ካርዲናል ግራሲያስ ‘ሲኖዶሳዊነት ለዓለም ስጦታ ነው’ ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
12ኛው ጠቅላላ የኢስያ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን ጉባኤ ሐምሌ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. ጃካርታ በሚገኘው ሙሊያ የእንግዳ ማረፊያ አዳራሽ ውስጥ በተካሄደ የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ የተከፈተ ሲሆን፥ ይሄንን የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ የመሩት ብፁዕ ካርዲናል ግራሲያስ የቤተክርስቲያኒቱ ተልዕኮ ሰዎችን አንድ ላይ ማሰባሰብ፣ እርቅን ማበረታታት እና የሰላም መሳሪያ መሆን እንደሆነ ተናግረዋል።
“ተልዕኳችን የሰላም፣ የእርቅ እና የአንድነት ድልድይ መገንባት ነው” ሲሉ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን ወቅት የተናገሩት ካርዲናሉ፥ ቤተክርስቲያኒቱ ድልድዮችን ለመገንባት መጠራቷን ጠቁመዋል።
የመክፈቻው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ይሄንን ብዝሃነት የሚያንፀባርቅ ሲሆን፥ ሥነ ስርዓቱ ከመላው ኢንዶኔዥያ የመጡ ባህላዊ ልማዶችን እና ሰፊውን የኢስያ ቤተክርስቲያንን የሚወክሉ ጸሎቶችን ማካተቱ ተነግሯል።
ካርዲናል ግራሲያስ መስዋዕተ ቅዳሴውን የሆንግ ኮንግ ጳጳስ ከሆኑት ብፁዕ ካርዲናል እስጢፋኖስ ቾው ሳው-ያን እና ከቲሞር-ሌስቴ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ቨርጂሊዮ ዶ ካርሞ ዳ ሲልቫ ጋር በመሆን ያሳረጉ ሲሆን፥ ከመላው ኢስያ የመጡ ከ100 በላይ ብፁዓን ካርዲናሎች፣ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያት እና ልዑካን ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ጉባኤ ላይ መገኘታቸው ተገልጿል።
የመግቢያ ዑደት ሲጀመር የኒያስ፣ የባታክ እና የሚናንግካባው ማህበረሰብ አባላትን ጨምሮ ከኢንዶኔዥያ ሰሜናዊ ሱማትራ ግዛት የመጡ ወንዶች እና ሴቶች ጳጳሳቱን እና ልዑካኑን ወደ ስብሰባ አዳራሹ በማጀብ አቀባበል ያደረጉ ሲሆን፥ ባህላዊ አቀባበሉ የኢንዶኔዥያንን የበለፀገ የጎሳ ትውፊት አጉልቶ እንዳሳየ እና የአስተናጋጇን ቤተክርስቲያን እንግዳ ተቀባይነትም ጭምር ማሳየቱ ተመላክቷል።
የምዕመናን የጸሎት መርሃ ግብሩ የኢስያን ብዝሃነት የበለጠ እንዳንጸባረቀ የተነገረ ሲሆን፥ የጸሎቱ መርሃ ግብር የጃቫኔዝ፣ ሜንታዋይ፣ ማንዳሪን ወይም ቻይንኛ እና የቤናዋስ ዳያክ ቋንቋዎችን ጨምሮ በተለያዩ ቋንቋዎች የተደረገ ሲሆን፥ ከቦርኒዮ የመጡ የቤናዋስ ዳያክ ጎሳዎች እንዲሁም ከምስራቅ ኑሳ ተንጋራ የመጡ ሱምባኔዛዊያንን እንደተሳተፉበትም ጭምር ተገልጿል።
ከዚህም ባሻገር በእነዚህ በርካታ ቋንቋዎች የቀረቡት ምልጃዎች በአህጉሪቱ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ህዝቦች፣ ባህሎች እና ቋንቋዎች መካከል ያለውን የቤተክርስቲያን አንድነት አጉልተው ያሳያሉ ተብሏል።
ሌላው የበዓሉ ልዩ ገጽታ ከመላው ኢስያ የተውጣጡ ቅዱሳን ወንዶችንና ሴቶችን ያሳተፈው የቅዱሳን ጸሎት መርሃ ግብር ሲሆን፥ በዚህም ጉባኤው ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከጃፓን፣ ከኮሪያ፣ ከማሌዥያ፣ ከፊሊፒንስ፣ ከስሪላንካ፣ ከሆንግ ኮንግ፣ ከታይላንድ፣ ከማይናማር፣ ከካዛክስታን፣ ከኢንዶኔዥያ፣ ከላኦስ እና ከአፍጋኒስታን ለተውጣጡ ቅዱሳን አማላጅነት በመጸለይ የአህጉሪቱን የበለጸገ የክርስትና ቅርስነት አጉልቶ ማሳየቱ ተገልጿል።
ብፁዕ ካርዲናል ግራሲያስ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን የኢስያ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን ጉባኤ ከተቋማዊ ስብሰባ በላይ መሆኑን ለተሳታፊዎች አስታውሰው፥ በዚህ ጉባኤ የኢስያ አብያተ ክርስቲያናት የጊዜውን ምልክቶች የመለየት እና ወንጌልን የማወጅ ቁርጠኝነታቸውን የሚያድሱበት መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የኢስያ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን ታሪክ በማንሳት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የተከሰተ ለቤተክርስቲያኗ ወሳኝ ፈተናዎች ውስጥ አንዱ እንደሆነ አስታውሰው፥ ቀውሱ በአህጉሪቱ ውስጥ መከራን ቢያመጣም፣ የኢስያ አብያተ ክርስቲያናትን የመቋቋም፣ የአብሮነት እና የትብብር መንፈስንም ጭምር ማሳየቱን በአጽንዖት ገልጸዋል።
ብፁዕ ካርዲናሉ ጦርነት እና ዓመፅ ዛሬ የሰው ልጅ ከሚያጋጥሟቸው ታላላቅ ፈተናዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ጠቁመው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ስለአሁኑ ዓለም አቀፍ ሁኔታ “በክፍልፋይ የሚካሄድ ሦስተኛ የዓለም ጦርነት” ሲሉ የገለጹትን አስታውሰዋል።
ሲኖዶሳዊነት ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለኅብረተሰቡ ትልቅ ስጦታ እንደሆነ የገለጹት ካርዲናል ግራሲያስ፥ አብሮ የመጓዝ መንፈስ በቤተሰብ ሕይወት፣ በማኅበረሰባዊ እሴቶች እና በመተሳሰብ የተሞላ መከባበር አማካኝነት ለረጅም ጊዜ የኢስያ ባህሎች አካል ሆኖ መቆየቱን አስታውሰው፥ ማዳመጥ፣ ተሳትፎ፣ ግልጽነት እና የጋራ ኃላፊነት የመሳሰሉ የሲኖዶሳዊነት እሴቶች ለመልካም አስተዳደር እና በኢስያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ሙስናን ለመቅረፍ አስተዋጽዖ ሊያደርጉ እንደሚችሉ በማከል ገልጸዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ግራሲያስ በመጨረሻም ልዑካኑ በመላው አህጉሩ ሰላምን እና ወንድማማችነትን ለመገንባት አዳዲስ እና የፈጠራ መንገዶችን እንዲፈልጉ በማበረታታት፥ “እግዚአብሔር የኢስያ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽንን እና ኢስያን ይባርክ” በማለት አጠቃለዋል።