በናይሮቢ ኬንያ በመካሄድ ላይ የሚገኝ የምሥራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ተካፋዮች በናይሮቢ ኬንያ በመካሄድ ላይ የሚገኝ የምሥራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ተካፋዮች 

21ኛው የምስራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባኤ በኬንያ እየተካሄደ ይገኛል

በየአራት ዓመቱ በሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት እና ተወካዮች ሐምሌ 11 ቀን 2018 ዓ.ም. ናይሮቢ ኬንያ የገቡ ሲሆን፥ ልዑካን ቡድኑ በጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በአሜስያ ጽህፈት ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና በወጣቶች ደማቅ ባህላዊ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተነግሯል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

መቀመጫውን ናይሮቢ ኬንያ ያደረገው የምስራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ - አሜሲያ (Association of Member Episcopal Conferences in Eastern Africa) በመላው ምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች አባል የሆኑበት ትልቅ ተቋም ሲሆን፥ ይህ ጉባኤ በዋናነት የሚያተኩረው በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል ባለው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ህብረት ላይ እንዲሁም የሃይማኖት አባቶችን በማስተባበር በህዝቦች መካከል ሰላምን፣ ፍትህን እና ልማትን ለማምጣት በጋራ እንደሚሰራ ይታወቃል።

በብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ የተመራው የልዑካን ቡድኑ ከሐምሌ 11 - 19 ቀን 2018 ዓ.ም በኬንያ የጳጳሳት ጉባኤ መሪነት በተዘጋጀው 21ኛው የምስራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባኤ ለመሳተፍ ኬንያ የገባው ሃምሌ 11 ሲሆን፥ ጉባኤው የዘጠኝ ቀናት ቆይታውን ናይሮቢ በሚገኘው በምስራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ዩኒቨርስቲ ውስጥ እንደሚያካሂድ እና መሪ ቃሉም “ሲኖዶሳዊ ጉዞ ከወጣቶች ጋር እና መልካም አስተዳደር” የሚል እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ጉባኤው ላይ የሚሳተፉት ከአባል ሀገራት የተወከሉ ብፁዓን ጳጳሳት፣ ወጣቶች፣ ገዳማውያን፣ ምዕመናን እና ግብዣ የተደረገላቸው ሰዎች እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በመወከል ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ ብፁዕ አቡነ ሙሴ የቀድሞ የእምድብር ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የጅማ ቦንጋ ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የእምድብር ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ደጀኔ የሶዶ ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሚልኪያስ የነቀምቴ ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ክቡር አባ ከተማ አስፋው የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸኃፊ፣ ክቡር አባ አብርሃም ገብረማርያም የሐዋሪያዊ ሥራዎች አስተባባሪ፣ እንዲሁም የምዕመናን፣ የወጣት ተወካዮች እና የሚዲያ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ

በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ዘንድሮ በኬንያ አዘጋጅነት ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. በይፋ የተከፈተ ሲሆን፥ ጉባኤው የዘጠኙን አባል ሀገራት ብፁዓን ጳጳሳትን ያቀፈ መሆኑ እና በመክፈቻ ጉባኤውም ከመቶ በላይ የሚሆኑ ብፁዓን ጳጳሳት መገኘታቸው ተገልጿል።

21ኛው የምስራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባኤ የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ የተካሄደው ኬንያ በሚገኘው የምስራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ሲሆን፥ በዚህ የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከብፁዓን ጳጳሳቱ በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ በኬንያ ከሚገኙ የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች እና ቁምስናዎች የተሰባሰቡ ምዕመናን እና እጅግ በርካታ ወጣቶች ተገኝተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ሚካኤል የቅድስት መንበር ሁለንተናዊ የሰው ልጅ እድገት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴውን ያሳረጉ ሲሆን፥ የኬንያ ጳጳሳት ጉባኤን በመወከል ብፁዕ አቡነ ሙሄሪያ ከአባል ሀገራት የተወከሉ ጳጳሳትን፣ የቅድስት መንበር ተወካዮችን እና ከመላው ዓለም ለጉባኤው የመጡ እንግዶችን አስተዋውቀዋል።

“ሲኖዶሳዊ ጉዞ ከወጣቶች ጋር፤ የአንድነት፣ የተስፋ፣ የፍትህ እና የመልካም አስተዳደር ድልድይን መገንባት” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ጉባኤ አባል ሀገራቱ በዋነኝነት ሐዋርያዊ ጉዳዮችን በማስቀደም የሚወያዩ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር በቀጠናው ያሉትን ማህበራዊ ጉዳዮች በማንሳት የጋራ የቤተክርስቲያን አቅጣጫ ያቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በምስራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ዩኒቨርስቲ የኬንያ ፕሬዝደንት ክቡር ዊሊያም ሩቶን በመወከል ክቡር ሚኒስትር ሙሳሊያ ሙዳቫዲ በተገኙበት በይፋ የተከፈተው የዘንድሮው 21ኛ የምስራቅ አፍሪካ የብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ በወጣቶች ህይወት ላይ በማተኮር ቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊ በሆነ መንገድ ከወጣቶች ጋር እንዴት መጓዝ እንደምትችል የሚወያይ ሲሆን፥ የወጣቶች ሥራ ማጣት፣ ከማህበረሰብ የመገለል፣ ስደት፣ የአቻ ግፊት እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ከብዙዎቹ በጥቂቱ የሚነሱ ጉዳዮች እንደሆኑ እና ጉባኤው ወጣቶችን በማዳመጥ አዲስ ተስፋ እና የመፍትሄ ሀሳቦችን ለማቅረብ ከሁሉም አባል ሀገራት ከተወከሉ ወጣቶች ጋር በቀጣይ ቀናት ቆይታ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በ21ኛው የምስራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ስርዓት ላይ የአባል ሀገራት ብፁዓን ጳጳሳት፣ የኬንያ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ በኬንያ የቅድስት መንበር ተወካይ፣ አምባሳደሮች፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንቶች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች፣ ከየሀገራቱ የተወከሉ ባለሙያዎች እና ግብዣ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን፥ ጉባኤው በዩኒቨርስቲው ዋና አዳራሽ በብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ የመክፈቻ ጸሎት ተጀምሯል።

ብፁዕ አቡነ ቻርልስ ካሶንዴ የምስራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ለተሳታፊዎች እና ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት እና የ21ኛውን ጉባኤ መሪ ቃል ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን፥ ክቡር ሚኒስትር ሙሳሊያ በበኩላቸው ጉባኤው ኬንያ በመካሄዱ ደስታቸውን በመግለጽ፥ ጉባኤው ዋና ትኩረቱን በወጣቶች ላይ ማድረጉ ጊዜውን ያማከለ እና ለዚህ ዘመን ወጣቶች ተስፋ ሰጪ መሆኑን አስረድተዋል።

ህብረቱ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለምታከናውናቸው ሐዋሪያዊና ማህበራዊ ሥራዎች ብዝሀነትን ማስተናገድ እንዲቻል በቀጠናው ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሁፎችም በሊቃውንት በማቅረብ የሚመክርበት ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላም እና ትብብር ለመፍጠር ከሌሎች የእምነት ተቋማት፣ ከመንግስታትና ከአፍሪካ ህብረት ጋር መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም በቀደሙት ጉባኤዎች ሲመክር እንደነበረ ይታወሳል። መቀመጫውን ናይሮቢ ኬንያ ያደረገው የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ህብረት የተመሰረተው የታንዛኒያ ብፁዓን ጳጳሳት በዚያን ወቅት በዚህ ክልል ውስጥ በቤተክርስቲያንም ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ የለውጥ አዝማሚያዎች ይነፍሱ ስለነበር እ.አ.አ. በ 1960 ዓ.ም. በናይሮቢ በሚገኘው የቀድሞው የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ልዑክ ጽህፈት ቤት በኩል በአካባቢው በሚገኙ የካቶሊክ ጳጳሳት መካከል ትብብር እንዲኖር ሐሳብ ማቅረባቸውን ተከትሎ እ.አ.አ. በ 1961 ዓ.ም. የተመሰረተ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተቋም ሲሆን፥ ይህ ጉባኤ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል የወንጌል ስርጭትን ለማጠናከር፣ ማህበራዊ ፍትህን ለማስፈን፣ የሰላም ግንባታ እና አጠቃላይ የህብረተሰብ ልማት ለማምጣት የሚሰሩ የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳትን አንድ የሚያደርግ ተቋም ሲሆን፥ በየአራት ዓመቱ አንዴ የሚካሄደውን ይህንን ጉባኤ ካስተናገዱ ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ 19ኛውን ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ማስተናገዷ ይታወሳል።

የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ ዘጠኝ ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ማላዊ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ እና ዛምቢያ ውስጥ ያሉ ብሔራዊ የጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት የሆነ የካቶሊክ አገልግሎት ድርጅት ሲሆን፥ ሶማሊያ እና ጅቡቲ ተባባሪ አባላት እንደሆኑ ይታወቃል።

  

 

 

 

 

21 Jul 2026, 17:09