ፈልግ

የሃኖይ ቅዱስ መስቀል ወዳጆች ገዳም እህቶች የሃኖይ ቅዱስ መስቀል ወዳጆች ገዳም እህቶች  

የሃኖይ ቅዱስ መስቀል ወዳጆች ገዳም እህቶች ለሰው ልጅ ክብር እንደሚገባ ወንጌል ይመሰክራል አሉ

የቬትናም ዋና ከተማ ከሆነችው ሃኖይ ከተማ ውጭ በሃገሪቷ ሰሜናዊ ክልል ውስጥ የሚገኙት የቅዱስ መስቀል ወዳጆች ገዳም እህቶች እጅግ የተገለሉ ሰዎችን ሰብዓዊ ክብር ለማበረታታት እና ለመጠበቅ የእግዚአብሔርን ፍቅር እያጋሩ እንደሚገኝ ተገልጿል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በዘመናዊቷ ቬትናም ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በቁሳዊ እሴቶች ላይ ያተኮሩበት እና በአቋራጭ ሀብትን የማግኘት ፍላጎት እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት ለጋራ ጥቅም መቆርቆር እና ለሰብዓዊ ክብር እውቅና መስጠት እየቀነሰ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህም የተነሳ የራስ ወዳድነት አዝማሚያ እየተንሰራፋ በመምጣቱ በእነዚህ ግቦች መንገድ ላይ የሚቆሙትን ሰዎች ማግለል እየተስተዋለ መምጣቱ ተነግሯል።

በጣም ተጋላጭ ከሆኑት መካከል ለህብረተሰቡ ምንም የማይጠቅሙ ሸክም ተደርገው የሚታዩት አካል ጉዳተኞች እና አዛውንቶች ሲሆኑ፥ በተለይም የወንድ የበላይነትን በሚያከብር ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ሴት ልጆች እና ህፃናት እንዲሁም በቬትናም ገጠራማ አከባቢዎች የሚኖሩ ድሆች እና አናሳ ጎሳዎች የችግሩ ሰለባ መሆናቸው ተነግሯል።

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሃኖይ የቅዱስ መስቀል ወዳጆች ማህበር (LHC) እህቶች በአከባቢው ላይ በሚሰጡት ሃዋሪያዊ አገልግሎት በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው አቋም ወይም ሁኔታ ምንም ይሁን ምን የሁሉንም ሰው ትክክለኛ ሰብዓዊ ክብር እንደሚገነዘቡ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ በመሆኑም ምክንያት የማህበሩ እህቶች የድሆችን፣ የተገለሉትን፣ የአረጋውያንን እና ጥበቃ የሌላቸውን ሰዎች ክብር ለመገንዘብ እና ለማክበር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እየሰሩ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ራሳቸውን እንዲንከባከቡ ማስተማር

የሃኖይ የቅዱስ መስቀል ወዳጆች ገዳም እህቶች የተገለሉ ሰዎችን ስቃይ ለመቅረፍ እና ሰብዓዊ ክብራቸውን ለማስጠበቅ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ‘የፍቅር ቤት’ የተሰኘ የማህበረሰብ ተቋም በመክፈት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እያደረጉ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ገዳማዊያት እህቶቹ በዚህ ቤት ውስጥ አስቸጋሪ ህይወት እና ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙትን ዓይነ ስውራንን፣ የነርቭ ችግር ያለባቸውን እና በተለያየ ምክንያት አካለ ስንኩል የሆኑ ሰዎችን የመሳሰሉ ረዳት የሌላቸው አካል ጉዳተኞችን እና አረጋዊያንን የሚቀበሉ ሲሆን፥ በዚህ ረገድ ‘የፍቅር ቤት’ ተብሎ በሚጠራው ወደዚህ ማዕከል የሚመጡ ሰዎች በእህቶች እንክብካቤ እንሚደረግላቸው ተነግሯል።

ወደዚህ ማዕከል የሚመጡ ሰዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች የገጠሟቸው ወይም በቤተሰቦቻቸው እንክብካቤ የማይደረግላቸው ሰዎች መሆናቸውን የገለጹት በማዕከሉ ውስጥ የሚሰሩት እህት ፎንግ ንጉዬን፥ በዚህም ምክንያት የተጎጂዎቹ ቤተሰብ አባላት ልጃቸውን ወይም ዘመዶቻቸውን ለእህቶቹ አደራ እንደሚሰጡ አስረድተዋል።

እህት ፎንግ በዚህ ማዕከል ውስጥ ገዳማዊያቱ በተቻለ መጠን ሰዎቹ ራሳቸውን እንዴት መንከባከብ እንደሚችሉ በትዕግስት እንደሚያስተምሯቸው ገልጸው፥ በዚህ ቤት ውስጥ ለሚኖሩ እና ተመላላሽ ለሆኑ ሰዎች ገዳማዊያት እህቶቹ ዕለታዊ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ፣ ምግብ ማዘጋጀት፣ ለሽያጭ የሚቀርቡ በእጅ የተሰሩ እቃዎችን እና ጣፋጭ ምግቦችን ማዘጋጀት የመሳሰሉ የዕለት ተዕለት የቤት ውስጥ እንቅስቃሴዎች ውስጥ  እንዲሳተፉ ያበረታቷቸዋል ተብሏል።

እነዚህ ተግባራት ልጆች በመንፈሳዊ ህይወታቸው እንዲያድጉ ብቻ ሳይሆን ከማህበራዊ ሕይወት ጋር እንዲዋሃዱ ይረዷቸዋል የተባለ ሲሆን፥ በዚህ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ፍቅር እየተለማመዱ ለማህበረሰቡ እና በዚህ ቤት ውስጥ ለሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ጠቃሚ እንደሆኑ ይገነዘባሉ ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ አብሮነትን ለማጎልበት እና አብረዋቸው በፍቅር ቤት ውስጥ ከሚኖሩት ሰዎች ጋር የመተሳሰብ እና የመረዳዳት ባህልን እንዲያዳብሩ ገዳማዊያት እህቶቹ እንደሚያበረታቷቸው፥ ለአብነትም ቢያንስ ከሌሎቹ በጥንካሬ የተሻሉ ሰዎች አካል ጉዳተኞችን እንዲረዱ፣ እንዲሁም መራመድ የሚችሉት በዊልቼር የሚንቀሳቀሱትን እንዲያግዙ እንደሚያበረታቱ የተገለጸ ሲሆን፥ በእነዚህ ትናንሽ ምልክቶች አማካይነት በማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በሌሎች ዘንድ እንደሚወደዱ፣ እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው እና በአነስተኛ ማህበረሰባቸው ውስጥ ጠቃሚ ሰዎች መሆናቸው እንዲሰማቸው ይደረጋል ብለዋል።

ድሆችን መደገፍ

ከዚህም ባሻገር የሃኖይ የቅዱስ መስቀል ወዳጆች ገዳም እህቶች ለድሆች የጤና አገልግሎትን እንደሚሰጡ የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት የቺ ሎንግ ማህበረሰብ በሃኖይ የቅዱስ መስቀል ወዳጆች ጉባኤ ከሚደገፉት ውስጥ እንዱ እንደሆነ እና በማዕከሉ ውስጥ ገዳማዊያን እህቶቹ የጤና ምርመራ ቀናትን በማዘጋጀት በካቶሊኮች እና ካቶሊክ ባልሆኑት መካከል ልዩነት ሳይፈጥሩ ለአካባቢው ህሙማን ነፃ መድሃኒት እንደሚሰጡ ተገልጿል።

እነዚህ የገዳማዊያኑ ጥረቶች ሀብታቸውን እና ጊዜያቸውን በሚሰጡ በጎ አድራጊዎች እንደሚደገፉ፥ ከዚህም በተጨማሪ እህቶቹ ዘወትር ቅዳሜ ማንነታቸው ምንም ይሁን ምን የሚንከባከቧቸው ዘመድ የሌላቸው አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ነፃ የጤና ምርመራ እንዲያገኙ እና መድሀኒት እንዲወስዱ በደስታ እንደሚቀበሏቸው ተነግሯል።

ይህ አገልግሎት በህክምና ድጋፍ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ምግብ ከሚያቀርቡላቸው እህቶች ጋር እንዲገናኙ የሚያደርግ ግብዣንም እንደሚጨምር የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ ገዳማዊያቱ በመንደሩ እና በአቅራቢያው ያሉ አረጋውያንን በታማኝነት እንደሚጎበኙ እና እነዚህ የጉብኝት መርሃ ግብሮች ለበርካታ ድሆች ወሳኝ መሆናቸው፥ ብሎም እነዚህ ፕሮግራሞች ባይኖሩ በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ በርካታ ሰዎች በተላያዩ በሽታዎች እንደሚጎዱ ተገልጿል።

የተዘረጋው የኢየሱስ ልብ

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በመከተል የሃኖይ የቅዱስ መስቀል ወዳጆች ገዳም እህቶች የኢየሱስ ክርስቶስን የማዳን ተልዕኮ ለማስቀጠል ለተረሱ ሰዎች የተዘረጉ እጆች፣ ልቦች፣ አእምሮዎች፣ አፎች እና እግሮች የመሆን ሃላፊነት እንዳለባቸው የተገለጸ ሲሆን፥ እነዚህ አገልግሎቶች ለድሆች ፍቅርን በማካፈል፣ በመርዳት እና በተለይ ሰብዓዊ ክብርን በመጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጡ ተመራጭ መገለጫዎች ናቸው ተብሏል።

የገዳማዊያቱ ተልዕኮ በዋናነት በህብረተሰቡ እና በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ተጎጂዎችን ሰብዓዊ ክብር ከፍ በማድረግ የጉባኤውን መስራች የሆኑትን የብፁዕ አቡነ ላምበርት ዴ ላ ሞቴ የቅዱስ መስቀል ወዳጆች ገዳም እህቶች የሕዝባቸውን ስቃይ ለመካፈልና ለማጽናናት ሩህሩህ ልብ እንዲኖራቸው እንዲሁም የተሰቀለውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚታዩ እጆች መምሰል እንዳለባቸው ያስተማሩትን አስተምህሮ ማሳካት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ሆኖም ግን ገዳማዊያኑ ይሄንን አገልግሎት በቬትናም እና በውጭ ሀገራት ካሉት በርካታ በጎ አድራጊዎቻቸው ትብብር እና ድጋፍ ውጭ ማሳካት እንደማይችሉ ተገልጿል።

ከዚህም ባሻገር እነዚህ አገልግሎቶች እህቶቹ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርስ በርስ እንድንዋደድ ለሰጠው ትእዛዝ ምላሽ የሚሰጡበት፣ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ የእግዚአብሔርን መገኘት የሚያሳዩበት፣ እንዲሁም ከክርስቶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያሳድጉበት አገልግሎት እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ ይህም በመሆኑ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢያንስ የምናደርገውን ሁሉ ለእርሱ እንደምናደርገው ያስታውሰናል ተብሏል።

 

 

 

 

10 Jun 2026, 16:20