የካሜሩን ሐዋርያዊ ጉብኝት 

የካሜሩን ሊቀ ጳጳስ በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን ኢሰብዓዊ የማረሚያ ቤቶች አያያዝ እና ሙስናን አወገዙ

በካሜሩን የዶዋላ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ክሌዳ ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ታትሞ በወጣው ሃዋሪያዊ ደብዳቤያቸው በሃገሪቱ ውስጥ እየታየ ያለውን የማረሚያ ቤት አያያዝ ሁኔታዎችን ያወገዙ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ በሃገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ስላለው የአፈና፣ የዘፈቀደ እስራት እና ኢሰብዓዊ የሆኑ የእስር ቤቶች ሁኔታዎችን አስመልክተው ‘የማንቂያ ደወል’ ማሰማታቸውን የቫቲካን ዜና ወኪል 'ፊደስ' ዘግቧል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“የህግ ታራሚዎችን የምንይዝበት መንገድ ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ግንኙነት መለኪያ ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ሳሙኤል፥ የእስረኞችን ስቃይ ችላ ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ችላ ማለት እንደሆነ አስታውሰው፥ ስቃያቸውን ለማቃለል እና ፍትህን ወደነበረበት ለመመለስ ራሳችንን መስጠት ክርስቶስን ማገልገል እንደሆነ አስረድተዋል።

የካሜሩን ሊቀ ጳጳስ ሳሙኤል ክሌዳ በሃገሪቱ ውስጥ እየተስተዋለ ስላለው አስከፊ የእስር ቤት ሁኔታዎችን አስመልክተው ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ታትሞ በወጣው ሃዋሪያዊ ደብዳቤያቸው ላይ ይህንን ማሳሰቢያ ማቅረባቸውን የቫቲካን የዜና ወኪል ፊደስ ኒውስ የዘገበ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ያለውን “ታስሬ በነበረበት ወቅት ልትጠይቁኝ መጥታችኋል” የሚለውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አስተምህሮ በማስታወስ፥ ሃዋሪያዊ ደብዳቤው ከንትርክ መንፈስ የመነጨ ሳይሆን ከግዴታ እና ከአስቸኳይ የርህራሄ ስሜት የመነጨ የእውነት እና የሃዋሪያዊ ፍቅር ተግባር መገለጫ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ እንደነበር አብራርተዋል።

ስልታዊ ኢፍትሃዊነት

የዚህ ደብዳቤ ዓላማ በበርካታ ካሜሩናዊያን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን የእስራት፣ እገታ እና እንግልት ዙሪያ ያለውን ስልታዊ ኢፍትሃዊነት ተግባር ማውገዝ እንደሆነ የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፥ ይህ ሃዋሪያዊ ደብዳቤ በህዝቡ ላይ የሚደርሰውን የጠለፋ እና የአፈና ድርጊቶች፣ በፖሊስ ጣቢያዎች እና በእስር ቤቶች ውስጥ የሚፈጸመውን አዋራጅ እና ኢሰብዓዊ ተግባራት፣ መላውን የፍትህ ስርዓት የሚያጠቃውን ሙስና እና በተደጋጋሚ የሚስተዋሉ የህግ ጥሰቶችን ለማጋለጥ ጥረት እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

ሊቀ ጳጳስ ሳሙኤል በቃለ ምልልሳቸው ወቅት በሃገሪቷ ውስጥ ደብዛቸው የጠፉ ሰዎችን ሁኔታ በማስታወስ በርካታ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የፖሊስ ልብስ በማይለብሱ ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ እንደሚታሰሩ እና እንደሚታፈኑ የገለጹ ሲሆን፥ እነዚህ ታፍነው የተወሰዱ ዜጎች ሚስጥራዊ በሆነ ቦታ እንደሚታሰሩ፣ ስልኮቻቸው እንደሚዘጋ እና ዱካቸው ጭምር እንደሚጠፋ አስረድተዋል።

ብፁዕነታቸው ከዚህም በተጨማሪ በፍርሃት የተዋጡ ቤተሰቦቻቸው ከአንዱ ፖሊስ ጣቢያ ወደ ሌላኛው፣ ከፍርድ ቤት ወደ እስር ቤት እንደሚንከራተቱ እና በዚህም ወቅት በህግ አስከባሪ አካላት የተለያዩ ዛቻዎች እንደሚያጋጥማቸውም ጭምር ገልጸዋል።

'ግልጽ የሆነ የህግ ጥሰት'

“ይህ በማይታወቁ እና አንዳንዴም መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች በሚስጥር የማሰር ተግባር ግልጽ የሆነ የሕግ ጥሰት ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ሳሙኤል፥ በመቀጠልም በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ህጋዊ እስር ቤቶች ውስጥ የሚስተዋሉ አስከፊ ሁኔታዎችን በማውገዝ፥ የህክምና አገልግሎት ማግኘት “ከቅዠት ብዙም የማይለይ ነገር” መሆኑን በመጠቆም የእስር ቤቶቹ ክሊኒኮች በቂ መሳሪያ የሌላቸው እና የህክምና ባለሙያዎች እጥረት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

የሳንባ ነቀርሳ፣ የቆዳ በሽታዎች እና ታይፎይድን የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መልኩ መሰራጨታቸውን በቁጭት ያመላከቱት ሊቀ ጳጳሱ፥ የኤችአይቪ ወይም የስኳር በሽታ ያለባቸው እስረኞች ህክምና ባለማግኘታቸው የጤንነታቸው ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ እያሽቆለቆለ መሆኑን ገልጸዋል።

የቫይታሚኖች እና የካሎሪ ጉድለት ያለበት የእስር ቤቶቹ ምግብ ጤንነታቸው ቀድሞውኑ የተዳከመውን የህግ ታራሚዎችን ለማቆየት በቂ እንዳልሆነ ያመላከቱት ሊቀ ጳጳሱ፥ በዚህም ምክንያት ታራሚዎቹ በሕይወት የመትረፋቸው እድል አብኛውን ጊዜ በዘመድ አዝማድ ወይም በእስር ቤት ውስጥ በሚከናወነው ሙስና ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለሴቶች እና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ስጋት

ከዚህም ባሻገር ሊቀ ጳጳስ ሳሙኤል ክሌዳ ለሴቶች እና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ትልቅ ስጋት እንዳላቸውም ጭምር ገልጸው፥ በእስር ላይ የሚገኙ ሴቶች ‘መሰረታዊ የሴት ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን እንደማያገኙ በምሬት የገለጹ ሲሆን፥ አንዳንዶቹ እናቶች ከጨቅላ ህፃናቶቻቸው ጋር አብረው እንደሚታሰሩ ጠቁመው፥ ይህ ተግባር ህፃናቱ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከማረሚያ ቤት ሲወጡ የወደፊት እጣ ፈንታቸው አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ያላቸውን ስጋት በአጽንዖት ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳሱ ከአዋቂዎች ተለይተው ተገቢው የትምህርት ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገቡ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህፃናት ችላ እንደተባሉ፣ ለአዋቂዎች ብቻ ለተዘጋጁ ህጎች፣ እንዲሁም ለተለያዩ ጥቃቶች እና ብዝበዛ እንደሚጋለጡ አስታውሰው፥ እነዚህ የመብት ጥሰቶች ሊፈጸሙ የሚችሉት “በሙስና እና ፍትህን በማጣመም ነው” ሲሉ አስምረውበታዋል።

ሊቀ ጳጳሱ ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ከፍርድ በፊት ለእስር የሚዳረጉበትን አሰራሮች በማውገዝ፣ ልዩ የሆነ ጉዳይ ሲከሰት ብቻ መፈጸም የነበረበት ነገር የተለመደ አሰራር እየሆነ መምጥቱን የገለጹ ሲሆን፥ በዚህ አሰራር ንፁህ እንደሆኑ የሚታሰቡ ሰዎችን ወንጀለኛ በማስመሰል የእስር ጊዜያቸው አብዛኛውን ጊዜ ለዓመታት እንደሚቆይ አመላክተዋል።

ይህ ፍትህን የመከልከል አካሄድ ድርብ ጉዳትን እንደሚያስከትል የጠቆሙት ሊቀ ጳጳሱ፥ የመጀመሪያው ነፃነትን መንፈግ እንደሆነ ጠቅሰው ሁለተኛው ጉዳት በተመጣጣኝ ጊዜ ውስጥ ፍትሃዊ የፍርድ ሂደት የማግኘት መብትን መከልከል እንደሆነ አሳስበዋል።

ሰብዓዊ ክብር እንዲጠበቅ የቀረበ ጥሪ

ሊቀ ጳጳስ ሳሙኤል ክሌዳ በመጨረሻም አንድን ሰው በህግ ቁጥጥር ሥር ማዋል ወይም እስራት ማለት ማህበረሰቡን ለመጠበቅ የሚደርግ ድርጊት መሆኑን፣ እንዲሁም ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸው ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸው ሙሉ በሙሉ በተጠበቀ መንገድ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ወደ ማህበረሰቡ በአግባቡ መቀላቀል እንዲችሉ የሚያስፈልጓቸውን ክህሎቶች እንዲያገኙ፣ እንዲጸጸቱ እና እንዲማሩ የሚያስችል አካባቢ መሆን እንዳለበት በድጋሚ በማሳሰብ፥ የህግ ታራሚዎችን በክብር እና በተገቢ ሁኔታ እንዲይዙ ለሚመለከታቸው አካላት ጥሪ በማቅረብ አጠቃለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከሚያዝያ 5 እስከ 15 ቀን 2018 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ አራት የአፍሪካ አገሮች ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት ካሜሩንን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

 

 

08 Jul 2026, 16:27